38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሣዊ ጉባኤ ውሳኔ ሐሳብና የአቋም መግለጫ

ታሪክ እንደሚመሰክረው ዘመናዊ ት/ት ባልተስፋፋበት ዘመን እንደ ት/ት ሚኒስቴር ሆና ወጣቱን በጥበብ ሥጋዊና በጥበብ መንፈሳዊ ኮትኩታ በማሳደግ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን መሪነት ያበቃች፣ ሀገርን የሚወር፣ ሃይማኖትን የሚያጠፋ ወራሪ ኃይል በመጣ ጊዜም ታቦትን ይዛ በመዝመት ሕዝቡን በማበረታታት ዳር ድንበርን ያስከበረች፣ የሰላም ምንስቴር ባልተዋቀረቡት ዘመን እንደ ሰላም ምንስቴር ሆና የሀገርን ሰላም ያስጠበቀች የሀገር ባለውለታ የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መከራዋ ተወግዶ ክብሯ እና ልዕልናዋ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በዚህ በ38ኛው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ለቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳዎች ግብዓት የሚሆኑ ባለ 27 ነጥብ የውሳኔ ሀሳቦችና የአቋም መግለጫዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለጉባኤው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርና ባሰሙት ቃለ በረከት ያስተላለፉትን አባታዊ መልእክትና የሥራ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ አቅማችን ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

2. ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደሯን የምትመራበት ቃለ ዓዋዲ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጊዜውንና ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል ቢደረግም አሁንም ሰፊ ክፍተት ያለው በመሆኑ ቃለ ዓዋዲውን ጨምሮ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጐች ደንቦችና መመሪያዎች የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንቦች በባለሙያዎች አስፈላጊው ጥናት እየተደረገ ለመልካም አስተዳደር ምቹ በሆነና ሊያሠራ በሚችል መልኩ በድጋሚ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው እንጠይቃለን፡፡

3. ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የአብነት መምህራን ፍልሰት ለማስቆምና መብታቸውን ለማክበር እስከ አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ ቢሆንም የመምህራኑና የደቀመዛሙርቱ ችግር ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ አንጻር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየጊዜው የሚያደርገው ድጐማ እንደተጠበቀ ሆኖ በአህጉረ ስብከት በኩልም ዐቅም በፈቀደ መጠን አስፈላጊው እንክብካቤና ክትትል ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

4. አስተዳደርን በተመለከተ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር መምሪያና በአህጉረ ስብከት በኩል የተሠራውና በሪፖርት የተገለጸው አበረታች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መልካም አስተዳደርን በማስፈን መርሕ ጊዜውን የዋጀ የተቀላጠፈ ፍትሕና ርትዕ የተሞላው አስተዳደር እንዲኖር ከማድረግ አንጻር የበለጠ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

5. የቤተ ክርስቲያናችን ክብሯ እና ልዕልናዋ በየጊዜው ተጠብቆ እንዲኖር የስብከተ ወንጌል መስፋፋት ወሳኝ በመሆኑ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በማጠናከር በሕትመት ውጤቶችም ሆነ በስብከተ ወንጌል ስምሪት ረገድ የትውልዱን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል እና በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የመገልገል ፍላጎትን በሚያሳካ መልኩ በቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲደራጅ እየጠየቅን ለስብከተ ወንጌሉ መጠናከርም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው የ1% አስተዋጽኦ ሳይሸራረፍ ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ እንዲውል ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

6. የነገይቱን ቤተ ክርስቲያን የሚረከቡና ዛሬም የቤተ ክርስቲያን ውበት የሆኑት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በመንከባከብ በማስተማርና ከጠላት ወረራ እንዲጠበቁ በማድረግ ከአባቶች የተማሩትን ያልተበረዘ ንፁሕ ትምህርት በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ሰንበት ት/ቤቶች ሁሉ ለማስተማር ያሉትን ለማጠናከር ባልተቋቋሙባቸው አብያተ ክርስቲያናትም ለማቋቋም ቃል አንገባለን፡፡ ከዚህም ጋር በማህበረ ቅዱሳን በኩል በየአህጉረ ስብከቱ በሚገኙ ወረዳዎችና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለልማት ሥራ የሚውል የገንዘብና ሙያዊ ድጋፍ መደረጉ ከየሪፖርቶቹ ማዳመጥ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውን ድጋፍ ወደፊትም ማዕከላዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ያሳስባል፡፡

7. የካህናት አስተዳደር መምሪያ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በዓለ ሢመት አከባበር ጀምሮ ዓመታውያን ክብረ በዓላት በድምቀትና በሥርዓት እንዲከበሩ ማድረጉ ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ግርማ ሞገስን የሚያጎናጽፍ ስለሆነ ለወደፊትም እንዲበረታታና ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን፡፡

8. በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ቅርስና ንብረት አጠባበቅ ደንብ መኖሩ ቅርሶች በጥንቃቄ እንዲጠበቁና የቱሪስት መስህብነታው እዲጎለብት እንዲሁም ቤተ መዘክሩ የጥናትና የምርምር ማዕከል ለማድረግ መሠራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንታዊነቷና ዓለም አቀፋዊነቷ አንጻርና በቱሪዝም ዘርፍ በደንብ ቢሠራ ዘርፉ በምጣኔ ሀብት ዕድገት ረገድ ለቤተ ክርስቲያንችን ሊኖረው ከሚችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንፃር ሲታይ ቤተ ክርስቲያን በቅርስና ቱሪዝም ዘርፍ ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ስለሆነም የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በተገቢው መንገድ በበጀትም ሆነ በሙያው በሠለጠነ የሰው ኃይል ተጠናክሮ ቤተ ክርስቲያናችን ውጤታማ የምትሆንበትን ሥራ እንዲያከናውን እያሳሰብን በአህጉረ ስብከትም ደረጃ በዘርፉ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

9. የገንዘብና የንብረት ቁጥጥር መጠናከር ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ምጣኔ ሀብት ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የቁጥጥር መምሪያውን በበቂ ባለሙያዎች በማደራጀት፣አህጉረ ስብከቱም የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ ተአማኒነትና ግልጽነት ያለው የሒሣብና የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ሒደት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

10. ቤተ ክርስቲያናችን በሺዎች የሚቆጠሩ ገዳማት፣ አድባራት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋይ ካህናት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምእመናን ያሏት እንደመሆኑ መጠን በዚሁ ልክ የንዋያተ ቅድሳት አቅርቦት በአብዛኛው የሚያገኙት ከግል ነጋዴዎችና ከእምነቱ ተቃራኒ ድርጅቶችና ግለሰቦች ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁኔታ ከመሠረቱ ለማስተካከልና ቤተ ክርስቲያናችንን ተጠቃሚ ለማድረግ የጐፋ ጥበበ ዕድ ድርጅት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ድርጅቱ በቂ በጀት እና የሰው ኃይል ተመድቦለት በተለያዩ ሃገራት ቅርንጫፎችን ከፍቶ ንዋያተ ቅድሳቶችን በብዛትም ሆነ በጥራት አምርቶ ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ በየቦታው ያለአግባብ በግለሰቦች የሚመረቱት ንዋያተ ቅድሳትን ሁሉ በራሳችን ድርጅት የተገልጋዩን ፍላጎት በሚያረካ ደረጃ በጥራት እንዲያመርት ጉባኤው አሳስቧል፡፡

11. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሕግና ሥርዓት ምንጮች የአስተዳደራዊ ብቃት መገኛዎች የቅርስና ንዋየ ቅድሳት ባለቤቶች የጸሎት የትምህርትና ግብረ-ገብ ማዕከላት መሆናቸው በሚገባ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ሲሆን ነግር ግን በአንዳንድ አህጉረ ስብከቶች ባሉ ታላላቅ ገዳማት ከሕገ ቤተ ክርስቲያንና ገዳማዊ ሥርዓት ውጪ የግል ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ሳይላኩ ተልከናል፤ ሳይሾሙ ተሹመናል፣ሳይበቁ በቅተናል እያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍጠር ምእማናኑን በማወናበድ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ ያሉትን ግለሰቦች አጥብቀን የምንቃወም ሲሆን የገዳማቱን ሕግ ለማስጠበቅ ሲባል ተጠናክረን በጋራ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

12. የአብነት ት/ቤቶች ትምህርት ከዘመናዊው ጋር ተቀናጅቶ ሊሰጥ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሥርዓተ ትምህርት በትምህርትና ማሠልጠኛ ማዕከልነት ቢዘጋጅ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚያበቃ እወቀት የያዙ ሊቃውንትን ማፍራት ስለሚቻል የአብነት ት/ቤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

13. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ህግ አገልግሎት መምሪያ የቤተ ክርስቲያናችንን መብት ለማስከበር እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መንፈሳዊ ፍ/ቤቱም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ባደረገ መልኩ መንፈሳዊ ፍትህ መስጠቱ ለቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለዘርፉ ሕግ ወጥቶና ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ዕውቅና እንዲያገኝ ለዓመታት ተደጋጋሚ ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም ጉዳዩ ፍጻሜ አለማግኘቱን በእጅጉ የሚሳዝን ሲሆን በውስጣዊ አስተዳደር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ ራሳችንን በራሳችን የመዳኘቱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከማድረግ ጎን ለጎን ቤተ ክርስቲያናችን በመንግሥት ዕውቅና ያለው መንፈሳዊ ፍርድ ቤት እንዲኖራት የማድረጉ ጥረት በሕግ አገልግሎት መምረያ በኩል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ያሳስባል፡፡

14. በቤተ ክርስቲያናችን እየተዘጋጁ የሚታተሙ መጻሕፍትና መዝሙራት ሁሉ በጉባኤ ሊቃውንት እየተመረመሩ እንዲታተሙ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ለዚሁ መሠረታዊ ሥራ በብቃት መወጣት እንዲችል ከአሁን በበለጠ እንዲጠናከር ሆኖ የቤተ ክርስቲያኒቱ ነባር መጻሕፍት በሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦች ያለፈቃድ እየተባዙና እየተነገደባቸው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን የራሷን መጻሕፍት በመጠበቅ እያሳተመች ለምእመናን እንድታቀርብ መሰረታዊና ተገቢውን አስተምህሮዋንን በተገቢው መልክ እንድታሠራጭ የበኩላችን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

15. በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እጅግ በበዛበት በዚህ ወቅት አብያተ ክርስቲያናት ከምን ጊዜውም በበለጠ እርስ በርስ መረዳዳትና በተለይም የተቃጠሉት እና የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት በቤተ ክርስቲያናችን መረዳዳት የተለመደ ስለሆነ በውጭው ሀገር ያሉ አብያተ ክርስቲያናትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት፣የሥራ ኃላፊዎች ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ርዳታ ይውል ዘንድ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ከምንግዜውም የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

16. የቅድስት ሥላሴ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስና የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጆች እስከ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሰለጠነ ሰው ኃይል በመጨመርና እና ሰባክያነ ወንጌልን በማፍራት ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ታውቆ በቀጣይም መንፈሳውያን ኮሌጆቹ የቅበላ አቅማቸውን ከፍ አድርገው በደቀ መዛሙርት ምልመላና መማር ማስተማሩ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ተጠናክው እንዲቀጥሉ እያሳሰብን ሰባክያነ ወንጌልን በብዛት፣ በብቃትና በጥራት እንዲያፈሩ ከእኛ የሚጠበቀውን እገዛ ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

17. የአበው ቅርስና የቤተ ክርስቲያናችን ቋሚ ሀብት የሆኑት ሕንጻዎችና ቤቶች አሁንም በቅዱስነታቸውና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጥረት እንዲሁም በጠቅላይ ሚንስትሩ መልካም አመራር ሰጭነት ለቤተ ክርስቲያኒቱ እየተመለሱ በመሆኑ በተገቢ መንገድ ኪራያቸው እየተሰበሰበ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ቤተ ክርስቲያንና፣ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ተጠቃሚነት ለሚደረገው ጥረት እገዛ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

18. የሕጻናትና ቤተሰብ ጉዳዩ ድርጅት ዋና ዓላማው ከቤተሰብና ህብረተሰብ ጋር ለሚኖሩ ሕጻናት የትምህርት፣ የምግብ የአልባሳትና የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ እጓለ-ማውታ ሕጻናትን ተንከባክቦ የማሳደጉ ምግባረ ሠናይ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ድርጅቱ ተናቦ ካለመሥራት የተነሳ ጉዳዩ ከቤተ ክርስቲያናችን አልፎ ወደ ፍርድ ቤት እንዲያመራና ቤተ ክርስቲያኒቱ ይዛ ያቆየችው ሀብትና መሬት በሌሎች አካላት እንዲወሰድባት ክፍተት እየፈጠረ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ብሎ የወሰነውን ውሳኔ አሁንም አሻሽሎና አጠናክሮ ድርጅቱ ከአህጉረ ስብከት ጋር ተስማምቶ የሚሠራበትን አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ፤ ካልሆነ ግን በሕጻናት ማሳደጊያዎች ስም ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት ይዛ ያቆየችው ርስት እንዳትነጠቅና ወላጅ አጥ ሕጻናትም እንዳይበተኑ ሙሉ በሙሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተረክባ የምታስተዳድርበትን ሕግና መመሪያ እንድትቀርጽ እየጠየቅን ለስኬታማነቱም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማደረግ ቃል እንገባል፡፡

19. የቤተ ክርስቲያናችን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ድርጅት ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በየበዓላቱ የወቅታዊና መደበኛ መርሐ-ግብሮች ሥርጭት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች እያካሄደ መሆኑ የሚበረታታ ነው፡፡ ይሁንና በተለይ በበጀት ዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ቃጠሎ፣የምእመናን ስደት እና ሞት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምእመናን በነቂስ ወጥተው ድርጊቱን ያወገዙበትን ሰላማዊ ሰልፎች ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ አለመዘገቡ በጉባኤው ጥያቄና ቅሬታ የፈጠረ ስለሆነ መገናኛ ብዙኃኑ የቤተ ክርስቲያናችን ልሳን ሆኖ የሚያገለግል እንደመሆኑ መጠን የተሸለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ድርጅቱ በበቂ ባለሙያዎች ተደራጅቶና በበጀት ተደግፎ ተደጋጋሚነትን በመቀነስና በአዳዲስ መርሐ-ግብር እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በመዘገብ ደረጃውን የጠበቀ ሚዲያ እንዲሆን ጉባኤው በአጽንኦት ያሳስባል፡፡
20. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገርን፣ ዳር ድንበር ጠብቃና አስጠብቃ ታሪኩን፣ ትውፊቱን፣ ዕውቀቱን፣ ሥነ-ጥበቡን ወ.ዘ.ተ ለዚህ ትውልድ በማስረከብ ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ዳሩ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ የመጡ ፀረ ቤተ ክርስቲያን አቋም ያላቸው ቡድኖች ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌና ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር ውጭ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተኗት ይገኛሉ፡፡
በባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት በአብያተ ክርስቲያናትና በምእመናን ላይ የደረሰው ጥፋት በዕቅድና በዓላማ በጊዜው በነበረው የክልሉ የመንግሥት አመራር የተፈፀመ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ለጠፋባት ንብረት ሁሉ የጥፋቱ ልክ በባለሙያ ተገምቶ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ካሣ ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲከፍል ተጠይቆ ተግባራዊ ሳይሆን ይባስ ብሎም በዚህ ዓመት በተለይ በጅማ፣ በከሚሴ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በድሬዳዋ፣ በሲዳማ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመተከል ወ.ዘ.ተ ግፍና በደሉ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ቤተ ክርስቲያናችን ተቃጥላለች፣ ካህናት በመሠውያው ሥር ታርደዋል፣ ምዕመናን ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሠደዋል፡፡ ስለሆነም በቅዱስ ሲኖዶሱ በኩል ለማዕከላዊ መንግሥት ቀርቦ እየተደረገ ያለው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ በመምጣቱ በቤተ ክርስቲያናችንና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል ለመቀነስና ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ጥፋት ከመድረሱ በፊት በሙያ የተደገፈ ቅድመ ትንተና የሚሰጥና የሚያነቃ ጥፋት ከረሰ በኋላም ለሚመለከተው አካል ሁሉ በወቅቱ የሚያሳውቅ፣ በውስጡ የሕግ ባለሙያዎች ያሉበት እና ጠንካራ የመረጃ ማዕከል ያለው፣ ሰንሰለቱም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚደርስ ዓለም አቀፍ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም እንጠይቃለን፡፡

21. ርዕዮተ ዓለማዊና የሐሰት ታሪኮችን ፈጥረው በመጻሕፍም ሆነ በሚዲያ የያሚሠራጩ ለሀገር ግንባታ፣ለመልካም አስተዳደር፣ ለትምህርት ወ.ዘ.ተ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንነት ትልቅ አሻራ ያሳረፈችውን ታላቋን ቤተ ክርስቲያናችንን ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተገኘን ነን የሚሉ ልዩ ልዩ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው አክቲቪስት ነን ባዮችና ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአሐዳዊ ሥርዓት ናፋቂና የአንድ ብሔር ሃይማኖት እንደሆነች በማስመሰል በሚያራግቡት የሐሰት ወሬ አንዳንድ ምእመናን እንዲደናገሩና ቤተክርስቲያንን እንዲጠራጠሩ መደረጉ አግባብነት ስለሌለውና ተራ ፕሮፓጋንዳ ስለሆነ ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አጥብቆ ይቃወመዋል፡፡

22. ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ጽንፈኞች በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 4 በተደነገገው መሠረት ለዘመናት አርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የነበረውና አሁንም የምትጠቀምበትን ቀስተ ደመና /ባንዲራ/ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፣ ቤተ ክርስቲያን ጣርያና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን ማዋከብና ወጣቶችን ማሰር፣ አልፎ ተርፎም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የቤተ ክርስቲያኒቷን ተቀማጭ ብር ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ ብቻ አስቀምጡ በማለት ለማስገደድ መሞከር፣ ለዘመናት የቆዩ የበዓለ ጥምቀትና የመስቀል አደባባይ ይዞታዎችን ነጥቆ ወይንም ቆርሶ ለሌሎች መስጠትና መሰል የሕገ መንግሥት መሠረት የሌላቸው ጭፍን ተጽእኖዎችን ጉባኤው አጥብቆ እየተቃወመ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስም ትኩረት ሰጥቶ እንዲወያይበት ጉባኤው በታላቅ ትሕትና ይጠይቃል፡፡

23. በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ውጫዊ ችግሮች ሳያንሱ በውስጧ እየታየ ያለው ዘረኝነትና ሙስና በየጊዜው ዓለም አቀፉን ዐቢይ ጉባኤ የሚያነጋገር በመሆኑ ችግሩን መግታት የሚቻለው በየደረጃው ያሉ መሪዎች መንፈሳዊ አመለካከት ኑሯቸው ሁሉንም በእኩል ዓይን ማየት ሲችሉና ጎጥ እና ሀገርን መሠረት በማድረግ ሳይሆን ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ፍትሐዊ ሹመት ወይም የሥራ መደብ ድልድል ማድረግ ሲቻል ነው፡፡
በመሆኑም መልካም አስተዳደር ሰፍኖ አሁን ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚቻለው ግልጽነት እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ መንፈሳዊነትን በማስቀደም በዘመናዊ ቴክናሎጂ የታገዘ የፋይናንስ፣ የንብረትና የሰው ኃይል አስተዳደር ደምብ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል ሲደረግ ሲሆን ለዚሁም ስኬት ሲባል ቀደም ሲል የተጀመሩ የመሪ እቅድ ዝግጅቶችና ሌሎችም ይጠቅማሉ የተባሉ የለውጥ አቅጣጫዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርበው ተፈትሸውና ታርመው ጊዜ ሳይሰጣቸው ወደ አፈጸጸም ሲገባ ብቻ በመሆኑ ጉባኤው አጽንኦት የሰጠው ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት እየጠየቅን ለተፈጻሚነቱም እንደምንሠራ ቃል እንገባለን፡፡

24. ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ዙሪያ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ያሏት ሲሆን በነበረው የአባቶች መለያየት ምክንያት ተከፍሎ የነበረው ሲኖዶስ ወደ አንድነት መጥቶ ሳለ በአሁን ሰዓት በምዕራብ ካናዳ እየታየ ያለውን ሲኖዶስን የመቃወም አካሄድና በሰሜን አሜሪካ በአንድ ግለሰብ ስም የወጣው የቤተ ክርስቲያን ፈቃድ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅረዊ አሠራርን የሚፈታተን ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሔ እንዲሰጠው እያሳሰብን በሀገር ውስጥም ከጀርባ የተለያዩ የተለያየ የፖለቲካ አጀንዳዎችን በመያዝ ለስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ የተቆጩ በማስመሰል ቤተ ክርስቲያናችን አቅሟ በፈቀደ መጠን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ስታስተምር የቆየችና አሁንም መጻሕፍትን በማስተርጐም ስብከተ ወንጌልን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማዳረስ የምታደረገውን ጥረት እያጠለሹ መዋቅሯንና አስተዳደሯን ብሎም አንድነቷን ለመበታተን በማሰብ እራሳቸውን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ብለው በመሰየም እንየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖች ድርጊታቸው ጉባኤውን ያስቆጣ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ በሆደ ሰፊነት ችግሩን በትእግስትና በጥበብ ለመፍታት የሄደበት መንገድ ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እያደነቀና ግለሰቦቹ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰበ ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና መዋቅራዊ አሠራሯ መጠበቅ ተግቶ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል፡፡
25. የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያናችን ዘርፈ ብዙ መንግስታዊ ድጋፍና ተደርጎላት፣ የተወረሱ ሕንፃዎቿ ተመልሰውላት ደስታዋን የገለጸችበት ወቅት ቢሆንም የተደረገላትን ውለታ ተናግራ ሳትጨርስ እየተደረገባት ያለው እኩይ ተግባርና በደል ያንኑ ያህል እያሳዘናትና እያሳሰባት በመሆኑ ጉዳዩ በዝምታ የሚታይ ስላይደለ አቤቱታዋንና ጬኸቷን ለምድራዊው መንግሥት አጠናክራ እያቀረበች መፍትሔ ያልተገኘላቸውን ደግሞ ይግባኝ ለክርስቶስ እያለች ጠባቂዋና ባለቤቷ ወደ ሆነው እግዚአብሔር እጆቿን እንድትዘረጋ ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ ጾምና ምህላ እንዲያውጅ በትሕትና እንጠይቃለን፡፡
26. በአሁኑ ሰዓት እየታየ ያለው የቤተ ክርስቲያን ሀብትን የመቀራመበት አዝማሚያ ወጣቱን በግብረ ገብ ኮትኩቶ ማሳደግ ባለመቻላችን የመጣ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍና በሥ-ምግባር የታነፀ እግዚአብሔርን የሚፈራ ትውልድን ለማፍራት ይቻል ዘንድ አህጉረ ስከት በአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ እየተገነቡ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከገቢ ማስገቢያነት ባለፈ ትውልድን የማነጽ ሥራ በተጠናና በታቀደ መንገድ እንዲሠራ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
27. በየዓመቱ በሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ የቀረቡ የውሳኔ ሐሳቦችና በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰኑ ችግር ፈቺ ውሳኔዎች አፈጻጸም ላይ እክል ሲገጥማቸው ይታያል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በየጊዜው የሚወሰኑ ውሳኔዎች አፈጻጸማቸውን የሚከታተልና በየጊዜ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት በሚያደርግ መፍትሔ የሚያመጣ ዐቢይ ኮሚቴ እንዲዋቀር እንጠይቃለን፡፡
28. በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የመጣውን ሰላም ማጣትና አጋጣሚውን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሽምግልና በዲፕሎማሲ የማረጋጋትና ሰላማችን እንዲመለስ ማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ ዓለም አቀፍ የሆነና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ሕጋዊ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲወሰንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የመጣው ለውለታዋ የማይመጥን በደል በአንዳንድ ፖለቲከኞች ሴራ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ጠንካራ አቋም እንዲይዝ፣ ችግር ፈቺ ውሳኔም እንዲያስተላልፍ እንጠይቃለን፡፡
29. በየዓመቱ የሚደረገው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በየአህጉረ ስብከቱ የታዩ ችግሮችን በሪፖርት የምናደምጥበት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶ በተፈጠሩ ችግሮችና ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ግብአት ጠንካራ ሀሳቦች የሚንሸረሸሩበት መድረክ ማድረግ ይቻል ዘንድ አስቀድመው ወደ ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የተላኩ የየአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ተጨምቀው በመምሪያው ኃላፊ እንዲቀርቡና ለውይይት ሰፊ ጊዜ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ክፉ ዘመን ለማለፍ በጠበቀ አንድነትና ንቃት ዘመኑን የዋጀ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም በሚገኙ አህጉረ ስብከት ሥር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች አገልግሎቷን አቀላጥፋ በማስቀጠልና ውጫዊውም ሆነ ውስጣዊ ተግዳሮቶችን ተቋቁሟ ለማለፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያለባት ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ይመክርበት ዘንድ ጉባኤው በአጽንኦት ይጠይቃል፡፡

ምንጭ፡-(የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት ድርጅት)