ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳን
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
- በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ
- ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ
- የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ
- በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ
- የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የተወደዳችኹ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ምእመናንና ምእመናት ልጆቻችን÷ እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለ፳፻፭ ዓ.ም. የቅድስት ድንግል ማርያም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኹ!!
‹‹ወኵሉ ዘሰአልክሙ በስምየ እገብር ለክሙ››፤ ‹‹በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለኹ›› ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ /ዮሐ.፲፬÷፲፫/
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለተከታዮቹ ከሰጠን ስጦታዎች አንዱ የምንሻውን ኹሉ በስሙ እየለመን ጥያቄአችንን የማስፈጸሙ ጸጋ ነው፡፡ እርሱን በስሙ እየለመን የምንሻውን ሁሉ ማግኘት እንደምንችል ቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ ደጋግሞ ያስረዳል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል በተረዱትና በተማሩት ትምህርት መሠረት ይህን ጸጋ ወዲያውኑ በሥራ አውለውታል፤ የለመኑትንም አግኝተውበታል፡፡
እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍቅር ስለኾነ፣ እኛ ሰዎች ፍቅር ኾነን፣ ፍቅርን መርሕ በማድረግ ስንለምነው መልሱ ይኹንታ እንደኾነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ኾኖ ቅድስት ድንግል ማርያምን በእናትነት ለቅዱሳን ሐዋርያት መስጠቱ የእናት ፍቅርና ክብር ከምንም በላይ መኾኑን ለማስረዳት እንደኾነ እንገነዘባለን፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ጌታችን ባዘዘውና ባስተማረው ትምህርት መሠረት የድንግል ማርያምና የሐዋርያት ፍቅር በልጅነትና በእናትነት ደረጃ ዘልቆአል፡፡ ሐዋርያዊት የኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከጌታችን ከሐዋርያት የተቀበለችውን የቅድስት ድንግል ማርያም እናትነትና ክብር ጠብቃ በተግባር እየፈጸመች ትገኛለች፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ በመጀመሪያ ቅዱስ ሥጋዋ ያለበትን ኹናቴ ለማወቅ፣ በሁለተኛ ትንሣኤዋንና ዕርገትዋን ለማየት ባደረባቸው የፍቅርና የአክብሮት ጉጉት ፈጣሪያቸውን በጾምና በሱባኤ ለምነው የልመናቸው መልስ በጥያቄአቸው መሠረት ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ማየት ኾኖአል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ትልቁ ቁም ነገር እንደ ጌታ ቃል በፍቅርና በሰላም ኾነን የምንለምነውን ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አዎንታዊ መልስ የምናገኝበት መኾኑን ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አምስት ቀን ለሁለት ሱባዔ በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት የምትፈጽመው አምልኮተ እግዚአብሔር ይህን መሠረት ያደረገ ነው፡፡
የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼና ወገኖቼ ምእመናንና ምእመናት
ጾማችንና ጸሎታችን ከእግዚአብሔር ፊት ደርሶ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ፍጹም ይቅርታና በረከት ሊያስገኝ የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የጾምን እንደኾነ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው ጾም በሕገ ቤተ ክርስቲያን ከተከለከሉ መባልዕትና መጠጦች መከልከል ብቻ ሳይኾን÷ ለተበደለና ለተገፋ ፍትሕን መስጠት፣ ለተራበ ቆርሶ ማጉረስ፣ ለታረዘ ቀዶ ማልበስ፣ የተጣላውን ማስታረቅ፣ የተሳሳተውን መክሮና አስተምሮ መመለስ፣ በአጠቃላይ በማኅበረ ሰቡ መካከል ፍጹም ሰላምና ፍቅር፣ እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲሰፍን ማድረግና የመሳሰሉት ሁሉ የጾም ወቅት ተግባራት ናቸው፡፡ በተለይም ስለ ሰላምና ፍቅር ስናስብ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ከዚያም እስከ ዓለም አቀፍ ያለውን ሰላም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ፣ ቀደም ብለው ካለፉት ዘመናት አሁን ያለንበት ዘመን የተሻለና ብሩህ ተስፋ የሚታይበት ቢኾንም፣ አሁንም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ቁልፍና ሀገራዊ ተግባር እንዳለ ሳናስገነዝብ አናልፍም፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ የኾነ ሁሉ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይከፋፍለው ለዘመናት የቆየውን ተፈቃቅሮ፣ ተከባብሮ በሰላምና በአንድነት የመኖር ጸጋችንንና ባህላችንን እንደ ዐይን ብሌን በመጠበቅ ወደ ጀመርነው የልማትና የዕድገት አጀንዳችን ብቻ እንድንመለከት ነው፡፡
ይህም እውን እንዲኾን የክርስቶስ ተከታይና የድንግል ማርያም ወዳጅ የኾነ ሁሉ አሁን በምንጀምረው ሱባዔ ፈጣሪውን ከልብ መለመን አለበት፡፡ በዚህ ዐይነት የምናቀርበው ጾምና ጸሎት የመጨረሻው ግቡ ፍቅርና ሰላም ስለኾነ ከእግዚአብሔር የምናገኘው መልስ ይኹንታ እንደኾነ በመገንዘብ ሁላችንም በሃይማኖት በመጽናትና ፍቅርን ገንዘብ በማድረግ መጾምና መጸለይ ይገባናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጾሙን የሰላምና የፍቅር ጾም ያድርግልን፡፡ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.
{flike}{plusone}