በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. በየዓመቱ የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በድምቀት ተከበረ

1

 እንኳን ለኃያሉ መልአክ ለሊቀ መላእክት ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን ፡፡
እኛ የምናመልከው አምላክ ኪሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፡፡ ት.ዳን.3፥17
በየዓመቱ ታህሳስ 19 ቀን የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በዚህ ዓመትም እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ውልዋል፡፡በዓሉ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባለበት ሁሉ ተከብሮ የሚውል ሲሆን ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናትና መዘምራን እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ሥነ ስርዓት በየዓመቱ ሁል ጊዚ ተከብሮ ይውላል፡፡በዘንደሮ ዓመትም እንደተለመደው በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባሉ የቅዱስ ገብርኤል አጢቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሉበት ሁሉ በዓሉ በድምቀት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ምእመናንም ተኝተዋል፡፡በተለይም አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ  በመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እጅግ በደመቀ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውሏል፡፡በበዓሉ ላይ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናት፣ መዘምራንና ብዛት ያለቸው ምዕመናን በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡
በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከታህሳስ 19 ቀን ጀምሮ ሲሆን የገዳሙ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምረው ለ32 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ ለእምነቱ ተከታዮች ምእመናን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እጀግ በጣም የሚያስደንቅ በዓል ነው፡፡
ዛሬ የምናከብረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከባቢሎን እሳት ያዳነበት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው በብሉይ ኪዳን ዘመን ከ605-562 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነገሠው በናቡከደነጾር ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከጣዖት አምላኪና አስመላኪ ኀያላን ነገሥታት መካከል አንዱ ናቡከደነጾር ነበር፡፡ ምስሉ የቆመው በ587 ቅ/ል/ክ እንደሆነ መተርጎማን ያስረዳሉ፡፡ ዳን.3፥1 ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን በማረከበት ዘመን ዳንኤልንና ሦስቱን ሕፃናት በልዩ ሁኔታ አክብሯቸው ነበር፡፡
•    ዳንኤልን ብርጣሶር አለው አሰበ በል አምኃ ቤል ሲል ነው
•    አናንያንም ሲድራቅ አለው ወልደ ሰቃየ አትክልት /አትክልተኛ/ ማለት ነው
•    ሚሳኤልንም ሚሳቅ አለው ፀሐቂ ተጋሂ ፍንው ለግብር መልእክት /ትጉህ ፈጣን መልእክተኛ/ ማለት ነው፡፡
•    አዛርያንም አብደናጎም አለው ገብረ ዳጎን /የጣዖት አገልጋይ/ ማለት ነው
የቀድሞ ስማቸው ትርጉም ግን 1)ዳንኤል ማለት ፍትሕ እግዚአብሔር ዳኛ እግዚአብሔር
2)አናንያ ማለት ደመና 3)ሚሳኤል ማለት ሰምዓኒ እግዚአብሔር /እግዚአብሔር ስማኝ/ 4)አዛርያ ማለት ረድኤት ማለት ነበር፡፡ ት.ዳን.1፥7 ንጉሡ እነዚህን ሕፃናት ለሦስት ዓመት በቤተ መንግሠት ጥሩ ምግብ እየተመገቡ የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያጠኑ ዘንድ አዝዞ ነበር፡፡
እነርሱ ግን ትምህርቱን እየተማሩ በንጉሡ ቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ሳይመገቡ ጥራጥሬና ውኃ እየተመገቡ በፈተና ያለፉ ነበሩ፡፡ ዳን.1፥8-21 ጠቢባንና አስተዋዮች በመሆናቸው በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ተሾሙ፡፡ ዳን.2፥46-49 የሠለስቱ ደቂቅ በንጉሡ ዘንድ መወደድና መሾም ያስቀናቸው ባቢሎናውያን ለናቡከደነጾር “በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሸምካቸው ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ አምላክህን ያላመለኩ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ” ብለው ከሰሷቸው ያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጣና እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ እነርሱም አንሰግድም አሉ፡፡ ዳን.3፥13-19”
ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ለምስሉ ለማሰገድ ጥረት አድርጓል 1. በመጀመሪያ ዐዋጅ በማወጅ ነው ይህ ዐወጅ ከተራው እስከ ባለሥልጣናቱ ያሉትን የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም ባለሥልጣናቱ ቀድመው በመስገድ አርአያ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡ 2. ሁለተኛው የሕዝቡን ልብ በሙዚቃ እንዲደሰቱ በደስታው ተውጠው ሳያስቡት እንዲሰግዱ ማድረግ 3. የመጨረሻው በማስፈራራት /ወደ እሳት ትጣላላችሁ እያለ/ እንዲሰግዱ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢያባብልና ቢጥር ሠለስቱን ደቂቅ ለማሰገድ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡
ከሠለስቱ ደቂቅ ሦስት ነገሮችን እንማራለን ማመን፣ መቁረጥ እና ማድረግን፡፡ ሃይማኖት እነዚህን 3 ነገሮች ይፈልጋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት በእግዚአብሔር ፍጹም አመኑ፣ ይህንንም እምነታቸውን ሲገልጡ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” በማለት ተናግረዋል፡፡ የመጣባቸውን ሁሉ ለመቀበል ወሰኑ ቆረጡ “አምላካችን እኛን ማዳን ይችላል ነገር ግን ፈቃዱ ከዚህ እሳት ገብተን ሠማዕትነትን እንድንቀበል ቢሆን ከእሳት እንገባለን” በማለት አንድ ልብ፣ አንድ ቃል ሆነው አቋማቸውን ገለጡ፡፡ የቆረጡትን ነገር አደረጉት፤ ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ሦስቱም ነገሮች ስለተፈጸሙ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እሳቱን አብርዶ አዳናቸው፡፡
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” በማለት የተናገረው ቃልም ተፈጽሞላቸዋል፡፡ /መዝ.33፥7/ ጠባቂ መልአካቸው ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ውስጥ ገብቶ ከመከራ ሥጋ አድኖአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና መልአኩል ልኮ የፈጸመውን ትድግና ያየው ናቡከደነጾር “ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡” ዳን.3፥28-30
  የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል  ተራዳኢነትና አማላጂነት አይለየን አሜን ፡፡

{flike}{plusone}