” እግዚአብሔር የስስትን መንፈስ ከልባችን አስወገደልን” … ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ
የሰሜንና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ባካሄደው መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ነው።
ብፁዕነታቸው በጦርነቱ ወቅት ለአምስት ወራት ገደማ በአህጉረ ስብከታቸው ከምእመናን እና ከሕዝቡ ጋር ስላሳለፉት ሁኔታዎች አስመልክተው ማብራሪያ ለጉባኤው ሰጥተዋል።
በዚያ በችግር ወቅት ምእመኑ እና ሕዝቡ አንዱ ለሌላው ሃይማኖትንና ዘርን ሳይለይ በትክክለኛ የሰብአዊነት ስሜት መድኃኒትን፣ ምግብን፣ አልባሳትን እና ገንዘብን ሲያካፍል መቆየቱን ገልጸዋል።
የቤተክርስቲያን መዋቅር በዚያ በፈተና ወቅት እንደረዳቸውም ጠቅሰዋል፤ በሀገረ ስብከት፣ በወረዳ እና በአጥብያ በካህናት አባቶች በኩል ምእመናኑን በማስተባበር የተለያዩ ድጋፎች እንደተደረጉም ጠቅሰዋል።
እግዚአብሔር የስስትን መንፈስ ከልባችን ስላስወገደልን ያለንን ነገር ሁሉ እየተካፈልን በአንድነት ያንን ክፉ ጊዜ በፍቅር አሳለፍን ሲሉ ተደምጠዋል።
አያይዘውም የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት 15 ሚሊዮን የሚገመት የአልባሳት፣ የአስቤዛ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ከልብ አመስግነዋል።
ዕርዳታውም ብፁዕነታቸው በተገኙበት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በአግባቡ መድረሱንም ለጉባኤው አረጋግጠዋል።
ዕርዳታውን ይዘው በቦታው ለተገኙት የክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች እና ምእመናን በተጨማሪም ለክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በአህጉረ ስብከታቸው በምእመናን እና በሕዝቡ ላይ የደረሰው ሰቆቃ እጅግ በጣም አስከፊ እና አሳሳቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን አብራርተዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።
ትምህርት ቤቶችን ገንብተን ተማሪዎቹን ማስቀጠል የሁላችንንም ዕርዳታ የሚጠይቅና የቤት ሥራችን ነው ብለዋል።
ሁሉም በመተባበር እና ያቅሙን ድጋፍ በማድረግ በኢኮኖሚ እና በስነ ልቦና የተጎዳውን ማኅበረሰብ ልንደርስለት ይገባል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
- ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese