ራሱን ቅዱስ ሲኖዶስ ብሎ የሚጠራው አካል ያወጣውን የሐሰት መግለጫ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

‹‹ኢያስሕቱክሙ አኃዊነ ፍቅራን፤ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ›› ያዕ. 1፡16

ስሕተት በባህርዩ ጎጂና በማናቸውም ጊዜ የማይደገፍ ቢሆንም ከሰው ጋር አብሮ የሚኖር በመሆኑ ሰው ከስሕተት ጸድቶ አያውቅም፤ ስሕተትም ከሰው ጠፍቶ አያውቅም፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ለሰው የሚያስተላልፈው ቋሚ ምክር ሰው ስሕተትን እንዳይፈጽም ነው፣ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ስሕተት ከፈጸመ ደግሞ በንሥሐ እንዲመለስ ነው፣ ቅዱስ መጽሐፍ ስሕተት እንዳይፈጸም አጥብቆ ከማስተማሩም በተጨማሪ ስሕተትን በንሥሐ ማሰረዝ የሚያስችል ጸጋ አለው፣ ሰዎች በዚህ ጸጋ እየተጠቀሙ ራሳቸውን ያስተካክላሉ እግዚአብሔርንም ያስደስታሉ፡፡

ሰው በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ፍጹም ተወቃሽ የሚሆነው ስሕተትን በመፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ስሕተቱን አምኖ በመቀበል በንሥሐ ለመታረም ዝግጁ ባለመሆኑ ነው፡፡

በክርስቶስ ደም የተመሠረተችና በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ የምትጠበቅ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በሃይማኖቷ በትምህርቷና በሥርዓቷ እንከን የለሽ ቤተ ክርስቲያን ለመሆኗ ዓለም የሚመሰክረው ሐቅ ነው፣ ይሁንና በውስጧ የሚገኙ አገልጋዮች ሰው እንደመሆናቸው መጠን አልፎ አልፎ ስሕተት አይፈጽሙም ማለት አይቻልም፡፡

ከዚህ አንጻር ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት በቤተክርስቲያናችን ከፍተኛ ባለሥልጣን የተፈጸመውን ቀኖናዊ ስሕተት የዚህ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን የፈጸሙ አባት፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡198 ላይ ‹‹ወአይደልዎ ለኤጲስ ቆጶስ ከመ ያውድቅ ርእሶ እም ሐራተ ንጉሥ ወይሠየም በምንትኒ እምግብራተ ንጉሥ ወለእመ እጥብዐ ውስተ ዝንቱ ይትፈለጥ እመዓርጊሁ እስመ እግዚእነ ይቤ ኢይክል አሐዱ ገብር ከመ ይትቀነይ ለክልኤ አጋእዝት ወእመ አኮሰ ያምዕዖ ለአሐዱ ወያሠምሮ ለካልኡ›» ፓትርያርክ ራሱን ከክርስቶስ አገልጋይነት ሌላ ለንጉሥ ከሚሠሩ ሥራዎች በማናቸውም ስፍራ መሾም አይገባውም፤ በዚህ ቢገኝ ከሹመቱ ይሻር፣ ጌታችን ‹‹አንድ አገልጋይ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻለውም፣ አለዚያ ግን አንዱን ያሳዝናል፣ ሌላውንም ደስ ያሰኛል ብሎአልና»፡፡ (ማቴ 6፡24) ተብሎ በቅዱስ ወንጌልና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለውን የዚህን ዓለም ሹመት ከመንፈሳዊው ሹመት ጋር በማዳበል እየሠሩ የጣሱት ቀኖና ሳያንስ ‹‹ወለእመ ተራድኦ በመኳንንተ ዝንቱ ዓለም ወተሠይመ ለቤተ ክርስቲያን እመኀቤሆሙ ይትመተር ወይሰደድ ውእቱኒ ወኩሎሙ እለ ተሳተፍዎ፣ ማለትም የቤተ ክርስቲያን መሪ በዚህ ዓለም ገዥዎች ጉልበት ለቤተክርስቲያን ቢሾም ይሻር እርሱና ግብረ አበሮቹ ሁሉ ይለዩ›› ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡175 የሚለውን ሌላ ቀኖና በድጋሚ በመጣስ የገዥዎችን ኃይል ተጠቅመው ሲኖዶሱን ተጭነውና መንፈስ ቅዱስን ተጋፍተው የፓትርያርክነቱን ሥልጣን ጨበጡ፡፡

በይቀጥላልም ለእግዚአብሔርና ለእውነት ከመታዘዝ ይልቅ ላስመረጣቸውና ለቆሙለት ምድራዊ ባለሥልጣን በማድላት፣ የተዛባ አሠራርን በመከተል፣ እውነትነት የሌለው መልእክትን በማስተላለፍ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለነቀፋ ዳረጉ፣ ሕዝቡንም ቅር አሰኙ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸሙ እነኚህ ስሕተቶች በቀኖናው ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ከሥልጣን የሚያሽሩ ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ድርጊታቸው ቅሬታ ያደረበት ሕዝብ እግዚአብሔር ብሶቱን እንዲገልጽ የፈቀደለት ቀን ሲደርስ ቅሬታውን እየገለጸ በሁሉም አቅጣጫ ተቃውሞውን አስተጋባ፡፡

ዐራተኛው ፓትርያርክ የነበሩት አባት ከሕዝቡ ይቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎች በርግጥ የተፈጸሙ ስለመሆናቸው ኅሊናቸው የሚያምንባቸው ነበሩና ሊያስተባብሉአቸው አልቻሉም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ነሐሴ 18 ቀን 1983 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስን ሰብስበው ሕመም ካደረብኝ ብዙ ጊዜ ቆይቶአል ስለሆነም የቤተ ክርስቲያን ሥራ እንዳይበደል ቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነቱን ተረክቦ እንዲሠራ በማለት በራሳቸው ጥያቄ ሥልጣናቸውን አስረከቡ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን ደረጃ በደረጃ ካጠና በኋላ ቀኖናው የሚጠይቀውን ሁሉ ጠብቆ እርሳቸውን ከሥልጣን አስነሣ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዐራተኛው የቀድሞ ፓትርያርክ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ፓትርያርክ አይደሉም፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ አሠራሩ በእርሳቸው ምክንያት የተፈጸመውን ቀኖናዊ ስሕተት በማስተካከል እርሳቸውን በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ ሲወስን፣ ቀኖናው ያዘዘውን ድንጋጌ ፈጸመ እንጂ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አላፈረሰም፣ ቤተ ክርስቲያናችንም ሁለት ፓትርያርኮች እንዲኖሩአት አላደረገም፣ ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ዐራተኛውን የቀድሞ ፓትርያርክ በሕጋዊ መንገድና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መርህ መሠረት ከሥልጣን ካስነሣበት ቀን ጀምሮ በሕግ ፊት ፓትርያርክ አይደሉምና ነው፡፡

አንድ ፓትርያርክ ለመሻር የሚያበቃ ቀኖናዊ ጥፋት ከተገኘበት መሻር እንዳለበት የሚከተለው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያስገድዳል፡፡ ‹‹ወለእመኒ ኢረከቡ ላዕለ ቀዳማዊ ኤጲስ ቆጶስ ዘይደሉ ለመቲሮቱ ለይንበር በመካኑ ወእመሰ ረከቡ በላዕሌሁ ለይሢሙ በመካነ ዘአሁ ዘአልቦ ነውር ውስቴቱ ወለዝንቱስ ያውግዝዎ፤ በፊተኛው ፓትርያርክ ላይ የሚያሽር ጥፋት ካላገኙበት በቦታው ይቀመጥ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለውን ጥፋት ፈጽሞ ቢያገኙት ግን እርሱን ሽረው ጥፋት የሌለበትን ሌላ ይሹሙ›› ይላል ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡17ዐ

ቅዱስ ሲኖዶስ ዐራተኛው የቀድሞ ፓትርያርክ ባቀረቡት ጥያቄና በዚህ ቀኖና መሠረት እርሳቸውን አንስቶ ሌላ ፓትርያርክን ሾመ እንጂ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ አልሾመም፣ሁለት ፓትርያርክ እየተባለ የሚነገረው አነጋገርም ሕጋዊነት የሌለው ፍጹም የስሕተት አባባል ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ውሳኔ ባስተላለፈበት ጊዜ ዛሬ በአሜሪካ ያሉት አባቶችም ባሉበት በተስማሙበትና በፈረሙበት ሁኔታ የተፈጸመ ሆኖ ሳለ ዛሬ ያ የፈረሙበት ሰነድ በቤተ ክርስቲያን ውሰጥ ተቀምጦ እያለ እውነትነት የሌለው ሌላ ታሪክን ለመተረክ ሲሞክሩ መሰማታቸው እጅግ ከፍተኛ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እምቀዳሚታ ተዓኪ ደኃሪታ፣ ከፊተኛይቱ ይልቅ የኋለኛይቱ ትከፋለች›› (ማቴ 12፡45) ብሎ እንዳስተማረን ፊት በተፈጸመው ስሕተት ተፀፅተው ቤተ ክርስቲያን ለመካስ በመዘጋጀት ፈንታ አሁንም ሌላ የባሰ ስሕተት ለመፈጸም ያለሀገሩና ያለመንበሩ ሲኖዶስን አቋቁሚአለሁ በማለት

1. የሰሜን አሜሪካ አባቶች ራሳቸው ስሕተት ፈጽመው ሌላውን ለማሳሳት እያደረጉት ያለውን ቀኖናዊ ስሕተት አቁመው የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ፣

2. መላው ሕዝበ ክርስቲያን በተለይም በውጭ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ከሚገልጽበት የአንድነት መንፈስ ዝንፍ ሳይል ከቤተ ክርስቲያኑ የሚተላለፍለትን መመሪያ እየተቀበለ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንዲቆም

3. ስሕተቱ ማን ጋር እንዳለ አውቆ ለመምከርም ሆነ የኅሊና ዳኝነትን ለመስጠት እንዲሁም በእነርሱ አፍራሽ የሐሰት ቅስቀሳ ግራ እንዳይጋባና እንዳይሳሳት እውነተኛ መረጃ ይደርሰው ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ በቀድሞ ዐራተኛው ፓትርያርክና ከርሳቸው ጋር ባሉት አባቶች የተፈጸመው ስሕተት ሁሉ በጽሑፍ በሚድያና በልዩ ልዩ ጉባኤያት ለሕዝቡ እንዲደርስ የሚደረግ ስለሆነ ሁሉም እየተከታተለ ለቤተ ክርስቲያኑ ሉዓላዊ አንድነት ዘብ እንዲቆም፤ በእነርሱ ላይም ሰላሙን እንዲቀበሉ የማያቋርጥ ተፅዕኖ እንዲያደርግ

4. ሕጉና ቀኖናውን ተከትሎ እየተከናወነ የሚገኘው የስድሰተኛው ፓትርያርክ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ይፈጸም ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ እስከአሁን ድረስ እያሳየ ያለውን የላቀ ተሳትፎና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል

5. የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮ በሀገር ውስጥና በዓለም ዙርያ ለማስፋፋት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ከግቡ ለማድረሰ የሁሉም ሕዝበ ከርስቲያን ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ ስለሆነ ሕዝቡ እንደ ካሁኑ በፊት የተለመደው ድጋፋን አጠናክሮ እንዲቀጥል

6. በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባቶች እየተከተሉት ያለው ሃይማኖትን የማይወክል ፖለቲካዊ አስተሳሰብን አውልቀው በመጣል በሃይማኖት አጀንዳ ብቻ ለመሥራት ፈቃደኞች ከሆኑ አሁንም ቤተ ክርስቲያናችን እጅዋን ዘርግታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን ሁሉም እንዲገነዘብ

7. ስሕተት የሚስተካከለው ስሕተተኛውን በመከተል ሳይሆን ስሕተተኛውን በማረምና ወደሚበጀው ነገር ለመመለሰ ጠንክሮ በመሥራት መሆኑን ግንዛቤ ተወስዶ የባህር ማዶ አባቶች የሀገርንና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከግምት ሳያስገቡ የበለጠ ስሕተት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተሳስተው እንዳያስቷችሁ በስሕተታቸውም እንዳትተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን በአጽንኦት ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊው ቀኖናን መሠረት አድርጎ ጊዜውን የዋጀ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመቅረጽና በማጽደቅ፣ መዋቅሩን በማጠናከርና አገልግቱን ዓለም አቀፋዊ ቅርፅ በማስያዝ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾምና ሕዝበ ክርስቲያንን በመከፋፈል ቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ይቅር የማይሉትን ታላቅ ስሕተት ፈጸሙ፡፡

‹‹የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ›› እንደሚባለው የፈጸሙት ቀኖናዊ ስሕተት ከባድና ተደጋጋሚ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ነገሩን በሰላም መፍታት ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ በማመንና ቀኖናውን በቀኖና በማሻሻል ለእርሳቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልቶ በክብር እንደሚይዛቸው ከእርሳቸው ጋር ያሉት ሿሚዎችና ተሿሚዎች አባቶችም ተቀብሎ በሥራ እንደሚመድብ 6ኛውን ፓትርያርክ በመምረጥና በመመረጥ ሂደትም አብረው እንዲሠሩ በሙሉ ልብ ቢጋብዝም መልሱ አይሆንም ሆኖአል፡፡

ይህም ድርጊታቸው አንድነትን የሚፈልጉ ሳይሆኑ ባይሳካላቸውም በውስጣዊ ኅሊናቸውና ከበስተጀርባቸው ባለ ሌላ አካል በስመ ሃይማኖትና በስመ ቀኖና ለመፈጸም የሚመኙት ሌላ ሕልም እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ተገንዝቦአል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ አንድነቱን በእጅጉ ቢናፍቀውም በአሁኑ ጊዜ ሰሚ አለማግኘቱን ሲረዳ ስድስተኛውን ፓትርያርክ አስመርጦ ሥራውን ለመቀጠል በመወሰን መደበኛ ሥራውን ቀጥሎአል፡፡

የተወደዳችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ምእመናንና ምእመናት

የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድነት ማየት እንደምትናፍቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ይገነዘባል፣ ይሁን እንጂ የምንመኘው መልካም ነገር ሁሉ ስለተመኘነው ብቻ የሚገኝ ሳይሆን እውነቱንና ሊሆን የሚችለውን ተከትለን በምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት ብቻ መልካም ምኞታችንን ማሳካት እንደምንችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የሚፈለገውን የአባቶች አንድነት ማረጋገጥ የሚቻለውን ሌላ የጥፋት ጎጆ ለመቀለስ የሰሜን አሜሪካ አባቶች የሚያስተላልፋትን አፍራሽ ቅስቀሳ በማሰላሰል ሳይሆን በሀገሩና በመንበሩ ያለውን፣ ዓለም ከእርሱ ጋር እየሠራ ያለውን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ተከትሎ በጥበብ በማስረዳትና በመውቀስም ጭምር የሚሳሳቱትን በመመለስ ነው፣ ስለሆነም ይህንን እውን ለማድረግ በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ምእመናን ሁሉ የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት በመፈጸም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ክብርና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና መጠበቅና መስፋፋት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንክሮ እንደሚሠራ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ላላችሁ ምእመናን ሁሉ መግለጽ ይወዳል፡፡

እግዚአብሔር ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ

የካቲት 13 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ