የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ

0051

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ፣ በኃይለ መለኮቱ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንንም በልዩ አጠራሩ ጠርቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚካሄደው በዚህ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዓቢይ ጉባኤ ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡
“ወንሩጽ በትዕግሥት ኀበ ዘጽኑሕ ለነ ተስፋነ ዘሃይማኖት፣ ተጠብቆልን ወዳለ ተስፋ ሃይማኖት ለመድረስ በትዕግሥት እንሩጥ” ዕብ. 12፡1
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ርክበ ካህናት ተብሎ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚታወቀው፣ ከጌታችን በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን፣ ማለትም በመንፈቀ በዓለ ሐምሣ በየዓመቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲደረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትደነግግ ትልቅ ዓላማ አላት፤
የጉባኤው ዓላማ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመንፈስ ቅዱስ በተሰጣቸው ሐዋርያዊ ተልእኮ መሠረት በየተመደቡበት ሀገረ ስብከት ሲሠሩ በመንፈሳዊም ሆነ በአስተዳደራዊ ሥራቸው ያጋጠመ እክል ካለ በጋራ ተሰብስበው ችግሩን መፍታት የሚያስችል ጥበብ እንዲፈልጉለት ለማድረግ ነው፡፡
ከዚህም ጋር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ለሰው ሁሉ ማዳረስ የምትችልበትን ብልሐት በመንደፍ ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመጥራት ዝግጅት የምታደርግበት ዓቢይ ጉባኤ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ተልእኮ “ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት፤ ሂዱ፣ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለው አምላካዊ ትእዛዝ ነው፤ ማር. 16፡15፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሥራ በርከት ያለ ቢሆንም ተጠቃሎ ሲታይ ለሰብከተ ወንጌል ድጋፍ ሰጪ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ከስብከተ ወንጌል ውጭ ሌላ ተግባር የላትም፡፡
እኛ የሐዋርያት ተከታዮች የሆንን ሊቃነ ጳጳሳትና ከዚያም በየደረጃው የተሠየሙ ካህናት በሙሉ እንድንሄድ የታዘዝነው ወደ አንድ ሀገረ ስብከት ብቻ ሳይሆን ወደ ዓለም ሁሉ ነው፣
የላከን አምላክ ድንበርና ወሰን የሌለው እንደሆነ ሁሉ መንግሥቱም እንደዚሁ ድንበር የለሽ ነው፤ እኛም የእርሱን ሥልጣን ስለተቀበልን ተልእኮአችን ድንበርና ወሰን የለውም፡፡
ይህም ሲባል ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው ሥልጣን በድንበር የተገደበ አይደለም ለማለት እንጂ የሥራ መደብ የለም ማለት አይደለም፤
ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ ማየት ያለበት በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ በዓለም ሁሉ ወንጌልን እንዴት ማዳረስ እንዳለበት በሚቃኝ መልኩ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ወንጌልን ለዓለም የማድረስ ተልእኮ የኛ የሊቃነ ጳጳሳቱ እስከሆነ ከሁሉም ዘንድ ለመድረስ ጠንክሮ መሮጥ የኛ ግዴታ ነው፣
ሆኖም ሩጫው ዕንቅፋት አጋጥሞት ለጉዳት እንዳይዳርገን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ትዕግሥትና ማስተዋል ያልተለየው ሊሆን ይገባል፡፡
ትዕግሥትና ማስተዋልን ገንዘብ አድርጎ ሥራን መሥራት ትልቅ ጥበብ እንጂ ቸልተኝነት አይደለም፤
ሃይማኖት የሚጠበቀው፣ ድኅነትም የሚገኘው፣ በትዕግሥት እንደሆነ ራሱ ባለቤቱ “ወበትዕግሥት ክሙ ታጠርይዋ ለነፍስክሙ” በማለት አስተምሮናል፡፡
ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድም “አርምሞ ተዓግሥ ተዓቅብ ሃይማኖተ” ማለትም ነገሮችን ታግሦ በማስተዋል ማለፍ ሃይማኖትን ትጠብቃለች ብሎ አስተምሮናል፡፡
መልእክቱ በዋናነት መሮጥንና ትዕግሥትን አጣጥሞና አገናዝቦ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል፤ ይህ ለሥራችን መቃናት በጣም ጠቃሚ ነው፣
መዘናጋት እንዳይኖር እንሩጥ፣ ስሕተትም እንዳይበዛ በትዕግሥት ይሁን፣ የሚለውን መርሕ መከተል ለሁላችንም ይበጃል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስሲኖዶስ አባላት
ባለፈው ዓመት የርክበ ካህናት ጉባኤያችን በቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ብልሹ አሠራር እንዲታረም፣ ቤተ ክርስቲያናችን ልዕልናዋና ክብሯ፣ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ፣ አንድነትዋና ሥርዓቷ፣ እንደነበረው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን መወሰናችን ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸው ውሳኔዎች በጥናት ተመሥርተው ደረጃ በደረጃ በተግባር ይተረጎሙ ዘንድ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፤
ኮሚቴዎቹም የመጀመሪያ ዙር ጥናታቸውን በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አቅርበው እንዲታይ አድርገዋል፡፡
ከዚያም በኋላ ጥናቶቹ በሊቃውንትና በባለሙያዎች እየታገዙ የቀጠሉ ቢሆኑም በሥራው ሂደት በመጠኑም ቢሆን አንዳንድ መሰናክሎች አልነበሩም ማለት አይቻልም፤
ይሁን እንጂ ቀዋሚ ሲኖዶስ በየጊዜው በሚያደርገው ክትትልና በሚሰጠው አመራር መልክ እየያዙና መሠረተ ደልደላ እየሆኑ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡
በተለይም በማእከል የተቋቋመው ኮሚቴና ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደንብ አጥኚ ተብሎ በድጋሚ የተሰየመው ኮሚቴ በአንድነት ሆነው ሥራውን ለመሥራት ያሳዩት ቅን ተነሳሽነት ለሥራው ጥራትና ቅልጥፍና ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ላይ የሚታየው ክፍተት የቆየና ሥር የሰደደ ከመሆኑ አንጻር በአጭር ጊዜ ይስተካከላል የሚል እምነት ብዙ ላይኖረን ይችላል፤
ይሁንና በጀመርነው መሥመር ከቀጠልን ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ለውጦችን ማየት እንደምንችል ጥርጥር የለንም፡፡
ሆኖም መልካም አስተዳደር በፍጥነት እንዲሰፍን ወሳኝ የሆኑ መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉን በዚህ አጋጣሚ ሳንጠቅስ አናልፍም፤ እነዚህም፤
1.    በየአቅጣጫው ለሚነፍሱ የውጭ ነፋሳት የማይበገር አንድነት፤
2.    ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ማእከል አድርጎ መሥራት፤
3.    በእናውቅላችኋለን ባዮች ግራ ሳይጋቡ በራስ በመተማመን መወሰን፤
4.    የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም ይሁን በማን እንዳይገሠስ ጥብቅና መቆም የመሳሰሉ ባህርያት ለዚህ ጉባኤ አስፈላጊ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ሌላው ከዚህ ጋር አያይዘን ማንሣት የምንፈልገው ዓቢይ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን የሰው ኃይል በአግባቡ አልምቶ ለተሻለ ውጤት የማብቃቱ ጉዳይ ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ያለው የሰው ኃይል እንደሌላው ዓለም አጠቃቀም ብንጠቀምበት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ በአጠቃላይ ይበቃ እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው በዓለም ውስጥ የሚገኘው ካህን በአጠቃላይ ቢበዛ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ላይሆን ይችላል፣
ይሁንና የኛ ቤተ ክርስቲያን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የካህን ብዛት እያላት ለምን ብዙ የሥራ ክፍተቶች በየጊዜው ይከሠታሉ? የሚለውን ጥያቄ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በውል ሊያጤነው ይገባል፡፡
እየተፈጠረ ያለው ክፍተት ባጭሩ ለመጠቆም ያህል ያለንን የሰው ኃይል በዕውቀት አልምተን ክፍተቱን ከመሙላት ይልቅ “በምንስ የደነቆረ ምን ሲል ይኖራል” እንደሚባለው ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩት አስገዳጅ ሁኔታዎች ያመጡብንን የዘመናት ልምዶች እንደመልካም ባህል ይዘን በዚያው በመቀጠላችን ክፍተቱ ተፈጥሮአል የሚል ጽኑ እምነት አለን፤
ለቤተ ክርስቲያን  አይደለም ለራሱ እንኳ በአግባቡ መቆም ያልቻለ የሰው ኃይል ይዘን የትም መድረስ አንችልም፤
ሆኖም ይህን ችግር ለማስተካከል ያለውን በማፍለስ ሌላ አዲስ ተክልን መትከል ሳይሆን ያለውን የሰው ኃይል በማልማትና በሥሩ የሰለጠነ የሰው ኃይልን በማስከተል ማስተካከል እንዳለብን ሊሠመርበት ይገባል፡፡
ስለሆነም ያለንን  የሰው ኃይል በዕውቀት በማልማት ክፍተቱን መሙላት ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ይህ ዓቢይ ጉባኤ ሊያስብበት ይገባል እንላለን፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ያለንበት ጊዜ እጅግ በጣም ከፍተኛ ውድድር የሚታይበት ጊዜ ነው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ባደረገችው ርብርቦሽ ዓለም በአድናቆት የተናገረለት የልማትና የዕድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚህ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ገጠሩ ድረስ በተንቀሳቀስን ቁጥር የምናየው ነገር ሁሉ ልማትና ግንባታ ነው፣ ትምህርት ቤቱ፣ የጤና ኬላው፣ የመስኖ እርሻው፣ የትራንስፖርት ግንባታው፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ሁሉ ሲጣደፍ ይታያል፤ ይህ ከእግዚአብሔር  ለኢትዮጵያ የተሰጠ ታላቅ በረከት ነው፡፡
በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን የልማት በረከቱ ባለበት ብቻ እንዲቀጥል ሳይሆን ካለበት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕዝቡን በማስተማር ለልማቱና ለዕድገቱ በሰፊው መንቀሳቀስ አለባት፣ የተለመደውን ሀገራዊ ኃላፊነቷም መወጣት አለባት፣
ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህች ሀገር አንድነት መጠበቅና ለህልውናዋ ቀጣይነት ለሦስት ሺሕ ዘመናት ያህል የሠራቸው ጉልህና ደማቅ ሥራ አሁንም መድገም አለባት፣
ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬም እንደቀድሞው ሃይማኖታዊና ልማታዊ ሥራን በመሥራት የመሪነት ሚናዋን የምታጠናክርበት አቅጣጫ ይህ ጉባኤ መቀየስ አለበት፡፡
ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተልእኮዋን በብቃት ከመወጣት ባሻገር በትምህርት ዘርፍ፣ በጤና ዘርፍ፣ በራስ አገዝ ልማት ዘርፍ፣ ወዘተ … በመሳሰሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ሕዝቡን አስተባብራ በየቅፅረ ቤተ ክርስቲያኑ መገንባት አለበት፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰበሰብበት ዋና ዓላማ እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ዓበይት ጉዳዮችን በማጥናት፣ በመገምገምና በመወሰን የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ነው፡፡
ስለሆነም መልካም አስተዳደር በማስፈን ለተሻለ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መሠረት የሚሆኑ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤው የተጣለበትን ኃላፊነት በተገቢው ይወጣ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ  ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

ግንቦት 6 ቀን 2006 ዓ.ም

አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

{flike}{plusone}