ትምህርተ ሃይማኖት

በሊቀ ካህናት ኃይለሥላሴ ዓለማየሁ

ወልድ ዋሕድ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት መሠረታዊ እምነት «ተዋሕዶ» ነው። ተዋሕዶን የሚተረጉም ኃይለ ቃልም ፣ «ወልድ ዋሕድ» የሚለው ነው።

ወልድ ዋሕድ ለሚለው ሥያሜ መሠረቱ «ቃል ሥጋ ኮነ» የሚለው ቃለ ወንጌል ነው። ዮሐ ፩፥፲፬። ስለሆነም፣ የዚህ ዝግጅት ዐቢይ ርእስ /ዋና ርእስ/ ወልድ ዋሕድ እንዲባል ተመርጦአል።
በዚህ ዝግጅት የሚቀርቡ ንኡሳን አርእስተ ትምህርት በየርእሳቸው እየታተቱ የሚቀርቡ ሆኖ ጥናቱ በማስረጃ የተደገፈ እንዲሆን ለማድረግ አዘጋጁ ተገቢውን ጥረት ያደርጋል። ለወጣቱ ግንዛቤ ይሰጣል ተብሎ የሚታመንበት ዝግጅት እንዲሆንም በቀላል አገላለጽ ለማቅረብ ይሞክራል። የትምህርተ ሃይማኖት ምሥጢራዊ ይዘት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከአበው ሊቃውንት የትርጉም ዘይቤ እየተገናዘበ ይቀርባል።

የዝግጁቱ ዋና ዓላማ፣ ወጣቶች የትምህርተ ሃይማኖት ግንዛቤያቸውን እንዲያሰፉ ማድርግ በመሆኑ፣ የቤተክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት ሊያዛቡ ከሚችሉ አዳዲስ አስተሳሰቦችና የግል አስተያየቶች ፍጹም ነፃ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ሆኖ እንዲቀርብ ተገቢው ጥንቃቄ ይደረጋል። ከአንባቢያን ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ አስፈላጊው ትኩረት እየተሰጣቸው ተገቢውን መልስ እንዲያገኙ ማድረግ የአዘጋጁ ተቀዳሚ ተግባርና ግዴታ ነው። ይህን ዝግጅት የሚከታተሉ አንባብያንም እያንዳንዱን ኃይለ ቃል፣ በማስተዋል መከታተል፣ ምሥጢሩንና ቁም ነገሩንም በጥንቃቄ መቅሰም ይጠበቅባቸዋል። ጥበብና ማስተዋል የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር ጥበቡንና ማስተዋሉን ይስጠን። ከእግዚአብሔር አጋዥነትና ረድኤት ውጪ ምንም ምን የሚሆን ነገር ስለሌለ፣ በተለይም ባሕረ ጥበባት የሆነውን ትምህርተ መለኮት ለማቅረብ መሞከር፣ ውቅያኖስን በእንቊላል ቅርፊት… ማለት በመሆኑ፣ የጥበባት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቡንና ማስተዋሉን እንዲሰጠን እንለምነዋለን።

ትምህርተ ሃይማኖት መለኮታዊ ምሥጢርን የሚያስረዳ እንደመሆኑ ትምህርቱ ጥልቅ፣ ረቂቅና ምጡቅ ነው። ይሁንና በዚህ ዝግጅት ግን እንደ ትምህርቱ ጥልቀትና ምጥቀት ሳይሆን፣ እንደ አዘጋጁ የዕውቀት ውሱንነትና እንደ ተቀባዩ የአእምሮ ስፋት መጠን፣ ግልጽ በሆነ አቀራረብ ባጭር ባጭሩ ይቀርባል።

የሃይማኖት ትርጉም 

ሃይማኖት ምንድን ነው?

ሃይማኖት ወይም እምነት ማለት ማመን፤ መታመን፤ የፈጣሪን ሕልውና ማወቅ፤ ከሃሊነቱን፣ መግቦቱንና ቸርነቱን መረዳት፤ መለኮታዊ እውነታዎችን በትክክል መቀበል፤ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥራ ፈጽሞ አለመጠራጠር፤ ጥርጥርን ከኅሊና ማስወገድ፤ ስለ ሰማያዊ ሕይወት ጽኑ ተስፋ ማድረግ በሚሉ አገላለጾች ይተረጐማል።

ሃይማኖት በረቂቅ ሐሳብ፣ በልብ ሰሌዳነት፣ የሚጻፍ የአእምሮ መጽሔት ነው። ሃይማኖት የኅሊና መሰላል በመሆኑ የዓለምን አስቸጋሪ ዳገት ይወጡበታል። ሃይማኖት የሕይወት መርከብ በመሆኑ ገፊውን ማዕበል ተቋቁመው ባሕሩን ይሻገሩበታል። ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙበታል። ዕብ ፲፩፥፮። ልክና መጠን፣ ወሰንና ዳርቻ የሌለው መለኮታዊ ባሕርይ የሚታየው፣ ሕልውናው ከሃሊነቱና መግቦቱ የሚታወቀው በሃይማኖት ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ የሃይማኖትን ኃይል ሲተረጉም፦ «እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው።» ይልና በመቀጠልም «ነአምር ከመ ተፈጥረ ዓለም በቃለ እግዚአብሔር። ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ እናውቃለን።» ብሎአል። ዕብ ፲፩፥፩-፫። ሃይማኖት ፍጡርን ከፈጣሪው ጋር የሚያገናኝ የኅሊና መሰላል በመሆኑ ፍጡር የሃይማኖት መሰላሉና ድልድዩ ከተሰበረበት ወደ ፈጣሪው መድረስ ይሳነዋል፤ ሌላ መድረሻ ሌላ መንገድ ፈጽሞ የለውም።

የሃይማኖት ኃይል ልዩና ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኘው፣ ምድራዊ ባለሥልጣን የማይገዛውን የሚገዛ፣ በዓይነ ሥጋ የማይታየውን የሚያሳይ፣ በእጅ የማይዳሰሰውን የሚዳስስ፣ በሥጋዊ ጥበብ የማይመረመረውን የሚመረምር ምሥጢር መሆኑ ነው። ማቴ ፲፮፥፲፯።

ልዕልና ነፍስ /የነፍስ ልዕልና/ ክብረ ነፍስ የሚገኘው በሃይማኖት ነው፤ ከሃይማኖት ውጪ የሚሆነው ሁሉ ኃጢአትና በደል ነው። «ወኲሉ ዘይከውን ዘእንበለ አሚን ኃጢአት ወጌጋይ ውእቱ። በእምነት ያልሆነ ሁሉ ኃጢአትም፣ በደልም ነው።» ሮሜ ፲፬፥፳፫። የሚታይና የማይታይ፣ ግዙፍና ረቂቅ፣ ሁሉ ከማይታይ እንደሆነ ማለትም በመለኮታዊ ሥልጣን የተገኘ መሆኑን ያሳውቃል።

እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ መገኘት ምክንያት ሳይሻለት በከሃሊነቱ እምሀበአልቦ ፈጥሮታል። ይህን ማወቅ የሚያስችል ከሃይማኖት ውጪ ሌላ ጥበብ ፈጽሞ የለም። የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሽ የመሆን ዕድል የሚያገኘው በሃይማኖት ብቻ ነው። በዓለም ያለውን ሥርዓት በቀላሉ በምሳሌነት ማየት ይቻላል፤ ይኸውም የአንድን ሰው ሃብትና ንብረት ለመውረስ በቀላሉ ባለመብት መሆን የሚቻለው የባለጸጋው ወይም የባለሀብቱ ልጅ ሆኖ መገኘት ሲቻል ነው። በእግዚአብሔር መንግሥትም በሃይማኖት ልጅነትን ካላገኙ የመንግሥቱ ወራሽ መሆን አይቻልም።

«እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።» እንዳለ ጌታ በቅዱስ ወንጌል። ዮሐ ፫፥፭።

«… ስለዚህ ከእንግዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም። ልጅም ከሆንክ ደግሞ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።» ገላ ፬፥፬-፯።
ሃይማኖት በአማኙ ዘንድ ሦስት ነገሮች ተሟልተው እንዲገኙ ግድ ይላል። እነዚህም፦

፩. ትክክለኛ አረዳድ /እውነት/
፪. የልብ ንጽሕና /ቅንነት/
፫. መጥዎተ ርእስ፣ ማለትም ጥብዓት፣ ራስን መካድ፣ ራስን አሳልፎ ለሃይማኖት መገዛት ፈቃደ ሥጋን አሸንፎ መስቀልን መሸከም የሚሉ ናቸው። እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ያልተሟሉለት አማኝ ግብዝ ሃይማኖተኛ ይባላል።

ማስረጃ

«… እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ። አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል። …» ያዕ ፪፥፲፬-፳፪። ማር ፭፥፯። ጌታም በቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይለናል። «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።» ማቴ ፯፥፳፩።

«ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ። መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።» ማር ፰፥፴፬። ሉቃ ፱፥፳፫። ማቴ ፲፥፴፰፣ ፲፮፥፳፬።

«ወኅሊናሁሰ ለነፍስትነ ሞተ ያመጽእ ላእሌነ፤ ወሕሊናሁሰ ለመንፈስ ሰላመ ወሕይወተ ይሁብነ። የሥጋችን ፈቃድ ሞትን ያመጣብናል /ያስፈርድብናል/ የነፍሳችን ፈቃዱ ግን ሰላምን ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን ድኅነትን ይሰጠናል። እስመ ኅሊናሁ ለነፍስትነ ፀሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ። የሥጋችን ፈቃዱ የእግዚአብሔር ጠላቱ ነውና ሞትን ያመጣብናል።» ሮሜ ፰፥፭-፰።
የሃይማኖት ዓላማውና ግቡ፣ ሀልዎተ እግዚአብሔርን ማሳወቅና ፍጡር በፈጣሪው ሕግና ትእዛዝ እየተመራ ዘለዓለማዊ ክብር እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ማቴ ፳፭፥፴፬።

ሀልዎተ እግዚአብሔርን ማወቅ ማለትም ቅድመ ዓለም የነበረ፣ በማዕከለ ዓለም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ ፈጣሪ፣ መጋቢ ሠራዒ፣ በመለኮታዊ ባሕርዩ ጸንቶ የሚኖር፣ ለመንግሥቱ ሽረት፣ ለሕልውናው ኅልፈት የሌለበት አንድ ፈጣሪ፣ አንድ አምላክ መኖሩን አውቆ ማመን ማለት ነው።

«እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላክህ እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው።» ዘዳ ፭፥፬።

የማይታይና የማይመረመር፣ የማይገሰስና የማይዳሰስ፣ ሕያወ ባሕርይ እግዚአብሔር በከሃሊነቱ ሁሉን የፈጠረ፣ በመግቦቱ ሁሉን የሚያስተዳድር፣ በቸርነቱ ሁሉን የሚጠብቅ አምላክ በመሆኑ ለፍጥረቱ የሚታወቅበት ገጽታ አንዱ ይኸው ነው። ሁሉን የሚገዛ፣ ሁሉን የሚያስተዳድር በመሆኑ ይቅርታውና መግቦቱ በሁሉም ላይ ነው።

«እስመ ቅንየትከ ወምልክናከ ላዕለ ኲሉ፣ ይሬስየከ ትሣሃል ላዕለ ኲሉ። ማለት በሁሉ ላይ ያለ ሥልጣንህና አገዛዝህ ሁሉን ይቅር እንድትል ያደርግሃል።» እንዲል።

«… እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።» ማቴ ፭፥፵፭።

በከሃሊነቱ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር የማይታይ፣ የማይመረመርና የማይዳሰስ፣ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ባሕርዩ ከሚገለጽባቸው አያሌ መገለጫዎች ጥቂቶቹን በምሳሌነት መመልከት ይቻላል። እነሱም፦

፩. ፈጣሪ
፪. ከሃሊ
፫. ምሉእ
፬. ዘለዓለማዊ
፭. ቅዱስ
፮. ፍጹም
፯. ማእምር /አዋቂ/ ጥበበኛ የሚሉ ናቸው። እነዚህን በዝርዝር እንመለከታለን።

እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው

ፈጣሪ ስንል የሌለን ወይም ያልነበረን ነገር በሥልጣኑና በከሃሊነቱ ያስገኘ፣ ዓለምን እምሀበአልቦ /ካለመኖር ወደ መኖር/ የፈጠረ ማለታችን ነው። ዓለምን እምሀበአልቦ ያስገኘ፣ በመለኮታዊ  ሥልጣኑ የሚታየውንና የማይታየውን፣ ግዙፉንና ረቂቁን ፍጥረት ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነው።

እግዚአብሔር ዓለምን /ፍጥረቱን/ ለመፍጠር ምክንያት የሆነው መለኮታዊ ሥልጣኑ ብቻ ነው፤ የፍጥረታት ሁሉ አስገኝ እግዚአብሔር በመሆኑም የፍጥረታት ሁሉ ጌታና ባለቤት እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ እንዲሁ አልተወውም፤ በመግቦቱ ይጠብቀዋል፤ ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑና በመለኮታዊ ሥልጣኑ መሳይ ተወዳዳሪ ስለሌለውም እግዚአብሔር አንድ አምላክ ይባላል።
 
እግዚአብሔር ዓለሙን ሲፈጥር፣ ይሁን ብሎ በቃሉ፣ በመለኮታዊ ሥልጣኑና በከሃሊነቱ ፈጠረው እንጂ ፍጥረታትን ለማስገኘት ሌላ አፍአዊ ምክንያት አላስፈለገውም። እንደዚህ ያለ መለኮታዊ ሥልጣን በሰማይም በምድርም ስለሌለ፣ እግዚአብሔር ብቻ ፈጣሪ እንዲባል ያደርገዋል። «ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቊጥር የሚያወጣ እርሱ ነው። ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። በኃይሉ ብዛትና በከሃሊነቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።» ይላል የእግዚአብሔር ቃል። ኢሳ ፵፥፳፮።

በእግዚአብሔር ረቂቅ ሥልጣንና ከሃሊነት የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ ሥርዓት ተሠርቶለት፤ ወሰን ተበጅቶለት ይኖራል። ከተሠራለት ሥርዓት አይወጣም፤ ከተደነገገለት ወሰን አያልፍም። ለይኩን ባለው መለኮታዊ ቃሉ እንደተፈጠረ ሁሉ፣ በመለኮታዊ ትእዛዙ ፀንቶ ይኖራል። መዝ ፴፪፥፬-፱፣ ዮሐ ፩፥፫።

«እነሆ ተራሮችን የሠራ ነፋስንም የፈጠረ፣. . . ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፣ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፣ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።» አሞ ፬፥፲፫። «ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ፤ ያፀናትም፣ መኖሪያ ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ እንዲህ ይላል። . . . ይናገሩ፤ ይቅረቡም፤ በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም፣ የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም። እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒትም ነኝ ከእኔም በቀር ማንም የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ኢሳ ፵፭፥፲፰-፳፪።

በዓለም ታላቁ መጽሐፍ በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፉን የሚጀምርልን የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር መሆኑን በማረጋገጥ ነው። ዘፍ ፩፥፩፣ ዮሐ ፩፥፫፣ መዝ ፴፪፥፮። ሰማይና ምድር ሲባልም፣ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ፣ የሚታየውንና የማይታየውን፣ በሰው ዘንድ የታወቀውንና ገና ያለተደረሰበትን ፍጥረት ሁሉ አጠቃልሎ የያዘ ነው። ለዚህም ሁሉ ፈጣሪውና አስገኚው እግዚአብሔር በመሆኑ ዓለም የእግዚአብሔር ፍጥረት በመባል ይታወቃል። ዮሐ ፩፥፫፣ ቆላ ፩፥፲፮።

ማንኛውም የሥራ ውጤት ያለ ሠራተኛ ሊገኝ እንደማይችል ሁሉ፣ ማንኛውም ፍጡር ያለፈጣሪ አልተገኘም። ምሳሌውን እንመልከት። በባሕር ላይ የሚንሳፈፉ ግዙፋን መርከቦች፣ ከባዱንና ቀላሉን ሸክም ችለው፣ ሕዋውን እየቀዘፉ በሰማይ የሚበሩ አውሮፕላኖች፣ ውስብስቡን የዓለም ምሥጢር በትንሽ አካሉ አከማችቶ የያዘ ኮምፒውተር፣ በአጠቃላይ ዕፁብ ድንቅ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሁሉ የሰው ልጅ አእምሮ ተጨንቆ ተጠብቦ ያስገኛቸው የጥበብ ውጤቶች እንጂ በራሳቸው የተገኙ አይደለም። ታዲያ ከላይ የተጠቀሱ የሰው ልጅ መገልገያዎች በራሳቸው መገኘት የሚችሉ ካልሆነ እነዚህን ያስገኘ ረቂቅ የሰው ልጅ አእምሮ እንዴት ያለ ፈጣሪ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል!!! ፈጽሞ አይታሰብም። ከታሰበም አስተሳሰቡ የስንፍና ውጤት ይሆናል። ለዚሁም ነው፣ «ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል።» ተብሎ የተጻፈው። መዝ ፲፫፥፩፣ ኢሳ ፵፭፥፲፩።

እግዚአብሔር ከሃሊ ነው

ከሃሊ ማለት ሁሉን የሚችል፣ በፍጡር ዘንድ ፈጽሞ የማይቻልን ሁሉ ማድረግ የሚችል፣ ለችሎታው ወሰንና ገደብ የሌለበት፣ ይህን ይችላል ያን ግን አይችልም የማይባል ፍጹም ከሃሊ ማለት ነው። እግዚአብሔር፣ ሁሉም ነገር ከሥልጣኑ በታች በመሆኑ ሁሉም ይቻለዋል።

ይህን አስመልክቶ በዕብራይስጡ ቃል «ኤልሻዳይ» ተብሎ ተሰይሟል፤ ሁሉን የሚችል ማለት ነው። እግዚአብሔር ለአብራም በተገለጠለት ጊዜ፣ ከሃሊነቱን በሚያረጋግጥ ቃል እንደተገለጠለት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስተምረናል። «አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፦ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፤ ፍጹምም ሁን። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ አለው።» ዘፍ ፲፯፥፩።

ፍጹም ከሃሊነት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን በመሆኑ እግዚአብሔር ፍጹም ከሃሊ ይባላል። «በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች።» ዘፍ ፲፰፥፲፬። «. . . ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው። ማቴ ፲፱፥፳፭-፳፮። ሉቃ ፩፥፴፭-፴፰።

እግዚአብሔር በሁሉ ምሉእ ነው

ምሉእ ማለት፣ ፍጹም የሆነ፣ ጉድለት /ሕፀፅ/ የሌለበት፣ በጊዜና በቦታ የማይወሰን፣ መቼም መች የነበረ ያለና የሚኖር ማለት ሆኖ የዚህ ባሕርይ ባለቤትም እግዚአብሔር ብቻ ነው።

እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ልዕልና ያለው አምላክ በመሆኑ ልዕልናውን ለመግለጽ ሲባል በሰማይ ያለ፣ ሰማያዊ አምላክ፣ ሰማያዊ አባት እየተባለ ይጠራል። ማቴ ፮፥፱-፲፣ ፲፰፥፲።

እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ይወስናል እንጂ ሰማይና ምድር እግዚአብሔርን አይወስኑም። ከፍታዎችና ጥልቆች ሁሉ በእግዚአብሔር መዳፍ ናቸው፤

ማስረጃ

«ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ፤ ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ፤ ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ። እንደ ንሥር የንጋትን ክንፍ ብወስድ እስከ ባሕርም መጨረሻ ብበር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፣ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች።» መዝ ፻፴፰፥፯-፲፪።

«እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፤ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።» ኤር ፳፫፥፳፫።

«የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር /ምሥጢር/ ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክን ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ? ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፤ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።» ኢዮ ፲፩፥፯-፱።

«ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፣ ሰማይንም በስንዝር የለካ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን፣ ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማነው?  . . . እነሆ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው። . . . አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው። ከምናምን እንደሚያንሱ እንደ ከንቱ ነገርም ይቈጥራቸዋል። እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? . . .።» ኢሳ ፵፥፲፪-፲፰።

እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ነው

ዘለዓለማዊ የሚለው ቃል ከቋንቋነቱ አኳያ ሲታይ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለመግለጽ ደካማ ወይም አናሳ ቃል ሆኖ የሚታይ ይመስላል። በእርግጥም የቃሉ ገላጭነት የደከመ ወይም የጠበበ ነው። ይሁንና ሌሎች ቃላት ቢሆኑም የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ በፍጹምነት የመግለጽ ብቃት አላቸው ብሎ መገመት አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም።

የሆነ ሆኖ ግን ዘለዓለማዊ ከሚለው ቃል መረዳት የሚቻለው፣ እግዚአብሔር አምላክ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ በማዕከለ ዓለም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ ፍጻሜ /መጨረሻ/ መነሻና መድረሻ የሌለው፣ እርሱ ራሱ መጀመሪያና መጨረሻ፣ የሆነ፣ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ኅልፈትና ሽረት የሌለበት አምላክ መሆኑን ነው።

ማስረጃ

«ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም፥ ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ አንተ ነህ።» መዝ ፹፱፥፪።

«የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፣ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።» ኢሳ ፵፬፥፮።

«ሙሴም አግዚአብሔርን፦ እነሆ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናነተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ ስሙስ ማነው ባሉኝ ጊዜ ምን እላቸዋለሁ? አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን ያለና የሚኖር እኔ ነኝ አለው።» ዘጸ ፫፥፲፫።
 
«ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።» ዮሐ ራእ ፩፥፰።

እግዚአብሔር ቅዱስ ነው

ቅዱስ ማለት ልዩ፣ ንጹሕ፣ ጽሩይ፣ ከክፉ ነገር ከረከሰ ነገር ሁሉ የተለየ ማለት ነው። እንደዚህ ያለ ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሌላው ፍጥረት ቅዱስ ቢባል ቅድስና ከእግዚአብሔር ስለሚሰጠው ነው። እግዚአብሔር ግን ከሌላ የሚያገኘው፣ የሚጨመርለት ወይም የሚቀነስበት አንድም ነገር ፈጽሞ የለም።

ፍጡርንና ፈጣሪን በአንድ ዓይነት አገላለጽ «ቅዱስ» እያልን ስንጠራ የቋንቋ እጥረት ሊሆን ይችላል እንጂ ባሕርየ ፈጣሪ ከባሕርየ ፍጡር ፈጽሞ የተለየ በመሆኑ የእግዚአብሔር ቅድስናም ከፍጡር ቅድስና ልዩ ነው። የተሻለ ስፋት ያላቸው አንዳንድ ቋንቋዎችም በፍጡርና በፈጣሪ መካከል ያለውን የቅድስና ልዩነት ለይተው ይጠቀማሉ።

ባጭር አገላለፅ ባሕርየ ፍጡር /የፍጡር ባሕርይ/፦
•    ጽድቅና ኃጢአት
•    እውነትና ሐሰት
•    ትሕትናና ትዕቢት
•    ክፋትና ደግነት
•    ሕይወትና ሞት
•    ሹመትና ሽረት
•    ፍትሐዊነትና ፍትሕ አልቦነት
•    ርኅራኄና ጭካኔ
•    ፍቅርና ጥላቻ
•    ቁጣና ትዕግሥት ወዘተ… እየተፈራረቁበት ሲወድቅ ሲነሳ የሚኖር ሕይወት ነው። ፍጡር በአብዛኛው ጊዜ በእግዚአብሔር ቸርነትና መግቦት የሚኖር በመሆኑ ቅድስናው የእግዚአብሔር ምሕረት ታክሎበት የሚገኝ ካልሆነ አስቸጋሪ ይሆናል።

«ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድን ነው? እነሆ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም። ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥ ኃጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?» ኢዮ ፲፭፥፲፬-፲፮።

ማስረጃ

«ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ፦ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮህ ነበር።» ኢሳ ፮፥፩-፫።

«እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ እቅዱሳን ሁኑ።» ዘሌ ፲፱፥፩-፪።

«ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።» ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፮።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በቅዱሳን አባቶች በቅዱስ ያሬድና በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አማካይነት ከእግዚአብሔር ባገኘችው ጸጋና በረከት በማሕሌትዋ፣ በሰአታትዋና በቅዳሴዋ እንደ መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር… እያለች ዘወትር ፈጣሪዋን ታመሰግናለች።

ማስረጃ

•    «ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት።»
•    «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉእ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ።»
•    «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ ወይሄሉ እስከ ለዓለም።»
•    «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘይሴባሕ እምትጉሃን ወይትቄደስ እምቅዱሳን።»
•    «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ ዘወትር /ሁልጊዜ/ በሰማይና በምድር ያለ፤ የሚኖር።»

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነቱ የማያቋርጥ ምስጋናዋ ከቅዱሳን መላእክት ተርታ ሊያሰልፋት ችሏል።

እግዚአብሔር ፍጹም ነው

ፍጹምነት የእግዚአብሔር ልዩ የባሕርይ ገንዘብ ነው። ፍጹም ማለትም በሁሉ ዘንድ በሁሉ አቅጣጫ የሚገኝ ሕፀፅ /ጉድለት/ የሌለበት፣ ነውር የማይገኝበት፣ በሁሉም የመላ፣ የተካከለ፤ መሳይ፣ ተመሳሳይ፣ አምሳያ የማይገኝለት፤ ኃያል፣ አሸናፊ፣ መጋቢ ሠራዒ፣ ሁሉን የሚገዛ፣ ወዘተ….. ማለት ነው።

የባሕርይ ፍጹምነት የእግዚአብሔር የግል ገንዘቡ በመሆኑ እንደ እግዚአብሔር ያለ በፍጹምነት የሚገኝ ማንም የለም።

«እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ምስጉን ነው። የአማልክት አምላክ ፍጹም አሸናፊ ነው። የሌለበት ጊዜ የለም፤ የታጣበትም ጊዜ የለም። በመለኮቱ ግን ፈጽሞ የታየበት ጊዜ የለም። እርሱን ማየት የሚችል የለም። አነዋወሩም እንደምን እንደሆነ የሚያውቅ /ማወቅ የሚችል/ የለም።» እንዳሉ ፫፻፲፰ አበው ርቱዓነ ሃይማኖት /ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምእት/።

«አነሆ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም [መርምረን አንደርስበትም]። የዘመኑም ቁጥር አይመረመርም።» ኢዮ ፴፮፥፳፮።

ማእምር

ማእምር ማለት ሁሉን የሚያውቅ፣ ሁሉን የሚረዳ፣ ድርሱን፣ ርግጡን፣ ልኩን የሚያውቅ ወይም ያወቀ ማለት ነው።
 
ዕውቀት ከባሕርይና ከትምህርት ይገኛል። የትምህርት ዕውቀት ማለትም ያልለመዱትን ነገር መልመድ፣ መረዳት፣ መገንዘብ ማለት ነው። ከትምህርት የሚገኝ ዕውቀት ከትንሽ ወደ ትልቅ፣ ግልጽ ከሆነ መነሻና መድረሻ ወደማይገኝለት ወይም ፍጻሜ ወደ ሌለው ውስብስብ ነገር አያደገ፣ እየመጠቀና እየረቀቀ የሚሔድ ልምድ ነው። ሌላው ማወቅ የሚባለው ደግሞ አንድን ነገር ከመሆኑ በፊት፣ በሆነ ጊዜና ከሆነም በኋላ ያለውን ነገር ያመለክታል።

እንዲህ ያለው ዕውቀት ፍጡር ከፈጣሪ በተሰጠው አእምሮ መሠረት የሚያገኘው ክሂሎት /ችሎታ/ ይባላል። ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው የእግዚአብሔር ሰዎችም መጻእያትንና ሐላፊያትን አውቀው ትንቢት ይናገራሉ፣ ያስተምራሉ።

ከባሕርይ የሚገኝ ዕውቀት ደግሞ አስተማሪ፣ መካሪ፣ አዘካሪ ወይም አስታዋሽ ሳያስፈልግ በተፈጥሮ ማለትም በአእምሮ ጠባይዕ የሚገኝ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ጸጋ ነው። በአጠቃላይ ፍጡር የሆነውን ነገር አይቶ ሰምቶ፣ ተምሮ ተመራምሮ ያውቃል፤ ሐላፊያትን መጻእያትንም እንደ ቅዱሳን ነቢያት መንፈስ እግዚአብሔር ገልጾለት /አናግሮት/ ያውቃል ይናገራል ይመሰክራል። ኢሳ. ፯፥፲፬፣ ፱፥፮። የፍጡር ዕውቀት ሁሉም በዓረፍተ ዘመን የተገደበ ነው፤ ገደብ የሌለው የፍጡር ዕውቀት ፈጽሞ የለም። መገኛውም እግዚአብሔር ነው።

የእግዚአብሔር ዕውቀት ከዚህ ሁሉ ፈጽሞ የተለየ ነው። ነገሮች ሁሉ ከመታሰባቸው፣ ፍጥረታት ሁሉ ከመፈጠራቸው፣ መጻእያት ሁሉ ከመድረሳቸው /ከመሆናቸው/፣ ሓላፊያት ሁሉ ካለፉ ከጠፉ በኋላ በሕሊና አምላክ አሉ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ይታወቃሉ። የእግዚአብሔርን ዕውቀት ሊገድብ የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።

ማስረጃ

«ውእቱሰ የአምር ሕሊና ሰብእ እምቅድመ ኵነታ።»

«ልብንና ጥልቅንም መርምሮ ያውቃቸዋል ምክራቸውንም ሁሉ ያውቃል እግዚአብሔር የልቡና አሳብን ሁሉ ያውቃል… ያለፈውንም የሚመጣውን እሱ ይናገራል የተሠወረውንም ምሥጢር ይገልጣል። ከእግዚአብሔር ምክር ሁሉ የሚያመልጥ የለም ከነገሩ ሁሉ አንዲት ቃል ስንኳ የሚሰወረው የለም።» ሲራ ፵፪፥፲፰-፳።

«አቤቱ መረመርኸኝ፥ አውቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሳቴን አወቅህ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥… አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ… እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም።» መዝ ፻፴፰፥፩-፮።

«ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።» ዮሐ ፪፥፳፭፣፮፥፷፬፤ ማቴ ፱፥፬።

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር