የአቃቂ ቃሊቲ እና የልደታ ክፍላተ ከተሞች አድባራት እና ገዳማት ተወካዮች በመዋቅራዊ ረቂቅ ሰነድ ዙሪያ ላይ ውይይት አካሄዱ

2527

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአቃቂ እና ልደታ ክፍላተ ከተሞች ሥር የሚገኙ የአድባራት እና የገዳማት ተወካዮች በመዋቅራዊ ረቂቅ ሰነድ ዙሪያ ለመወያየት ዛሬ አርብ ታህሳስ 11 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተገኙ ሲሆን ከሁለቱም ክፍላተ ከተሞች ከሚገኙ ከ30 ያላነሱ አድባራት እና ገዳማት ብዛታቸው 480 የሚደርስ  ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅድስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎት እና ቡራኬ አድርገው ጉባኤውን ከጀመሩ በኋላ በመቀጠልም ብፁዕነታቸው የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ለቤተ ክርስቲያናችን ይጠቅማል ይበጃል ብለን በምንሠራው መልካም ሥራ ስለ ሥራን እየተወቀስን ነው ያለነው አዲሱ የሥራ መዋቅር ረቂቅ ጥናት ለውይይት ቀርቦ ስንወያየበት ብንቆይም እንኳን አንድአንዶቹ ግን በሰነዱ ላይ ቅሬታ አለን እያሉ ስለሆነ በዚሁ መሠረት ረቂቅ ጥናቱ በሊቃውንት ጉባኤ እንደሚገመገም ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እየሰጠበት ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ውይይቱን አካሂደን አስፈላጊው ግምገማ በሊቃውንት ይገመገማል ካሉ በኋላ ሀገረ ስብከቱ ይህንን የውይይት መድረክ የከፈተው በራሱ ተነሳሽነት ሳይሆን በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ነው በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በመዋቅራዊ ረቂቅ ሰነዱ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ በንባብ ለጉባኤው አሰምተዋል፡፡
በመቀጠል የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በጥናት መግለጫ አቅራቢው እንደተገለጸው ለጥናቱ መነሻ የሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ችግሮች ስናነሳ የመዋቅር የአደረጃጀት፣ የአሠራር ችግር፣ ሀገረ ስብከቱ ለአራት መከፈሉ፣የቤተ ክርስቲያን ሀብት ያለ አግባብ እየባከነ በመሆኑ፣ የአገልጋዮች ችግር ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እየሄደ የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ በመሆኑ፣ በካህናት እና ምዕመናን መካከል አለመግባባት መፈጠሩ፣ ችግር የፈጠሩ ሰዎች ዝውውር፣ የስብከተ ወንጌል መዳከም ከአስር ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን መውጣታቸው የተጠሪነት እና የመወሰን ድርሻ አለመኖሩ፣ የሰው ሀብት አስተዳደር ችግር ቅጥር በወገን፣ በትውውቅ፣ በሙስና፣ በብልሹ አሠራር፣ መከናወኑ፣ እና ግልፅነት የጐደለው ቅጥር መፈጸሙ፣ የደመወዝ አከፋፈል ሙያን፣ የአገልግሎት ዘመንን ያገናዘበ አለመሆኑ፣ ሀገረ ስብከት የማያውቃቸው ቅጥር ሠራተኞች መኖራቸው፣ የሥራ መመሪያ አለመኖሩ፣ ባለሙያዎች አለመቀጠራቸው፣ ወጥና ግልጽ የሆነ ዝውውር አለመኖሩ፣ አድራሻን ያላገናዘበ ዝውውር አለመኖሩ፣ የሥራ አፈጻጸም ሥራ የተጠናከረ አለመሆኑ፣ ሰው በሥራው ተመዝኖ አለመሾሙ፣ የስልጠና እና የአቅም ግንባታ ሥራ አለመኖሩ የደረጃ ዕድገት እና የሹመት ሥርአት አለመኖሩ፣ የአበል አከፋፈል ችግር መፈጠሩ የሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ፣ የሒሳብ አሠራር ችግር መኖሩ፣ የሙዳይ ምፅዋት አከፋፈት ችግር፣ ገቢ ሳይሆን ሕገ ወጥ ክፍያ መፈጸሙ ያልተፈቀደ ሙዳዬ ምፅዋት ማዘጋጀትና በየቦታው ማስቀመጥ፣ የሙዳዪ ምፅዋት መጥፋት እና መሰበር፣ መዘረፍ፣ የዕለት ገቢና የደረሰኝ አጠቃቀም ችግር፣ የተከለከለ ደረሰኝ መጠቀም፣ በርካታ ገንዘብ ወደ ባንክ አለማስገባት፣ ከምዕመናን የሚሰጥ ስለት ለግል ጥቅም ማዋል፣ የገቢ ደረሰኝን በማጭበርበር እስከ መታሰር መድረስ፣ በሥራ ላይ የዋለ ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር አለመኖሩ፣ የሂሳብ ሪፖርት አለመቅረብ፣ የውጭ ምንዛሬን በንብረት መልክ በማስገባት ለዘረፋ መጋለጥ የምንዛሬ ውጥነት አለመኖሩ፣ ሕጋዊ ጨረታ አለመኖሩ፣ በቃለ ጉባኤ ያልተመዘገበ ወጪ መኖር፣ የቁጥጥር ሥርአት ሙያዊ አለመሆን የስነ ምግባር ችግርና የሙስና ችግር መኖሩ አንዳንዶቹ በቤ/ክርስቲያኒቱ የምንኩስና ሥርዓት አለመመራት፣ የዘረኝነት በሸታ መስፋፋት፣ የአገልጋዮች መከፋፈል የሚሉት ሲሆን መዋቅሩ እነዚህን ችግሮች ሊፈታ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ከተሰታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ተገቢው ምላሽም ተሰጥቷል፡፡

{flike}{plusone}