ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2006 ዓ.ም አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዓውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
• በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የዘመናት ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ከሁለት ሺ አምስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማቴዎስ ወደ ሁለት ሺሕ ስድስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ!!!
“ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እግዚአበሔር፣ እርሱን ፈልገው ያገኙት ዘንድ፣ ሰዎች የሚኖሩባቸውን የዕድሜና የዘመናት መጠን ሠራ” (የሐ.ሥራ.17÷26-27)
አምላካችን እግዚአብሔር፣ ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል፣ የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት፣ ፍጥረታትን ውብ አድርጎ ሲፈጥር፣ ዘመናትንና ዕለታትን ለመለየት ያስችሉ ዘንድ፣ ብርሃናትን በሰማይ ጠፈር ፈጥሮአል፤ (ዘፍ.1÷14-19) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ የሰው ልጅ፣ በብርሃን ዑደት እየታገዘ፣ ዘመናትን፣ ወቅቶችን ፣ወራትንና ዕለታትን ለይቶ በማወቁ፣ መርሐ ግብር እያወጣ፣ ለሥራው አፈጻጸም ይጠቀምባቸዋል፤ በመሆኑም፣ ዘመናት፣ ለሥራችን የሚሰጡት ግብአት፣ ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል፤ እግዚአብሔር፣ ዘመናትን በሰዓታት፣ በቀናት፣ በወራት በወቅቶችና በዓመታት፣ ከፋፍሎ የፈጠረበት ዋና ምክንያት፣ በእነርሱ መለኪያነት፣ አቅደን፣ አልመንና ጠንክረን በመሥራት፣ ራሳችንን፣ ቤተ ሰባችንን፣ ሀገራችንንና በአጠቃላይ ዓለማችንን፣ ለኑሮ የተመቸች፣ ውብና ለም አድርገን እንድንከባከብና እንድንጠብቅ ነው፡፡ (ዘፍ.2÷15)
የዘመን ጸጋ፣ በሥጋዊ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ከፍተኛ ትርጉም አለው፤ የእግዚአብሔር ቃል፣ ከፍ ብሎ እንደነገረን፣ ዘመናት፣ እግዚአብሔርን ፈልገን ለማግኘት የሚያስችሉን መሣሪያዎች ናቸው፤ ይህም ማለት፣ እያንዳንዱ ዓመት፣ በሰው አእምሮ ውስጥ ጥሎት የሚያልፍ፣ ተግባራዊ ትምህርትና ዕውቀት አለ፤ ከዚህ አኳያ፣ ሰው፣ በየዓመቱ ከሚቀስመው ሰፊ ግንዛቤ፣ ዕውቀቱን እያሰፋ፣ ወደ ተሻለ ማስተዋል ይሸጋገራል፤ ጤናማ ማስተዋልን ሲያገኝ፣ ፈጣሪውን ወደ መፈለግና ወደ መከተል፣ ፍጹም ሰው ወደ መሆንም ይደርሳል፤ በዚህ ምክንያት፣ ዘመን፣ ሰው፣ ፈጣሪውን እንዲያውቅ የሚያስችል፣ የማብቃት ጸጋ አለው ማለት ነው፤ (የሐ.ሥራ. 17÷26-27)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት!
እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥር ዓላማ አለው፤ ተቀዳሚ ዓላማውም፣ በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን፣ እርሱን እንድናውቅ፣ እርሱን እንድናምን፣ እርሱን እንድናመልክና ለእርሱ እንድንታዘዝ፣ በእርሱም የዘላለም ሕይወትና ክብር እንድናገኝ ነው፤ (ሮሜ.1÷19-21፤ ዮሐ.20÷31)
በምድራዊው ኑሮአችንም እንዳንቸገር፣ ልዩ ልዩ ሀብት ያላትን ምድር ፈጥሮ ሰጥቶናል፤ ይሁንና፣ ምድራችን፣ በማኅፀንዋ የተሸከመችውን ልዩ ልዩ ጥሬ ሀብት፣ መልክና ጣዕም እንዲኖረው አድርጎ ወደ ጥቅም የመለወጡ ኃላፊነት፣ ለእኛ አስረክቦአል፤ ይህም፣ እግዚአብሔር፣ እኛን የሥራው ተሳታፊዎች የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር፣ የሥራ ሁሉ ጀማሪ ከመሆኑም ሌላ፣ ሁሌም ሲሠራ የሚኖር፣ ሥራ ወዳድ አምላክ ነው፤ (ዮሐ. 5÷17) የእኛንም አካል ለሥራ የተመቸ አድርጎ መፍጠሩ፣ የሥራው ተሳታፊዎች እንድንሆን ብሎ እንደሆነ ልናስተውል ይገባል፤ ስለለሆነም፣ እኛ፣ ታታሪ ሠራተኞች በሆን ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ተባባሪዎች እንሆናለን፤ ከሥራ በራቅን ቁጥር ደግሞ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ላለመተባበር እየከጀልን እንደሆነ፣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንጸር፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዓቢይ ነገር፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኃላፊነቴ ምን ሠራሁ? ምንስ ቀረኝ? በአዲሱ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋር ተባባሪ ልሁን የሚለውን ነው፤ ሥራ መሥራት ማለት፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር ማለት ነውና፤ እያንዳንዱ ሰው፣ ይህንን አስተሳሰብ አንግቦ፣ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው፣ እውነትም ዘመኑን በሥራ ወደ አዲስነት ይለውጣል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፡-
ዓይነተ ብዙ በሆነ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በተፈጥሮ ጸጋ የጎደላት የሌለ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም የበለጠና የተሻለ ሀብት ያላት ሀገር ናት፤ ነገር ግን፣ በሀገራችን ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ተከማችቶ የሚገኘውን ሀብት፣ ጠንክረን በመሥራት ወደ ጥቅም መለወጥ እየቻልን፣ የሌላውን ትርፍራፊ ለመለቃቀም በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ፣ መተኪያ የማናገኝላቸውን ልጆቻችን፣ በየአቅጫው እየተጎዱብን ነው፤ ወጣት ልጆቻችን፣ ለአደጋ በተጋለጠ ሁኔታ፣ በሕገ ወጥ መንገድ፣ ከውድ ሀገራቸው እየወጡ በየአካባቢው ወድቀው እየቀሩ ናቸው፤ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ለማስቆም፣ ሕዝቡ በርትቶ በማስተማርና በመሥራት፣ ልጆቹን ከአሰቃቂ ሕልፈተ ሕይወት ማዳን አለበት፡፡
ሃይማኖታችንና ሀገራችንን የምንወድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በሀገራችን ሥር ሰዶ የቆየውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመቅረፍ፣ በማኅበራዊ ኑሮው የተስተካከለና በኢኮኖሚው የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርቦሽ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀር፣ በስምምነትና በመመካከር መሥራት፣ ተቀዳሚ ዓላማችን ማድረግ አለብን፤ ከሁሉም በላይ፣ የተጀመሩም ሆኑ ለወደፊት የሚጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ ፍጻሜ አግኝተው፣ ሀገራችንን በልማት የመለወጥ ሕልማችንን እውን ሊያደርግ የሚችል፣ ሰላማችን በአስተማማኝ ሁኔታ የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ ብቻ መሆኑን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ለአፍታ እንኳ ሊዘነጋው አይገባም፡፡ በመሆኑም፣ ሁላችንም ኢትዮያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ በአካባቢ ሳንለያይ የዕድገታችን ዋስትና የሆነው ሰላማችንን፣ በንቃት መጠበቅ አለብን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፡-
የሀገር ደኅንነትና ልማት ከሚረጋግጥባቸው አንዱ፣ በአካል፣ በአእምሮና በአስተሳሰብ ጭምር፣ ሙሉ ጤናማ የሆነ ማኅበረ ሰብ ሲኖረን ነው፤ ስለሆነም፣ በሀገራችን፣ በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ጊዜ፣ የጤና ባለሙያ ተገቢ እንክብካቤና እገዛ ባለማግኘት፣ ለሞት አደጋ የሚጋለጡ እናቶችና ሕጻናት፣ በርከት ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህን ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ፣ በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን የእናቶችና የሕጻናት የጤና እንክብካቤ፣ የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሕዝባችን ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል፤ ሕክምና ማለት ጥበብ ማለት ነው፤ ጥበብን ደግሞ አጽንተን እንድንከተላትና እንድንጠቀምባት፣ እግዚአብሔር ያዘዘን በመሆኑ፣ በባለሙያና በሕክምና ጥበብ እየተረዱ፣ በጤና ተቅዋም መውለድ እግዚአብሔር የፈቀደውና የሚወደው ነው፤ በተለይም፣ እናቶቻችን፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው፣ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቅዋማት እየተገኙ፣ በጤና ባለሙያ ድጋፍና ርዳታ በመውለድ፣ ጤንነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በመጨረሻም፣ በአዲሱ ዓመት፣ ሕዝባችን ሁሉ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ኑሮው የበለፀገ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የተካነ፣ ጤንነቱና ሰላሙ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ፣ በተሠማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመሥራት፣ ሀገሩን ያለማ ዘንድ፣ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ይባርክልን ይቀድስልን አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2006 ዓ.ም
ባሕረ ሐሳቡን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ(ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ)
{flike}{plusone}