ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባለ 4 ነጥብ መግለጫ አወጣ

w00822

                           የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ኅሡ ሰላማ ለብሔር እስመ በሰላመ ዚአሃ ይከውን ሰላምክሙ
(የአገርን ሰላም ሹ ፈልጉ የአገራችሁ ሰላም የእናንተ ሰላም ነውና)
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት !
የሐገርና የወገን ፍቅር ያለው ሕዝብ ሰላም ከእግዚአብሔር መሆኑን ያውቃል፣ ሰላም ለሰው ልጆች ከማናቸውም መሠረታውያን ፍላጎቶች በላይ ተቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ተቻችለውና ተረዳድተው የሚኖሩባት የዓለም ምሳሌ ናት፡፡ ይህን ዓለምን የሚያስደንቅ ገጽታችንን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲከተለው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት !
ኢትዮጵያ አህጉረ ሰላም (የሰላም ሐገሮች) ከሚባሉት ከዓለም ሀገሮች አንዷ ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት ሁሉንም የሚያሳስብ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ከዚህም ጋር ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሰተው ያልተጠበቀ ችግር፡-
1.በአንዳንድ አካባቢ የሰው ሕይወት ሲጠፋ፣ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ የንግድ ተቋማት፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት፣ የእምነት ተቋማት ሲወድም የሕዝባችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ሲናጋ ሁሉም ኀብረተሰብ የችግሩ ተጠቂ ሆኗል፣ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት በዚህ ሁኔታ የሕዝባችን ሕልውና የትውልዱም የወደፊት ዕድል አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡
2.ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሰተው ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች በመሪር ሐዘንና ጸሎት እናስባቸዋለን፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም ልጆቻችን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳትሉ ችግራችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው እንድታቀርቡ መንግሥትም የሕዝቡን ችግር እና ሰላማዊ ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሔ በመስጠትና ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን የዕለት ከዕለት ጥረት እንዲቀጥልበት በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናሳስባለን፡፡
3.ሕዝባችንና ሐገራችን በረሃብ፣ በድኅነትና በበሽታ ቸነፈር በተቸገረበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መሠረታዊ ወደሆነው ልማት የሰላምና የድርቅ ጉዳይ በማተኮር መልስ ሰጭ መሆን ይገባዋል ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡
4.ወገኖቻችን ሆይ በአሁኑ ጊዜ የወቅቱ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ (ብሎጐችና የፌይስ ቡክ) ተጠቃሚዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ከሙያችሁ ከእውቀታችሁ ተጠቃሚዎች የመሆን ምኞታቸው የላቀ ነው፡፡ ሆኖም መልካሙንና ለእድገት የሚያግዛቸውን ዕውቀት እንጂ ኅብረተሰቡን የሚለያይና የሚያራርቅ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) ዕለት ዕለት ብታስነብቡት ትርፉ መራራቅን እንጂ መቀራረብን፣ መለያየትን እንጂ መግባባትን አያመጣም፣ ከዚህ አንጻር የእናንተም ጥረትና ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡
በመሆኑም የተከበረ እውቀታችሁን ሙያችሁን ለሕዝባችን ፍቅርና አንድነት፣ ለሀገራችን ሰላምና ዕድገት እንድታውሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ትጠይቃለች፡፡
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን
ተቻችሎና ተረዳድቶ የመኖር የተቀደሰ ነባር ባሕላችንን የሚያጎድፍ ማናቸውንም አስተሳሰብና እንቅስቃሴ በአንድነት መቋቋም እንደሚገባ አበክረን እየገለጽን፣ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን በሙሉ በተለይም አገር ተረካቢ ትውልድ የሆናችሁ ወጣቶች ሁከትና ብጥብጥን ከሚያስከትሉ መጥፎ ድርጊቶች እንድትቆጠቡ ለአገር ልማትና ሰላም ጠንክራችሁ እንድትቆሙ በልዑል እግዚአብሔር ስም አጥብቀን እያሳሰብን በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የሀብትና፣ የንብረት ውድመት፣ በተለይም የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የእምነት ተቋማት መቃጠል የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን፡፡
ይልቁንም ከሁሉም በላይ ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን ለኢትዮጵያ ለሀገራችን ሕዝቦች ሰላሙን፣ ፍቅሩን አንድነቱን ይሰጥልን ዘንድ፣ ድርቁን ረሀቡን አስታግሶ መጪው ጊዜ ዝናመ በረከቱን ይሰጠን ዘንድ በያዝነው በዐቢይ ጾም ሱባኤ ጸሎተ ምህላ በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

{flike}{plusone}