ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምሥራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ
የብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምሥራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልዕክት
አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል፡፡ 1ኛ ቆሮ 15.20
ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ለክብርና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንዲኖር የተፈጠረው የሰው ልጅ በአዳምና በሔዋን የእግ/ርን ትዕዛዝ መጣስ የተነሳ ከሕይወት ወደ ሞት፣ ከክብር ወደ ውርደት ወርደው የሞት ሞት ተፈርዶባቸው 5500 ዘመን በፍዳ በመከራ ኑረዋል፡፡ ሞትም የሰው ልጆችን እንዲገዛ ስልጣን ተሰጥቶት 5ሺ ዘመን ከዘለቀ በኋላ በደጋግ ነቢያቱ ፀሎት እና ልመና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም በመወለድ 33 ዓመት ከ3 ወር በምድር ላይ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አይሁድ በምቀኝነት ተነሳስተው በመወንጀል ለስቅለት እንዲበቃ አድርገውታል፡፡
የማይስማማውም አካል ለክፉ ነገር ይስማማልና ክርስቶስን ለመግደል የማይስማሙ ጥል የነበሩት ፈሪሳዊያንና ሳዱቃዊያን ጴላጦስና ሄሮድስ ተስማምተዋል፡፡ ክርስቶስም ሲሰቀል የእርሱ ተከታዮች እጅግ ደነገጡ፡፡ ጠላቶቹም የማይነሳ መስሎአቸው ደስ አላቸው፡፡ ከላይ በጠቀስነው በቆሮንቶስ መልዕክት 1ኛ ምዕ 15 ላይ ሞት ዓለምን እንዲገዛ በሁሉም ላይ ስልጣን ተሰጥቶት ነበር ይላል፡፡ እስከ ክርስቶስም ድረስ በሁሉም ላይ በስልጣን ገዝቷል፡፡
የኋለኛው ጠላት የሚሻር ሞት ነውና፡፡ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛ፡፡ ገዥ እንዲሆን ከሾመው በቀር ሁሉም ተገዥ ሆኖለታል፡፡ ነገር ግን ይህን ገዥ ለመሻር ለማሸነፍ ገዥ እንዲሆን ያደረገው ራሱ ለዚህ ሞት ተገዝቶ አሸንፎታል፡፡ ለዚህ ነው ክርስቲያን የትንሣኤን በዓል በተለየ ሁኔታ የሚያከብረው ክርስቶስ እንደሞተ ቀርቶ ቢሆን ኑሮ አይሁድ ቀና ብለው በማሳፈር የት አለ አምላካችሁ ያሸነፈው ይሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሙታን በመነሳቱ የድል ቀን አድርጎታል፡፡ መጽሐፍም በመዝሙር 77፣ 65 ላይ እግ/ር ከእንቅልፉ እንደሚቃ ተነሣ ይላል፣ ክርስቶስም ከሙታን በመነሳቱ ጨለማ የነበረው ዓለም ብርሀን ሆኖአል ሮሜ 6. 5 ፡፡
የተወደዳችሁ ልጆቻችን ማንም ሰው ሰዎችን በመደገፍ የሰዎችን ደግነት በጎነት ሊመሰከር ሊናገር ይችላል፡፡ ነገር ግን እናትም ብትሆን ስለ ልጂ ራሷ ለመሞት ፈቃደኛ አትሆንም፡፡ ያውም ለደግ ልጂ ፡፡ ክርስቶስ ግን ደግ ሆነን በመገኘታችን ሳይሆን ሊሞትልን ለማይገባው ለእኛ ወንጀለኞች ለሆን በሕይወት ለማኖር የራሱን ሕይወት አሳልፎ ሰጥቶልናል፡፡ ሮሜ 5፣ በትንቢተ ሆሴዕ ምዕ 6 እንደተጠቀሰውም በአዳም ኃጤያት ምክንያት ራሱ እንደሰበረን ራሱ ጠግኖናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፡፡ በሦስተኛውም ቀን ያስነሳል በፊቱም በሕይወት እንኖራለን በማለት ስለ ትንሣኤውና ስለሕይወታችን እንደተናገረው ሁሉ እኛ በትንሣኤው ሕይወት አግኝተናል፡፡ እርሱም ለትንሣኤው በኩር ሆኖ እንደተነሳ እኛም እንነሳለን፡፡
ለዚሁም ደግሞ በትንሣኤው ልናምን ይገባል፡፡ በትንሣኤው አምነን ስናከብር ደግሞ እርሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠልን፣ ትህትናን እና ራስን ዝቅ ማድረግን እንዳስተማረን እኛም ትህትናን ገንዘብ በማድረግ በጎ በማድረግ ለሥጋ ወደሙ በመቅረብ፣ አቅም የሌላቸውን በመርዳት፣ አብሮአችሁ እንዲፈስኩ እንድታደርጉ እያልኩ በዓሉ የሰላም የብልፅግና እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንንም ይባርክ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ፡፡
ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
በዓቢይ ኃይል ወስልጣን
አሠሮ ለሰይጣን
አግዓዞ ለአዳም ሰላም
እምይእዜሰ ኮነ ፍስሃ ወሰላም
{flike}{plusone}