በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ጋር የትውውቅ መርሃ ግብር ተካሄደ
በመ/ር ዘሩ እና ኃይሉ
ክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ስብሰባውን ሲመሩ
ታኅሣሥ 26/005 ዓ.ም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠዋቱ 3.00 ሰዓት ጀምሮ መርሃ ግብሩ የተካሄደ ሲሆን በትውውቅ መርሀ ግብሩ ላይ ክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የክፍል ሃላፊዎቹና ሠራተኞች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፤የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የደብር ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞች ሰባኪያነ ወንጌልና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፍ ሃላፊዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ስብሰባው በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የመግቢያ ንግግር በኩቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የተደረገ ሲሆን በንግግራቸው ላይ ሁሉም ነገር የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ አንድም ነገር ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ነገር የለም፤ ለዚሁም ነው ዛሬ የእግዚብሔር ፈቃድ ሆኖ እናንተን አባቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼን ለማገልገልና እንደወጣትነቴ ላይ ታች ብዬ ለመታዘዝ እዚሁ ቦታ ላይ ለመታዘዝና ለማገልገል የመጣሁት ብለዋል፡፡ ስለሆነም እናንተ የምታዙኝን በአግባቡ፣ በሰዓቱና በወቅቱ ህጉን ተከትዬ ከሠራሁና ከፈፀምኩ እናንተም ሀገረ ስብከቱን የሚያዛችሁና በስሥራችሁ የምታስተዳድሯቸው ሰራተኞች ሥራውን በህጉና በመመሪያው ከሰራችሁና ካሰራችሁ ከአሁን በፊት የነበረውን የሀገረ ስብከቱ የአሠራር ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡
በመቀጠልም በ5ት ዋና ዋና ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መመሪያ ሰጥዋል፡፡
- በመስተንግዶ ዙሪያ ጉዳይ
- በሥራ እቅድ ዙሪያ ላይ
- በመልካም አስተዳደር ዙሪያ
- በስብከተ ወንጌል ዙሪያ
- በደሞወዝና የጥምቅት በዓል አከበባር ዙሪያ
- በመስተንግዶ ዙሪያ በተመለከተ፡- በሀገረ ስብከቱ እንደ ከአሁን ቀድም በር ላይ ተሰልፎ መዋል አይኖርም፤ ማንኛውም የገዳማትና አድባራት ሥራም ይሁን የሠራተኞች የግል ጉዳይ የሚፈልጉትን ነገር ግልጽ በሆነ ደብዳቤ ገልጸው ካመጡ አንዳችም የሚዘገኝበት ጉዳይ አይኖርም ሊያስኬድ በሚችለው ሁሉ በህጉና በሥራዓቱ ሁሉም ሰራተኞች በእኩል ጥያቄዎቻቸው እንዲስተናገዱ ይደረጋል፡፡ ይሁንና ግን የተመደቡበትን መደበኛ ሥራ እየተው ያለ አግባብ እና በቂ ምክንያት ሀገረ ስብከቱን እየመጡ ማጨናነቅ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡ ይልቁንም የገዳማትና አድባራት ሠራተኞችና ምዕመናን የተሟላ አገልግሎት ልትሰጡዋቸው ይገባል ምክንያቱም ጽ/ቤቱን ዘግታችሁ ስትመጡ ብዙ ባለ ጉዳይ ይጉላል አሁን ያለንበት ዘመን ደግሞ አይደለም ብዙ ሰው አንድም ሰው በምንም ተአምር ሊጉላላ አይገባም በመሆኑም ሀገረ ስብከቱ እናንተን አያጉላላም እናንተም ሰራተኞችና ምዕመናን ማጉላላት የለባችሁም በማለት መመሪያ ሰጥተዋል፡
- በሥራ እቅድ ዙሪያ ላይ በተመለተ፡-ሀገረ ስብከቱም ሆነ ገዳማቱና አድባራቱ በእቅድ እና በእቅድ ብቻ መመራት እና መሥራት አለባቸው ምክንያቱም በእቅድ የማይመራ መስሪያ ቤት ኮንፖስ እንደሌለው አውሮፕላን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከየት ተነስተን የት መድረስ እንዳለብን የምንሰራቸው ማናቸውም ሥራዎች ልማታዊም ሆኑ ማህበራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ በበጀት ዓመቱ አቅደን በሚመለከታቸው የበላይ አካላት ተተችቶና ተገምግሞ ከጸደቀ በኋላ በእቅዱ መሠረት መጓዝ በጣም ቀላል ነው ምክንያቱን ሲገልፁ በእያንዳንዱ ወር ምን መስራት እንዳለብን ዝርዝር እቅዱን እያየን በቀላሉ መስራት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ከእቅዳችን ተነስተን መስራት ከነበረብን ምን መስራት እንዳልቻል እና መስራት ከነበረብን ምን የተሻለ ስራ እንደሰራን መገምገም ይቻላል፡፡ በዚሁም በቀላሉ ጠንካራና ደካማ ጐናችንን ማወቅ እንችላለን ስለሆነም በእቅድ ስንመራ ጠንካራ ጐናችንን አጠንክረን ደካማ ጐናችን ደግሞ አርመንና አስተካክለን በቀጣይ ወር የተሻለ ስራ ለመስራት ያስችለናል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በእቅድ፤ በሰዓትና በጊዜ ልንመራ ይገባል ብለዋል፡፡
- ስለመልካም አስተዳደር በተመለከተ፡- ቤተ ክርስቲያኒቷ የመልካም አስተዳደር ፣ የህግ ፣ የቋንቋና፣ የካላንደር ባለቤት መሆኗን ገልጸው ነገር ግን ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በተለይም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሥራው ታሪክ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም ፍትህ በእኩል ያለ አድሎ ለሁሉም መስጠት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሃይማኖታዊ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን የሀገረ ስብከቱና ገዳሙቱ መልካም አስተዳዳር ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሲነጻጸር ለመናገር የሚከብድ ነገር መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ስለዚህ መልካም አስተዳደር ከስም የዘለለ በሀገረ ስብከቱም ሆነ ሀገረ ስብከቱ በሚመራቸው ገዳማትና አድባራት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም መድረክ ላይ የምንሰብከውና በተግባር የምንሰራው ስራ ሁሉ አንድ መሆን አለበት ሃይማኖታዊ ግዴታችንም ጭምር ነው፤ በተግባር ያልተፈተነ ሃይማኖት ደግሞ ሃይማኖት ሊሆን እንደማይችል ለሁላችሁም ግልጽ ነው ከዚህም የተነሳ ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ አድባራቱ በየሶስት ወር በሀገረ ስብከቱ እየተገኙ ሀገረ ስብከቱን እንዲገመግሙ ይደረጋል፤ እንዲሁም ሀገረ ስብከቱ አድባራቱ ድረስ ወርዶ የስራ ሀላፊዎችን በሰራተኞች ያስገመግማል ይህም አሰራሩ ጥሩ ያደርገዋል ሁላችንም ተጠባብቀን እንድንሰራ ያደርገናል ብለዋል፡፡ከዙሁ ጋር በተያያዘ ቴክኖሎጀው ባመጣው መሳሪያ በመጠቀም አሠራራችን የተሻለ ዘመናዊ መድረግና ለተገልጋዬ ማህበረ ሰብ የተሟላ አግልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርን መስፈን እንችላለን ለዚሁም 4ቱም አህጉረ ስብከት ለአሥራር ያመች ዘንድ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ዌብ ሳይት በሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን ይህ ደግሞ በቀላሉ ከሁም ጋር ለመገናኘትና አስፈላጊና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን በዚሁ ዌብ ሳይት በመልቀቅና ምልክቶቻችሁም በኢ-ሜል፤በፋክስና በስልክ በመቀበል ፈጣን እና ዘመኑ የሚፈቅደውን ሥራ መሥራት እንችላለን ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡የአቅም ግንባታ ሥልጠናም አስፈላጊ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋር ለሁሉም የስራ መስኮች በተዋረድ ወቅታዊ ስልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑንም ገልፀዋል፡
- ስለ ስብከተ ወንጌል አስመልክቶም የቤተክርስቲያኒቷ ትልቁ አገልግሎት ስብከተ ወንጌል ማስፋፋት መሆኑን ገልጸው ትክክለኛ ሰው በትክክለኛ ቦታ ላይ ሊቀመጥ ይገባል ምክንያቱም በዚህ ቦታ ላይ ተመድበመው የሚሰሩ ሰዎች ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅቸዋል፡፡ በተለይም የስብከተ ወንጌል ሀላፊዎችና አስተዳዳሪዎች የስብከተ ወንጌሉን መድረክ ሊያስከብሩት ይገባል ለዚህ የሚመደበው በጀትም ከሁሉም የተሻለ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህ የስራ ዘርፍ ሥራው የሚያተኩረው ሰው በማዳን ሥራ ስለሆነ ነው በለዋል፤ ሰው ለማዳን ደግሞ ከሁሉም የተሻለ በጀት መመደብ አግባብ ነው፡፡ በመሆኑም ደብሩ ጥሩ በጀት ሊመድብ ይገባል፤ ሁሉም ሰባኪያነ ወንጌል ደግሞ ለህዝቡ ጥሩ አርያ መሆን ይገባቸዋል በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡
- የደሞወዝ ጭማሪን በተመለከተ፡-ምንም እንኳን የደሞወዝ ጭማሪው ከተየቀ የቆየ ቢሆንም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ4 በመከፈሉ ምክንያት ቢዘገይም በአገልግሎት ተሰማርተው ምዕመናን የሚያገለግሉ አገልጋዮች አቅም በፈቀደና ህጉ በሚፈቅደው መልኩ ወቅቱን ጠብቆ ደሞወዝ ጭማሪ ማግኘት መብታቸው ስለሆነ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ተነጋግረው ውሳኔ ስላስተላለፉ በቅረብ ጊዜ እንደሚለቀቅ አስታውቀዋል፡፡ በመቀጠል ከተሰብሳቢዎች መካከል መልአከ ብርሃን ክብሩ ገ/ጻዲቅ የዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ አስተዳዳሪ፣ ወ/ሮ አሰፋች ተስፋዬ የገነተ ኢየሱስ ም/ሰበካ ጉባኤ፣ መጋቤ ሥርዓት ልዑል ሰገድ ተ/ብርሃ የመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዋና ፀሀፊ፣ መጋቢ ሀዲስ ገብረማርያ እሸቴ የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የስብከተ ወንጌል ኃላፊ እና ብዙ የስብሰባው ታዳሚዎች ክቡር መላአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመመደባቸው እጅግ መደሰታቸውን ገለጽው በወጣው መርሃ ግብር መሠረት መስተናገዱ ለእኛ እጅግ ትልቅ ክብር በመሆኑ እጅግ በጣም ደስ ብሎና ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሰሜኑ ክፍል ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ገለጽው የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በመዲናይቱ ዋና ከተማ በቤተ መንግስቱ፣ በመንበረ ፓትሪያሪኩ፣ በፖርላማውና በዩንቨርስቲው መሃል የሚገኝና አገራዊና አሁጉራዊ ፤መንፈሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚከናወኑት በዚሁ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመሆኑ በጣም ደስ ብሎል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመሆን በልማቱና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል በመጨረሻም የተደረገውን ነገር ሁሉ በማመስገን በቀጣይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስብሰባ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆም ለሁሉም የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞች፤ለገዳማትና አድባራት መኅበረ ካህናትና ልዬ ልዬ ሠራተኞች መልካም የገና እና የጥምቀት በዓል እንዲሆንላቸው በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስም መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ የዕለቱን መርሃ ግብር በፀሎት ተዘግቷል፡፡