የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት ሊቀህሩያን ሰርፀ አበበ ከአድባራት እና ገዳማት ተወካዮች ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር አደረጉ

                                                                                                                                                                                      

2223

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት ሊቀህሩያን ሰርፀ አበበ ከቦሌ ክፍለ ከተማ አድባራት እና ገዳማት ተወካዮች ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር ያደረጉ ሲሆን በዚሁ ዕለት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ሀሳብ እንዲሰጡ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተጋበዙ ሲሆን ሥራ አስኪያጅ ንግግር ካደረጉ በኋላ ብፁዕነታቸው የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የዛሬው መርሐ ግብር አዲሱን የሀገረ ስብከታችንን ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ በመኮንንን፣ የምንቀበልበት፣ ሊቀ ህሩያን ሠርፀ አበበን የምናስተዋውቅበት ሲሆን ላዕከ ወንጌል በዕደ ማርያም ይትባረክ ከስራ አስኪያጅነት ወደ ስብከተ ወንጌል የሸኘንበት ነው፡፡

ብፁዕነታቸው አክለው ለተሰብሳቢው አካል የክፍለ ከተማውንም ሆነ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅም ምን እንስራ ልትሉአቸው ይገባል ገንዘባችንን በአግባብ ከተቆጣጠርን ገቢው ተመልሰው ወደ እኛው ነው የሚመጣው ለምዕመናን አገልግሎት እየሰጠን፣ እየፀለይን የምንኖር ከሆነ አንድ አገልጋይ የአንድ ምኒስቴር ደመወዝ ያህል ሊያገኝ ይችላል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ጥሩ ጠንካረን ተግባብተን እና ተከባብረን ከሠራን ነው፡፡ እንዱ ከልክ  ያለፈ ከበሬታ ሲሰጠው አንዱ ሊናቅ አይገባም፡፡ ጉድለታችንን ልትነግሩን እንጂ ልታሙን አይገባም፤ ጉድለት የሌለው ማንም ሰው የለም፤ እግዚአብሔር ከነጉድለታችን ነው የተሸከመን አንዱ ለሌላው መስታወት መሆን አለበት፡፡ አንዱ ከአንዱ ጋር መጻጻፍ ጉዳት እንጂ

ጥቅም የለውም፡፡

ችግር የሚፈታው በውይይት ነው፡፡ እርስ በእርሳችን መፈቃቀር አለብን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን እርስ በርሳችሁ ብትፋቀሩ የእኔ ደቀ መዛሙርት መሆናችሁን ዓለም ያውቃል ብሎአል፡፡ ጥርስ እና ከንፈር ሲደጋገፍ ነው የሚአምረው በዚህ ዓለም እስከመቼ እንደምንኖር አናውቅም፡፡ ስለዚህ መመካከር አለብን ሙስናን ማጥፋት አለብን፤ ሙስና ሰይጣናዊ ሥራ ነው በሙስና ጉዳይ ማስፈጸም አይገባንም ጉዳይ አልፈጽምም የሚል አካል ካለ ይግባኝ አለ፡፡ ሙስና አቀባዩ የዘረፈውን ካልሆነ በስተቀር ከየት ሊያመጣው ይችላሉ፣ ዘርፎ ለዘራፊ መስጠት የወንጀል ወንጀል ነው፡፡ የንፁሀንን ሰዎች ስም የሚያስጠፋ ሰው እግዚአብሔር የእጁን ሊያሰጠው ይችላል በማለት ሰፋ ያለ ማበራሪያ ከሰጡ በኋላ ሊቀህሩያን ሰርፀ አበበ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ሥራ እስኪያጅ በበኩላቸው ስለሙስና አስከፊነት ሲገልጽ ለዘመናት ጥንተ አብሶ ሆኖ የቆየውን መጥፎ ተግባር እንድንቃወም ብፁዕ አባታችን አቡነ እስጢፋኖስ አስገንዝበውናል፡፡ ዕፀ በለስን የበላ አዳም ነው የሞቱት ግን ብዙኃን ናቸው፡፡ አሁንም በለሱን የሚበላ አንዱ ሊሆን ይችላል የምንጠፋው ግን ብዙዎች ነን፡፡ ሁሉም ሌባ ላይሆን ይችላል የሌብነቱ ልምድ ያለቸው ብቻ ናቸው ይህንን ተግባር የሚፈጽሙት እንክርዳድ ከስንዴ ጋር ተደባልቋል ወገባችን የታጠቀ ሊሆን ይገባዋል ጫማችን፣ ልብሶችን በካህን ሕይወት ትርጉም አለው፡፡ ሁላችንም ንዑስ አነ እምአኃውየ ልንል ይገባናል፡፡
ሁላችንም ከተባበርን ተራራ መናድ እንድችላለን በአዲሱ አወቃቀር ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፤ በየክፍለ ከተማው ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ በአንድ ሊቀ ጳጳስ ጩኸት ብዙ ሥራ ተሠርቷል ድካማችን ከሜዳ ላይ ሊቀር አይገባም፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው መራራውን ጣፋጭ፣ ጣፋጩን መራራ፣ ብርሃኑን ጨለማ፣ ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ ወዮላቸው ይላል፡፡ መርዙን ማር ማሩን መርዝ የሚያደርጉ ክፍሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በጣም የሚወደዱ ሰዎችም አሉ፤ እንክርዳድም ስንዴም አለ፤ በአንድ ወቅት እንጨቶች ምሳርን ለማጥፋት መከራ ይበላል ከመካከላቸው አንዱ ጥፋተኛው ምሳር ሳይሆን ከመካከላችን የሚወጣው ጠማማ እንጨት ነው አለ ይባላል፡፡
  ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዝመራው ብዙ ነው ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው እንጀራው ብዙ አዝመራ አለ፡፡ ስለዚህ ጠንክረን መሥራት ይገባናል በማለት አብራርተዋል፡፡ በማያያዝም የቀድሞው የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ላዕከ ወንጌል በዕደ ማርያም ይትባረክ በበኩላቸው የምንመገበው ምግብ፣ የምንለብሰው ልብስ፣ የምንጠለልበት መጠለያ የስብከተ ወንጌል ምርት ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል ተራራን ይንዳል ቅዱስ ጳውሎስም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ልዩ ክብር ሲሰጥ ወንጌልን በመስበክ ለሚደክሙ ዕጥፍ ዋጋ ይገባቸዋል ይላል፡፡
የስብከተ ወንጌል ጉዳይ የኑሮ ጉዳይ ነው፤ ስብከተ ወንጌል ከምንም በላይ ነው ሁሉ ነገር የሚቃናው በስብከተ ወንጌል ነው በማለት አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ገንቢ የሆነ አስተያየት ከተሰጠ በኋላ በብፁዕነታቸው ጸሎተ ቡራኬ ጉባኤው ተጠናቅቋል፡፡

{flike}{plusone}