ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

                                              በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

በስመ አብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን

z

 

ከስድስተኛው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ስድስተኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ከተቋቋመበት እና ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እየሰራ ያለውን ስራዎች ለሚዲያ ተቋማት መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም ምርጫው በካህናት እና በምዕመናን ዘንድ ግልፅ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ የካቲት 8 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በሰጠነው መግለጫ እንደገለፅነው የምርጫው ሂደት በወጣው መርሃ ግብር መሰረት በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በምርጫ ህገ ደንቡ በተደነገገው መሰረት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ካህናትና ምዕመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክርስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይሆናል የሚሉትን እንዲጠቀሙ በተላለፈው ጥሪ መሰረት ጥቆማቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከየካቲት 8-14 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጡ ጥቆማዎችን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡

በተደረገው ማጣራትም 2791 ጥቆማዎች ለኮሚቴው ደርሰዋል፡፡ ለፓትርያርክነት የተጠቆሙ ብፁዓን አባቶች ቁጥር 36 ሲሆኑ 15 የጥቆማ ወረቀቶች በአግባቡ ተሞልተው ባለመገኘታቸው ኮሚቴው ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡ ጥቆማዎችን ከማጣራት ጎን ለጎን የአስመራጭ ኮሚቴው ከአምስት ያልበለጡ ከሶስት ያላነሱ ዕጩ ፓትርያርኮችን የካቲት 16 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ለሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለማቅረብ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በተደረገው ውይይትም አሁን በአገልግሎት ላይ ካሉ ብፁዓን አባቶች መካከል 19 ሊቃነ ጳጳሳትን በቀጣይነት ለማጣሪት አሳልፏል፡፡ የተከተለው መመዘኛም ዕድሜና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

በዕድሜ በተደረገው ማጣራት በምርጫ ህገ ደንብ በተደነገገው መሰረት ዕድሜያቸው ከ75 የበለጡተን እና ከ5ዐ ዓመት በታች የሆናቸውን አባቶች ወደ ምርጫ እንዳይገቡ አድርጓል፡፡ ለቀጣይ ማጣራት ከቀረቡት 19 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የምርጫ ህገ ደንቡን መሰረት አድርጎ ከሰፊ ውይይት በኋላ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት መርጧል፡፡ ኮሚቴው ሰፊ ጊዜ በመውሰድ ማጣራት ያደረገው በስምንቱ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ነው፡፡ በተደረገው ማጣራትም አምስት ሊቃነ ጳጳሳት ለይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቧል፡፡

እነርሱም፡-

1. ብፁዕ አቡነ ማትያስ – ዕድሜ 71- በኢየሩሳሌም የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ

2. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ – ዕድሜ 75 የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

3. ብፁዕ አቡነ ዮሴም – ዕድሜ 61 የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

4. ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል – ዕድሜ 59 – የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፣ የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ፣ የከፋ ሽካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

5. ብፁዕ አቡነ አቡነ ማቴዎስ – ዕድሜ 5ዐ – የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ህገ ደንቡን መሰረት አድርጎ ለዕጩ ፓትርያርክ ለቅዱስ ሲኖዶሰ ምልዐተ ጉባኤ ያቀረባቸው ከላይ ስማቸው የተዘረዘሩት ብፁዓን አባቶች የካቲት 16 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቀርበው የምልዐተ ጉባኤውን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም ስድስተኛው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ፓትርያርክ ይሆኑ ዘንድ በነዚህ ብፁዓን አባቶች ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያና የድጅት ኃላፊዎች፣ ከ53 አህጉረ ስብከት የሚወከሉ የካህናት፣ የምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የአድባሪት እና የገዳማት አስተዳዳሪሪዎች በውጭ ሀገር ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የማፀበረ ቅዱሳን ተወካይ፣ ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚወከሉ መራጮች፣ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ከጧቱ 1፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ ምርጫውን ያከናውናሉ፡፡

መራጮችም ከየሚወከሉበት ሀገረ ስብከት እና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ተቋማት በመግባት ላይ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የወደደውን እና የፈቀደውን አባት መንጋውን ይጠብቅና ያሰማራ ዘንደ በመንበሩ እንዲያስቀምጥ ከዛሬ የካቲት 18 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተገኙ ፀሎታቸውን በማድረስ ላይ ናቸው፡፡

መላው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ካህናትና ምዕመናን በዕጩነት ከቀረቡት ብፁዓን አባቶች መካከል ለመንጋው እረኛ እግዚአበሔር አምላክ እነዲሰጠን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ በፆምና በፀሎት ፈጣሪያቸውን እንዲጠይቁ፤ መራጮችም የተወከሉበትን ደብዳቤ እና የመረጡበትን ቃለ ጉባኤ በመያዘ የካቲት 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጧቱ 2፡ዐዐ ሰዓት በመገኘት የመራጮች ምዝገባ እንዲያካሄዱ ምርጫው የወጣውን የምርጫ ህገ ደንብ ተከትሎ መካሄዱን ለመታዘብ የአራቱ እኀት አበያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ የዓለም አበያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ሶስት የመንግስት ተወካዮች እና ሶስት የሀገር ሽማግሌዎች እንዲታዘቡ ደብዳቤ የደረሳቸው በመሆኑ በዕለቱ የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ከጧቱ 12፡ዐዐ ሰዓት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተገኝተው ምርጫውን ይታዘባሉ፡፡

ምርጫው የሚካሄደው በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመሆኑ ሁሉም መራጮች የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ከጧቱ 1፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ በቦታው በመገኘት ምርጫውን እንዲያካሄዱ እየጠየቅን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በሰላም እንዲፈፀም ከዛሬ የካቲት 18 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ጀምሮ ምርጫው እስከሚፈጸምበት የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ቀናት ፈጣሪያቸውን በፆምና በፀሎት እንዲጠይቁ ደጋግመን እናሳስባለን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአበሔር