የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ 4ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በታላቅ ድምቀት ተከበረ!!

390

ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት 4ኛ ዓመት በዓለ ሢመት የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባለቤት ወ/ሮ መዓዛ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ አህጉር አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የመንፈሳውያን ኮሌጆች ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገዳማትና አድባራት የሰንበት ተማሪዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በላቀ ድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ መርሐ ግብር ወቅት የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ሊቃውንት፣ የአጫብር ዜማ ምሁራንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች በዓለ ሢመቱን የተመለከተ ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል፤ በመልአከ ብርሃን ፍስሐ ጌታነህ ቅኔያት ቀርበዋል፡፡
በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፤ ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና የምሥራቃዊ ዞን አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዓለ ሢመቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት
…ዛሬ በዚህ ቤተ መቅደስ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓትና ትውፊትን በጠበቀ መልኩ እያከበርነው ያለው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 4ኛ ዓመት በዓለ ሢመት የቤተ ክርስቲያናችን በዓል መሆኑ ግልጽ ነው፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኙ÷ አላዩምም፤ እናንተ የምሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ÷ አልሰሙም” (ሉቃ10÷24) እንዳለ፤ ብዙዎች አባቶቻችን ይህን ክብር ሊያዩ ተመኝተው ዐረፍተ ዘመን ስለገታቸው ለማየት  አልቻሉም፤ እኛ ግን ይህን ለማየት በቅተናል፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ ልጆች የራሷን መንፈሳዊ አስተዳደር መምራት እንድትችል ለማብቃት ብዙ መሥዋዕትነት የከፈሉና ብዙ ጥረት ያደረጉ አባቶቻችን ቅዱሳን ነገሥታት፣ ካህናትና ምእመናን ለዚህ በዓል መሠረት ጥለው አልፈውልናልና ሊታወሱና ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
እነርሱ በጣሉት መሠረት ላይም አሁን ያለነው የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናንም የቤተ ክርስቲያናችን እምነት፣ ታሪክና ሥርዐተ አምልኮት እንዲሁም ሁለንተናዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕድገትና ልማት አስፋፍቶ የመሥራት፣ የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን የሚታየው እድገት ብዙና ከፍተኛ ሲሆን በአንጻሩም ለዚህ ዕድገት ዕንቅፋት የሚፈጥሩ ቢጸሐሳውያን መታየታቸው አልቀረም፡፡ በመሆኑም የእነዚህ ቢጸሐሳውያን የሐሰት ትምህርት ለመግታት ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷን፣ ታሪኳንና ሥርዐተ አምልኮቷን ጠብቃ ወይም አስፋፍታ ህልውናዋን እንድትጠብቅ ካህናት በትምህርተ ወንጌል ምእመናንን በሥነ ምግባርና በጽንዐ ሃይማኖት ማስታጠቅ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም የቤተ ክተርስቲናችን የትምህርት ተቋማት ማለትም መንፈሳውያን ኮሌጆቻችን የሚያሰለጥኗቸውን ካህናት በጥራትና በብቃት እንዲያሰለጥኑ መምህራኑን ማበረታታትና ክትትል ማድረግ ይጠይቃል፡፡
ይህንንም ሁሉ በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ሰላም በዓለም፣ ሰላም በሀገር እንዲሰፍን ቤተ ክርስቲያናችን በነግህና በሠርክ፣ በመዓልትና በሌሊት “ሰላም ለአኀዊነ ወተፋቅሮ ምስለ ሃይማኖት እምኀበ እግዚአብሔር አቡነ ወእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ- ለወንድሞቻችን ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ከሃይማኖት ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ” (ኤፌ.6÷23) በማለት አዘውትራ ታስተምራለች፡፡
ይህም ሰላም የእግአብሔር ቃል የእግዚአብሔር ትእዛዝ ስለሆነ ሁሉም ሊቀበለውና ሊያከብረው ይገባል፡፡ “አፀምዕ ዘይነብበኒ እግዚአብሔር አምላኪየ እስመ ይነብብ ሰላመ ላዕለ ሕዝቡ ላዕለ ጻድቃኑ ወላዕለ እለ ይመይጡ ልቦሙ ኅቤሁ- እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ÷ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና” (መዝ.24÷8)፡፡  በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ሆይ! የሰላም አምላክ እግዚአብሔር እንኳን ለ4ኛው ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላም አደረስዎ በማለት በቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን እንዲሁም በራሴ ስም መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፤ መጪው ጊዜም የተሳካ የአግልግሎት ዘመን እንዲሆንልዎ እመኛለሁ በማለት አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና አባታዊ ትምህርት በዓለ ሢመተ ክህነታችን የግብረ ክህነት አገልግሎታችን፣ የግብረ ኖሎት ጥበቃችን  የስብከተ ወንጌል ተልእኮአችን በንዋየ ቤተ እግዚአብሔር ያለው አያያዛችን ምን ይመስላል? በምን ደረጃስ ይገኛል? የሚለው ቆም ብለን የምናስብበትና የምናስተካክልበት ቀን እንጂ የአንድ ርእሰ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ሢመት የምንተርክበት ቀን ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የእግዚአብሔር በጎች የሆኑ ምእመናን በልዩ ልዩ ምክንያት በባዕዳን እንዳይነጠቁ ከምን ግዜም ነቅተን የምንጠብቅበትና በዚህም ቃል የምንገባበት ዕለት ሊሆን ይገባል፡፡
እኛ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን የተሾምነው በመእመናንና በምእመናት ላይ እንደሆነ አንረሳውም፤ የህልውናችን ዋስትናም ከእግዚአብሔር ቀጥለው እነርሱ መሆናቸውን አንዘነጋውም፤ ሐቁ ይህ እስከሆነ ድረስ እኛ ካህናት ለእግዚአብሔርና ለምእመናን የማንከፍለው መሥዋዕትነት ሊኖር  አይገባም፤ ምእመናንን በተለይም  ሃይማኖት ተረካቢው ወጣቱ ትውልድን እንደ እግዚአብሔር  ቃል ተንከባክበን ካልያዝን የነገ ቀጣይነት ጥያቄ ላይ እንደሚወድቅ ልብ እንበል፤ ምእመናንን የመጠበቅና እግዚአብሔርን የማገልገል ኃላፊነታችን ዘርፈ ብዙ እንደሆነም አንዘንጋው፤ እግዚአብሔር የሥጋም የነፍስም አምላክ እንደመሆኑ መጠን ምእመናን በጎቹም በሥጋቸውም ሆነ በነፍሳቸው እንዲጠበቁ አዟል፤ ለምእመናን ሲል ደሙን ያፈሰሰ አምላክ ምእመናን በሥጋቸውም ሆነ በነፍሳቸው እንዲለሙ እንዲበለጽጉና እንዲያድጉ ይፈልጋል፤ እኛ ሥዩማነ እግዚአብሔር የሆን ካህናት ምእመናንን በሥጋዊ ሕይወታቸው የሰላም ኃይሎችና የልማት አርበኞች ሆነው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲሳድጉ፣ የጥንካሬአቸው ዋስትና አንድነት፣ ፍቅር ወንድማማችነት ብቻ መሆኑን እንዲገነዘቡ፣ መለያየት፣ መቃቃር፣ አለመተማንና ቅራኔ የውደቀትና የድክመት ጉዞ እንደሆነ እንዲረዱ አበክረን ልናስተምርና ልናሳምን ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ምእመናን በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሥጋዊ ልማትን ብቻ እያየ በሥጋዊ ምኞትና ፍላጎት በመሸነፍ (በሴኩላሪዝም)፣ በባህል ወረራና በቅይጥ ሃይማኖት በመባዘን  (በግሎባሌይዜሽን) በስመ ነጻነት ልቅ በሆነ አስተሳሰብ አኗኗር በመዝቀጥ (በሊበራሊዝም) ተጠራርጎ እንዳይጠፋ ቅዱስ ወንጌልን በትክክል ከማስተማር ጋር በቃላችንም ሆነ በሥራችን ምእመናንን የምንስብና የምንወደድ ሥዩማን መሆን ይገባናል፡፡
ይህንን ሁሉ የምናውቅና በሥራ የምንተረጒም ሆነን ስንገኝ እውነትም ጌታ በቤቱ ንብረት ሁሉ ላይ የሾመን ታማኝና ደጋግ አገልጋዮች ነን ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የሚወደን የሚያከብረንና የሚንከባከበን ክርስቲያኑ ሕዝባችን ስለ እግዚብሔር ቃልና ለስራሳችን ስንል ያለምንም እንከን በታማኝነትና በደግነት እንድናስተምር፣ እንድናገለግልና እንድንጠብቅ አደራ ጭምር መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን በማለት የማጠቃለያውን አባታዊ መልእክት በማስተላለፍ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡