የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የቅዳሴ ቤት በዓል ተከበረ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፐትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ቁጥራቸው ከሃያ ሰባት ያላነሰ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በርካታ ማህበረ ምዕመናን በተገኙበት ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2006 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤል ፅላት ከነባሩ ቤተክርስቲያን በመውጣት በቅዱስ ፓትርያርክና በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ወደ አዲሱ ካቴድራል የገባ ሲሆን በዚህ ዕለት የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አጽም ቀደም ሲል ከበረበት ቦታ ተነስቶ ወደ አዲሱ ካቴድራል በመግባት የብፁዕነታቸው የፋልስተ አጽም በዓል ተከብሯል፡፡
በማያያዝም ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ከማታው ዋዜማ ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ የማህሌቱና የቅዳሴው ሥርዓት ተከናውኖአል፡፡ ከዚያም በኋላ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት በቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በካህናትና በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራን እና በበርካታ ሕዝብ ታጅቦ የኡደት ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከትለብሱ ኃይለ እምአርያም በሚል የመጽሐፍ ቃል ተነስተው፤ የዕለቱን በዓል፣ የጌታን ዕርገት እና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የታሪክ ጎዞ በማውሳት ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ከዚያም የሚከተለውን ጉባኤው ቃና ቅኔ አበርክተዋል፤
መርአተ አማኑኤል ቤቴል እንተ ቆምኪ በዘአማኑኤል ገቦ፣
ሰርጎ አእዛንኪ እንቁ ወአጶሮግዮን ዘቦ፣
ከዚያም በማያያዝ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የበላይ ኃላፊ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጥሪ የተደረገላችሁ የመንግሥት መ/ቤቶች ተወካዮች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች የጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ኃላፊዎች፣ የሀገረ ስብከታችን ሠራተኞች፣ የወረዳዎች ሊቃነ ካህናት፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአጥቢያዎች ሰራተኞች እና ምዕመናን በሙሉ በዚህ ታላቅ ሥራ ላይ የተሳተፋችሁ በዛሬው ዕለት የተገኛችሁ ሁሉ ለሼር ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ሠራተኞች የዚህን ሕንጻ ቤተክርስቲያን የግንባታ ሥራ በመምራት የደከማችሁ የገዳሙ ማሕበረሰብ አባላት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረው የዚህ ታላቅ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በቸርነቱና በረድኤቱ ተፈጽሞ ለማየት ስላበቃን እንኳን ለዛሬው በዓል አደረሰን አደረሳችሁ፤
እንደሚታወቀው ሁሉ ወደር የሌለው የእግዚአብሔር ቸርነት እየረዳን በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እየታነጹ ናቸው፡፡ በየዘመናቱ የነበሩ እግዚአብሔርን የሚወዱ ለሥራው የተመረጡ ደጋጎች ሰዎች መሆናቸው ከቅዱሳት መጽሐፍት መረዳት ይቻላል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር የፈቀደላቸው ሰዎች ሁሉ በየዘመናቸው የፈጸሙት ተጋድሎ በአስተማሩት ትምህርት እና በፈጸሙት በጎ ሥራ ሁሉ የሚነበቡ መጻሕፍት ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ አርአያነት እና ለምሳሌነት ለትውልድ የሚተላለፉ መንፈሳዊ ታሪክ ትተው ስላለፉ ገድላቸውና ሥራቸው ሲዘከር ይኖራል፡፡ ይህ ዛሬ የምንገኝበት የዘዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው በ1959 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካኝነት ሲሆን ለብዙ ጊዜያት አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በደርግ ዘመነ መንግሥት በተፈጠረው የመንግስት ለውጥ ምክንያት ማሰልጠኛው ተዘግቶ እና የማሰልጠን ሥራውን አቋርጦ ለመሠረተ ትምህርት ጣቢያነት ውሎ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ዳግመኛ የተከፈተው በሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በታላቁ አባታችን በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አማካኝነት በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድና ውሳኔ በ1971 ዓ.ም ነው፡፡ በቀጣዩ ዓመት በ1972 ዓ.ም በብፁዕነታቸው ተዘጋጅቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበው መተዳደሪያ ደንብ በጉባኤው ሙሉ ድምጽ ጸድቆ የዘዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ተብሎ እንዲጠራ መደረጉ ከመዛግብት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የካህናት ማሰልጠኛው መሥራች የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ልንዘክራችው ከሚገቡት ባለ ታሪኮች አንዱ ናቸው፡፡ መካን ይቄድሶ ለሰብእ ወሰብእ ይቄድሶ ለመካን፡፡
ሰው ቦታን ያከብራል፣ ቦታም ሰውን ያከብራል፤ እንደሚለው በእግዚአብሔር ፈቃድ በብፁዕነታቸው ጥረት የነበረውን ይህን ሥፍራ የወንጌል አገልጋዮች የእግዚአብሔር አርበኞች እንዲሆኑ የሚሰጡበትና በቃለ እግዚአብሔር የሚታይበትን መንፈሳዊ ት/ቤት ለመሆን በቅቷል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተሰጠውን ትምህርት መተግባር ለመፈተን የሚአስችል ሕንጻ ቤተክርስቲያን አልነበረም አገልግሎቱ በዛፍ ሥር ይደረግ እንደነበር የስርክ ጸሎተ ምህላ፣ መሀረነ አብም፤ በዚሁ በቂ ባልሆነ ቦታ ይሠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ብፁዕነታቸው አገልግሎት የሚሰጥበት አነስተኛ መቃኞ እንዲሠራ ያደረጉ ሲሆን ሥራውም በየካቲት 1973 ዓ.ም ተጀምሮ በሶስት ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ግንቦት 19 ቀን 1973 ዓ.ም ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል እንዲገባ ተደርጓል፡፡
ይህ ቤተክርስቲያን ጠባብ ስለነበር እና ለቅኔ ማህሌት አገልግሎት የሚበቃ ሥፍራ ስላልነበረው እስከ ዛሬ ስንገለገልበት የነበረውን ያህል እንዲሰፋ የተደረገ ሲሆን ቤተክርስቲያኑ በአሁኑ ጊዜ አባቶች የሚስተናገዱበት ፅርሐ ጽዮን በ1973 ዓ.ም ስለተገነባ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ተብሎ ተባርኳል፡፡ በዚህ ዓመት የገዳሙ መተዳደሪያ ደንብ እንደገና ተሸሽሎ ጸድቋል፡፡
የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፋልስተ አጽም
ገዳሙም እንደሌሎች የኢትዮጵያ ገዳማት የነግህ እና የሰርክ የማህበር ጸሎት የሚደርስበት፤ ሆኖ በሥርዓተ ገዳም እየተመራ እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፡፡ ይህ ገዳምና የካህናት ማሠልጠኛ ከራሱና ከሌሎቹ አህጉረ ስብከት ለስልጠና የሚላኩ ሰልጣኞችን መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርትና ሥርዓት የቤተክርስቲያን ሥርዓት በቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን እያገናዘቡ ትምህርት እንዲማሩና ለደረሱበት የአገልግሎት መስክ ለቤተ ክርስቲያን እንዲቆረቆሩና እውነተኛ ትምህርትን እንዲአስተምሩ መምህራንን አፍርቷል፡፡
ከዚህ ሌላ ከመጀመሪያው ኮርስ ስልጠና በተጓዳኝ የአዳሪ ትምህርት ቤት በማቋቋም በአካባቢው እናት አባት የሌላቸውን ሕጻናትና ወጣቶች በመሰብሰብ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት የአብነት ትምህርት እንዲማሩ ተደርጎአል፡፡ ከዚህ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲኖራቸው እና በተግባርም የማስተማር ልምድ እንዲኖራቸው ለማድረግና ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ ማሰልጠኛው ዛሬ በልዩ ልዩ ከፍተኛ ማዕረግ ላይ የሚገኙ ምሁራንን አፍርቷል፡፡ በዚህ መሠረት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተምረው በአሁኑ ወቅት በሊቀ ጵጵስና ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ብፁዓን አባቶች ለማፍራት በቅቷል፡፡ ዛሬ በመካከላችን የማይገኙትን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን እና ብፁዕ አቡነ ይስሐቅን በገዳሙ ያስለፉትን የአገልግሎት እና መምህርነት ሥራ በማሰብ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች የሚማሩ ወጣቶች ወደ ገዳሙና ማሠልጠኛው ገብተው የክረምት የዕረፍት ጊዜአቸውን በትምህርት እና በስልጠና እንዲአሳልፉ ተደርጓል፡፡
በዚህ የትምህርትና የሥልጠና መርሐ ግብር መሠረት ስለ ሃይማኖታቸው እና ስለ ቤተክርስቲያናቸው እንዲአውቁ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውም ፈጽመው ከተመረቁ በኋላ በተሠማሩበት ሥራ የተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን የመጠበቅ እና ሃይማኖታቸውን እንዲአገለግሉ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም መነሻውና መሠረቱ ይህ ገዳም ነው፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ፍሬዎች ሊገኙ የቻሉት ገዳሙና ካህናት ማሰልጠኛው የመንፈሳዊ ዕውቀት መቅሰሚያ የገዳማዊ ሕይወት መገኛ የልማት እና የሥራ ባህል መማሪያ የቤተክርስቲያን መሠረት መጣያ አንድ ክርስቲያናዊ ቋንቋ የሚነገርበት ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሰፊ ቤተክርስቲያን እንዲሠራ ምኞት ቢኖራቸውም ሐምሌ 22 ቀን 1982 ዓ.ም በማለዳው ክፍለ ዕለት በደረሰባቸው ድንገተኛ ጥሪ ከመካከላችን ተለይተዋል፡፡ የታላቁ አባታችን ምኞት ውጥን እና ጅምር ሥራ ሁሉ ይህ ታላቅ ኃላፊነት ከወደቀባቸው እና ቀንበሩን በሚሸከሙበት አማካኝነት ሥራው ተጠናክሮ በተለመደው ሁኔታ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለወደፊቱም እንደዚሁ ይቀጥላል፡፡ ከእነዚህ መካከል አዲስ የታነጹት የአብነት ትምህርት መማሪያ የተግባር ቤት፣ ቢሮ፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ መጋዘኖች፣ የመጸዳጃ ቤት፣ የነባሮቹ ሕንጻዎች ዕድሳት ሊጣቀሱ ከሚችሉ ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ዛሬ በዚህ ገዳም ለመሰብሰባችን ምክንያት የሆነው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘበኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጥቅምት 4 ቀን 1997 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ አስቀምጡ፡፡
በመሆኑም ዛሬ ለመመረቅ በቃ፡፡ የዚህ ሕንጻ ምርቃት የገዳማችንን መስፋት የሚአበስር እና የታላቁ አባታችን የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምኞታቸውን መሳካት አመላካች ነው፡፡ ዛሬ ልጆቻቸው ሁሉ በዚሁ ተሰብስበን የምናከብረውን ደስታ በመካከላችን ተገኝተው ቢመለከቱ ኑሮ ምን ያህል ደስተኛ እንደሚሆኑ ሁላችንም እናምናለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማነጽ ባሰበ ጊዜ በልጁ በሰሎሞን እንዲታነጽ እንዲፈቀድለት እና እንዲሠራው ሁሉ ታላቁ አባታችን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ያሰቡትን እና የተመኙትን ይህንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን እኛ ልጆቻቸው እንደጀመርነው ሠርተን እንድንፈጽመው እና የዚህ መንፈሳዊ ታሪክ ባለቤቶች ለመሆን እንድንበቃ ያስቻለን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ በመሥራት የሚገኘው መንፈሳዊ በረከት የላቀ ስለሆነ የሰው ልጆች ከዚህ በረከት እንዳይጠቀሙ ጠላት ዲያብሎስ ልዩ ልዩ ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን መፍጠሩ ባይቀርም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረው ሁሉ ሥራ ይፈጸማል፡፡
ስለዚህ በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት በእመቤታችን አማላጅነት በቅዱሳን ተራዳኢነት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚያዩት በቤተክርስቲያናችን ልጆች ጥረት ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ተፈጽሞ እንሆ ለምረቃ በቅተናልና ደስ ይበላችሁ፤ ለዚህ ያደረሰን ቸሩ አምላካችን ይክበር ይመስገን፡፡ እንደቀደሙት አባቶቻችን እኛም ደግሞ በቀሪው ዘመናችን የእግዚአብሔር ቸርነት የሚነገርባቸው ቤተክርስቲያን የምትኮራባቸው ሀገር የምትከበርባቸው እና ለምሳሌነት ሊዘከሩ የሚችሉ መልካም ታሪኮችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ታጥቀን መነሳት ይኖርብናል፤ በዚህ መልክ ልንሠራቸው ከሚገቡ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት መካከል ይህ የሰው አእምሮ የሚለማበት መንፈሳዊ ተቋም አንዱ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ የደስታ ቀን ለዚህ ያበቃንን ፈጣሪያችንን እናመሰግነዋለን፤ በልዩ ልዩ መልክ የረዱንን ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም እናመሰግናቸዋለን፤ በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ ሪፖርት አሰምተዋል፤ የብፁዕነታቸው ሪፖርት እንደተጠናቀቀ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር የሚከተለውን ጉባኤ ቃና ቅኔ አበርክተዋል፡፡
ጎርጎርዮስ ሊተ ገዳምከ ባሕረ ሰሊሆም ይእቲ፡፡
አእይንተ ብርሃን ዘውስጥ ክልኤተ አምጣነ ረከብኩ ባቲ፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ብፁዓት አእይንቲክሙ እለ ርዕያ ወአእዛኒክሙ እለ ሰምአ በሚል ርዕስ ጅምረው የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ይህንን ጸጋ ያዩ አይኖቻችሁ የሰሙ ጆሮቻችሁ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ ነቢያት ጌታ ይወርዳል፣ ይወለዳል፣ ይሞታል፣ ይነሳል እያሉ ትንቢት ሲናገሩ ቆይተው አረፍተ ዘመን ገትቶአቸው ትንቢታቸው በተፈጸመ ጊዜ በአካል ጌታን አላዩም፤ ነገር ግን ከእነርሱ በኋላ የተነሡ ሐዋርያት ናቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል ያዩት፤ አዲስ ሕገ ወንጌልን የተማሩ እነርሱ ናቸው፡፡ ብዙ አባቶች ይህን ጸጋ ለማየት ቢጓጉም አረፍተ ዘመን ስለገደባቸው ይህን ጸጋ አላዩም፡፡ እናንተ ግን አይታችኋል፤ በዘመናችን ይህንን የተቀደሰ፣ የአማረና የሰመረ፣ ያጌጠና የተዋበ የእግዚአብሔር አምልኮ የሚፈጸምበትን ሕንጻ ቤተክርስቲያን በማየታችን እኛ እድለኞች ነን፡፡ እናንተም ለወደፊቱ አቅማችሁ በፈቀደ ብዙ ሥራ ይጠበቅባችኋል፤ ሥራውም የተሠራውን ቤተክርስቲያን መጠበቅና ቦታውን ማልማት ይኖርባችኋል፤ ቦታው የሰው አእምሮ የሚለማበት ነው፡፡ አሁንም ካለው በበለጠ የሰው አእምሮ ሊለማበት ይገባል፡፡ ዘመናችን የልማት ዘመን ነው፤ ትምህርት ቤት መንገድ፣ መብራት፣ ወዘተ ሁለገብ ልማት እየለማ ነው ያለው፡፡ በመጀመሪያ ስለ ሰላም መጸለይ አለብን ሰላም ከሌለ ሁሉም የለም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ስንለምን ቆይተናል፡፡ አሁን ግን እራሳችን እያለማን ኑሮን ማሸነፍ እየቻልን ነው ያለነው፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ብዙ ደክመውና ሠርተው የሥራውን ውጤት ለማየት እንኳን አበቃዎት፤ ለወደፊቱም ቀጣዩን ሥራውን እንዲሠሩ እግዚአብሔር ይርዳዎት፤ አምላካችን ይህንን ያማረ ሥራ እንድናይ ስለፈቀደልን ስሙ የተመሰገነ ይሁን በማለት ቅዱስነታቸው የመጨረሻውን ቃለ ምዕዳን አስተላልፈው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖል፡፡
{flike}{plusone}