የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በግማሽ ዓመት 74 ሚሊየን ብር ከፐርሰንት ገቢ ሰበሰበ

c001
ፎቶ ፋል

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያን ባለፈው ግማሽ ዓመት ብር 74,000,000.00 (ሰባ አራት ሚሊየን ብር) ሰበሰበ፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት በመላው ኢትዮጵያና በውጪ ሀገራት ለሚያደርገው ሐዋርያዊ ተግባር አስፈላጊ የሆነውን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያቀርብ ሀገረ ስብከት ሲሆን የዘንድሮ የፐርሰንት አሰባሰቡ በ2007 ዓ.ም ተመሣሣይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲመዛዘን ከ2 እጥፍ በላይ ልዩነት ያለው ሲሆን ከሦስት ዓመታት በፊት መሰብሰብ የቻለውን የዓመት ገቢ የሚመጣጠን ገቢ በ6 ወራት መሰብሰብ መቻሉ ታውቋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በገንዘብ አያያዝ ላይ በሰጠው መመሪያና በሚያደርገው ቁጥጥር፣ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ድረስ ያሉ ኃላፊዎች የፐርሰንት አሰባሰብን በሚመለከት ያላቸውን ግንዛቤ በማሻሻል ግዴታቸውን እንዲወጡ በተሠራው ሰፊ ሥራ፣ በተለይ የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች ለሥራው ትኩረት ለመስጠት ባደረጉት ያልተቋረጠ ጥረት ውጤቱ ሊመዘገብ መቻሉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ገልጸዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሒሣብ አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የአሠራር ለውጥ ዝግጅቱን አጠናቆ በሒሳብ ሥራ የተሰማሩትን ባለሙያዎች በተለያዩ ዙሮች እያሰለጠነ መሆኑና እስከ አሁን ከ60 በላይ ሒሳብ ሹሞች ሰልጥነው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እጅ የተመረቁ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

{flike}{plusone}