39ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ተጀመረ
39ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ጥቅምት 3/2013 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዲስ በተሠራው ጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል።
ጉባኤው እስከ ጥቅምት 7 ቀን እንደሚቀጥልም ተገልጿል።ጉባኤው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በርዕሰ መንበርነት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በምክትል ሰብሳቢነት የሚመራ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ፥ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የመንበረ ፓትርያርክ የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ ኃ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፥ ከየአህጉረ ስብከቱ የተወከሉ ልዑካን ካህናት፣ ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችና በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካን ተወካዮች በተገኙበት ጠቅላላ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ተምሯል።አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አባታዊ ቡራኬና ጸሎት በይፋ እንደተከፈተ ጸሎተ ወንጌል ደርሷል።
በመቀጠልም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለጉባኤተኛው ሰፋ ያለ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
የዘንድሮ መንፈሳዊ ጉባኤያችን በርካታ ወገኖቻችን ሰማዕትነት የተቀበሉበት፣ መከራ፣ ስደትና የንበረት ውድመት በፈጠረው የሕሊና ቁስለት እያሰብን እንዲሁም የሃገራችን ሰላም አንድነትና የሕዝባችንን ደኅንነት እያሰብን መሆን አለበት ብለዋል።
ያለፈው 2012 ዓ/ም በተፈጥሮኣዊና ሰው ሰራሽ፣ እንዲሁም የሰው ልጅ እርስ በርስ በፈጠረው ችግር በርካታ ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወት ማለፍና የንብረት ውድመት የተስተናገደበት ዘመን መሆኑን ገልጸዋል።
በማስከተልም የቤተ ክርስቲያንዋ ታሪክና ማንነት ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው፣ በማይጠፋና በማይደበዝዝ ቀለም የተጻፈ፣ በማይፈርስ ሐውልት ተቀርጾ የተሣለ፣ ማንም የማይለውጠው ሀቅ፣ በቅዱሳን ተጋድሎ የጸና ዘለዓለማዊ መሆኑን በማብራራት ከ2000 ዘመን በላይ የኖረች መሠረቷ በወርቀ ደመ ክርስቶስ የተመሠረተ፣ በልበ ምእመናን የተሣለች፣ በሰማያዊት መንግሥት የተመሰለች፣ አናቅጸ ሲዖል የማያናውጧት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥራ ማዳፈን፣ ታሪኳና ክብሯን ማሳነስም ሆነ መለወጥ ሕልውናዋን መፈታተን ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን በማብራራት ክፋ አድራጊዎች በሰማይም ሆነ በምድር ከተጠያቂነትና ከፍርድ እንደማያመልጡ ገልጸዋል።
ለምእመናንም የቤተ ክርስቲያን ክብርና ልዕልና የሚጎላው በዓመታዊ የአደባባይ በዓላት በዓውደ ምኅረቱ በሚታየው ዑደት ብቻ ሳይሆን በልማት ጎዳና ከፊት በመሰለፍ መሆኑን በመግለጽ ለመንፈሳዊም ሆነ ለማኅበራዊ ልማት ወገባችንን አጥብቀን አርዓያነት ያለው ሥራ ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የማይረሳ ወገናዊ መልካም ሥራ ለሠሩ ወገኖች በማመስገን፣ በቀጣይም በይበልጥ በተጠናከረ፣ መዋቅሩን በጠበቀና በተደራጀ መልኩ ዘላቂ ሥራ እንዲሠራ በመማጸን ሕዝብና አሕዛብ በታረቁባት፣ ሰማይና ምድር በተዛመዱባት፣ የአንድነት ቤታችን በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በአንድ ልብና በአንድ ሀሳብ እየተመካከርን በትጋት በመሥራት ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርኩ አባታዊ መልእክት በመቀጠል የብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አሰኪያጅ አጠቃላይ የ2013 ዓ/ም ሪፖርት ተደምጧል፦ በሪፖርቱ አጠቃላይ የዓመቱ የቤተክርስቲያኒቱ ዋና ዋና ክንውኖች የቀረበ ሲሆን ዓመቱ ፈታኝ እንደነበረ በመግለጽ ለዚህም ደግሞ ጥልቅ የሆነ ውይይት እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል።
65% ለመንበረ ፓትርያርክ ፈሰስ የሚያደርው አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ስራ አስከያጅ በተሰጠው ከፍተኛ አመራርና ክትትል፣ በክፍላተ ከተሞች እና በገዳማትና አድባራቱ ብርቱ ጥረት የዘመኑ ገቢ 327,223,307.58 በማስመዝገብ ከአምና የ93,714,307 ብልጫ ማሳየቱ በጉባኤው ተገልጿል።
ይህም አብዛኛው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የዓመቱ በጀት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደሚሸፈን ያመላክታል ።
ፎቶ ከEOTC Facebook page የተወሰደ