በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር ለሚገኙ አድባራት እና ገዳማት ተወካዮች ለሁለት ቀናትየቆየ የመዋቅር ረቂቅ ሰናድ ውይይት ተካሄደ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር የሚገኙ አድባራት እና ገዳማት ተወካዮች ከህዳር 29 – 30 ቀን 2006 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ ስልጠና እየተሰጣቸው የሚገኝ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊዎች ከሰላሳ አድባራት እና ገዳማት የተውጣጡ ናቸው፡፡ አጠቀላይ የሰልጣኞቹ ብዛትም ከ480 የማያንሱ መሆናቸውን ተረጋግጧል፡፡
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እየተሰጠ የሚገኘው የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ ጥናት ሥልጠና በአራዳና ጉለሌ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር ለሚገኙ የአድባራት እና ገዳማት ተወካዮች ከተሰጠው ቀጥሎ ለሁለተኛ ዙር እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በስልጠናው መጀመሪያ ላይ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅድስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ለቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮች ሕግ ያስፈልጋቸዋል ምክንያቱም ሕግ ከሌለ አገልጋዮች መብታቸውን ሊአስከብሩ አይችሉም፡፡ እኛም በምንሠራው ሥራ ልንጠየቅ የምንችለው ሕግ ሲኖር ነው፡፡ በዚህ በቀረበው የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ ላይ ሐሳብ መስጠት ይቻላል የምንሰጠው ሀሳብ ግን ከቅንነት የመነጨ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳን ተለያይተን አንድ ሆነን እንኳን የእኛን መለያየት የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው እኛ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ብለን በዘረጋነው የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ ለምን ተብሎ ነው ስማችን በከንቱ የሚጠፋው? በአንድ ላይ እየተወያየን ችግሮችን መፍታት ይኖርብናል እንጂ ከዚህ ውጭ የሆነ ተግባር ልንፈጽም አይገባንም በማለት ብፁዕነታቸው የመክፈቻ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል በመቀጠልም የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ በመዋቅሩ ረቂቅ ሰነዱ አጠቃላይ ዝርዝር ዙሪያ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ ማዕከል፣ የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል የመዋቅር ረቂቅ ሰነዱ ለ3 ወራት ያህል የተዘጋጀ ሲሆን በመጀመሪያ ሰነዱ ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ ለብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ የመዋቅር ረቂቅ ሰነዱ የተዘጋጀው ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ ቃለ ዓዋዲን እና ሌሎች ደንቦችን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይህ ባለ13 ጥራዝ የመዋቅር ረቂቅ ሰነድ መነሻ ያደረገው ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ የነበረውን የመዋቅር፣ የአደረጃጀት፣ የስነ ምግባር፣ የሰው ሀብት እና የመሣሠለው ችግር በማየት ነው የመዋቅር ረቂቅ ሰነዱ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርቦ መመሪያ የተሰጠበት ሲሆን ለቅዱስ ሲኖዶስም ቀርቦ ከታየ በኋላ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተያየት ከሰጡበት በኋላ ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ እና ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ከቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ መዋቅሩ የሰው ሀይል ትመና፣ የደመወዝ እስኬል የአገልጋዮች መስፈርት፣ የፋይናንስ፣ የልማት፣ የዕቅድ፣ የኦዲት እና ኢንስፔክሽን የስልጠና ማዕከልን እና የመሳሰለውን ያካትታል በማለት ግልፅ የሆነ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ከተሳታፊዎች በስልጠናው የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ጥያቄዎችም ተነስተው ተገቢው ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በመጨረሻም የቡድን ውይይት ተደርጐ ስልጠናው ተጠናቅቆአል፡፡
{flike}{plusone}