36ኛው የኢ/ኦ/ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላም ተጠናቀቀ

230

ከጥቅምት 6/ 2010 እስከ ጥቅምት 9 /2010 ሲካሄድ የሰነበተው  የ36ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለ 21 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ በጉባኤው መጨረሻ ቀን የተከናወኑትን ክንውኖች አስመልክቶ ዘገባው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ማንኛውንም ሥራ ከመስራት አስቀድሞ መጸለይ መጽሓፍ ቅዱሳዊ መርህ ስለሆነና እግዚአብሔር የሚለመንበት መንገድ በመሆኑ በዕለቱ ከሁሉም አስቀድሞ ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል፤ ከዚህ በመቀጠልም ሰው ከእግዚአብሔር  አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ  በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ በወንጌል እንደተጻፈው ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ለጉባኤው ታዳሚዎች የሕይወት እንጀራና የነብስ ስንቅ የሆነውን ትምህርተ ወንጌል  አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ዕለት የጉባኤው መጨረሻ ቀን እንደመሆኑ መጠን በጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ  ከመጀመሪያው  የጉባኤ ቀን አንስቶ ቃለ ጉባኤ እንዲይዙ በታዘዙት የቃለ ጉባኤ አርቃቂ ኮሚቴዎች አማካኝነት የሶስቱን ቀናት ሪፖርት፤ ውይይትና ምክክር አስመልክቶ ጥልቅና አስደማሚ  እንዲሁም ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ችግሮችን በዳሰሰ  መልኩ በመጋቤ ካህናት ኃ/ስላሴ ዘማርያም ተወካይነት ለጉባኤው ታዳሚዎች ባለ 21 ነጥብ የጋራ አቋምና ውሳኔ ተነቧል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቀረበው የጋራ አቋምና ውሳኔ ጥሩ ነው ቢሉም በጉባኤው ያልተካተተ  ሐሳብ አለው ይህ ደግሞ እንደጋራ መግለጫ ሊቀርብ አይገባም ስላሉ  ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በሲኖዶስ የጸደቀውን  ጨምረው ጻፉ እንጂ  የራሳቸው ሃሳብና ልበ-ወለድ ኣይደለም ሲሉ የአቋም መግለጫውን በማጽደቃቸው የታዳሚውን ልብና የቤተክርስቲያንን ሉዓላዊ ክብር አስጠብቀዋል፡፡በመቀጠልም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ስላለፉት የጉባኤ ቀናት አጠቃላይ ቆይታና ወደፊትም ቤተ ክርስቲያን በምን መልኩ መጓዝ እንዳለባት ሰፋ ያለ ማብራሪያ በንባብ መልክ አስደምጠው መድረኩን ለቅዱስ ፓትሪያርኩ አስረክበዋል፤ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ስለ 36ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤና ስለ ቤተ ክርስቲያን ህልውና አባታዊና መንፈሳዊ መልእክታቸውን ለጉባኤው ታዳሚዎች እንዲህ በማለት አስተላልፈዋል የቤክርስቲያንን ጥሪ አክብራችሁ ፡ ከውጭም ከውስጥም ስለመጣችሁ እናመሰግናችኋለን የጋራ ቤታችን በሆነው የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ያገናኘን እግዚአብሔር ይመስገን፡ቤተክርስቲያናችን የሁላችን ህልውና ናት፡ሁላችን ልንጠለልባትም ይገባል፡ከዚህ መጠለያ ወጥተው የሚኮበልሉ ወገኖቻችን በምን ምክንያት እንደሚኮበልሉ ልንረዳቸው ያስፈልጋል፤ ቤተክርስቲያን  ከስብከተ ወንጌል የበለጠ ሌላ ሥራ የላትም  ይህንን ትረዱን  እንፈልጋለን በማለት እነዚህንና በአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት አበክረው የተናገሩ ሲሆን በተለይም ደግሞ የስብከተ ወንገል መስፋፋት፤ የቤተክርስቲያን ህልውናና ክብር እንዲሁም  የቤተክርስቲያን ህብረት ከመልእክቶቻቸው  መካከል ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፤  ከዚህ ጋር ተያይዞም ቤተ ክርስቲያን የአማኞች ሕብረትና በክርስቶስ ደም የተመሰረተች ናት በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው የስብከተ ወንጌል መስፋፋት ደግሞ የቤተክርስቲያን ህልውና ነው በማለት አክለውበታል፡፡በተጨማሪም  በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሰባክያነ ወንጌል  የአገልጋይ እጥረት  ወዳለባቸው ገጠር አብያተ ክርስቲያናት እየተጓዙ የቤተክርስቲያን ህልውና የሆነውን ወንጌልን እንዲያስፋፉ የመፍትሔ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡ ጥሪያቸውም አስተላልፈዋል፡፡በሚድያ በኩልም ቤተክርስቲያን የጀመረችውን የሚዲያ  ስራ ከዚህ በበለጠ መልኩ ጠንክራ ትሰራ  ዘንድ ይገባል በማለትና  አገልጋዮችም ሥራው የራሳቸው እንደሆነ ተገንዝበው የበኩላቸውን እንዲወጡ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደረጉና  ታዛዥነታቸውን እንዲገልጹ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡ በማከልም ሰው አስተውሎ ሲናገር ይመሰገናል ነገር ግን ተናግሮ የሚያናግር ደግሞ ተናጋሪ ቢያሰኝም በአደባባይ የተነገረ ስህተት በአደባባይ ሊታረም ይገባዋል ካሉ በኋል በጉባኤው ተገቢ ያልሆነ ቃል ተናግረዋል ያሉዋቸውን አንድ ሊቀ-ጳጳስ በአጽንኦት ገስጸዋል፡፡በመጨረሻም የሽልማት ኮሚቴ ባዘጋጀው የውድድር ነጥብ መስጫ ሃሳቦች መሰረት በአስር ምድብ በመከፋፈል ከየምድቡም ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት አህጉረ ስብከቶች ሽልማትና ሰርተፊኬት   ተበርክቷል፡፡የአዲስ አበባ ሃገረ-ስብከትም ፈር ቀዳጅነቱን በአደባባይ አስመስክሯል፡፡
በአጠቃላይ 36ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቅዱስነታቸው ጸሎት ተጀምሮ ለ4 ተከታታይ ቀናት ፡በርካታ የቤተክርስቲያን ጉዳዮችን ሲመለከት ቆይቶ፡ለሚቀጥለው በጀተ ዓመትም ሊሰሩ የሚገቡ ዋና ዋና የቤተክርስቲያን ሥራዎችን በመዳሰስና መመሪያ በመስጠት እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ ሊመለከታቸው የሚገቡ ባለ ሃያ አንድ ነጥብ  የአቋም መግለጫ አውጥቶ በቅዱስነታቸው ጸሎትና አባታዊ መመሪያ፤እንዲሁም በጠቅላይ ቤተክህነት እራት ጋባዥነት ተጠናቋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡፡