የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት 33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለ 21 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

200701

ዝርዝር የቋም መግለጫው ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል

፫፡የአቋም መግለጫና የውሳኔ አሳብ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ካስተላለፉት መልእክትና አባታዊ መመሪያ፣ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ ጽ/ቤትና በአህጉረ ስብከት ከከቀረቡ የሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች እና ጉባኤው ካደረጋቸው ግምገማዎችና ውይይቶች) በመነሣት ጉባኤው የሚከተለውን የአቋም መግለጫና የውሳኔ አሳብ አውጥቷል፡፡
፫.፩.የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉዞ
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉዞዎች ለአህጉረ ስብከት፣ ለወረዳዎችና ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ኀላፊዎችና ሠራተኞች መመሪያ በመስጠት፣ ምእመናንን በአካል አግኝተው በመባረክና በማስተማር፣ ካህናትንና ዲያቆናትን በመሾም፣ የአስተዳደር ችግሮችን በቦታው ተገኝተው በመፍታት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገርና ችግሮች ካሉ እንዲፈቱ በማድረግ እንዲሁም አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ባርከው በመክፈት ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ከፍተኛ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ከመ/ፓ/ጠ/ ቤተ ክህነትና ከየአህጉረ ስብከት ከቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች ጉባኤው ተገንዝቧል፤ ስለሆነም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክና ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የላቀ አባታዊ የአገልግሎት ስኬት ከመመኘት ጋር ይህን መሰል ሐዋርያዊ ጉዞዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
፫.፪. ስብከተ ወንጌል
በብዙ አህጉረ ስብከት የሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች አህጉረ ስብከት በሚያደርጉት የስብከተ ወወንጌል ማስፋፋት ሥራ አዳዲስ አማንያን በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን እየተጨመሩ መሆኑን አይተናል፤ አሳሳቢ የሆነውን የምእመናን ፍልሰት ለመግታት ዋናው መፍትሔ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ ማድረግ ስለሆነ ስብከተ ወንጌል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጠበቅብንን አስፈላጊ ጥረት ሁሉ እናደርጋለን፡፡
ሆኖም ግን በዐሥር ዓመታት ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያናችን ወጥተው ወደ ተለያዩ እምነቶች የፈለሱ መሆኑን ስናይ የተገኘው ፍሬ የደረሰውን ጥፋት የሚያካክስ፣ ወደ ፊት ሊደርስ የሚችለውን ጥፋትም ለመቋቋም በቂ ሆኖ አላገኘነውም፤ በአንጻሩም የስብከተ ወንጌል እንቅስቃስውንና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የተመለሱን ምእመናን ቁጥር ስናይ ፈጽሞ የማይመጣጠንና እጅግ አንስተኛ  መሆኑን አይተናል፤ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የምእመናን ፍልሰት ችግር መቋቋም የሚችል መጠነ ሰፊ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለመሥራት እኛ የ፴፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን፡፡ 
ለምእመናን ፍልሰት አንዱና ዋነኛው መንስኤ የችግሩን ብዛትና የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ በቂና ሰፊ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አለመኖርና የመልካም አስተዳደር መጥፋት ችግር ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን የህልውና መሠረት ቀዳሚ ተልዕኮ የሆነውን ስብከተ ወንጌልን ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በበለጠ በማጠናከር የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት፣አዳዲስ አማንያን በትምህርተ ወንጌል ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማምጣት፣ያሉትንም በሃይማኖት ለማጽናት ተግተን እንሠራለን፤ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን በፊት ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ በደተጋጋሚ የወሰናቸውንና ወደፊትም የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ለመፈጸምና ለማስፈጸም እንተጋለን፡፡
፫.፫. የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት
በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ሰበካ ጉባኤን በሚያደራጁበት፣ ከመንግሥት አስተዳደር አካላትና ከፍርድ ቤቶች ጋር የሥራ ግንኙነት በሚያደርጉበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች የገጠሟቸው ከመሆኑም በላይ በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለው ቃለ ዓዋዲ ከሀገሪቱ ሕጎችና ደንቦች ጋር ተጣጥሞ መሄድ ባለመቻሉ የአስተዳደር ሥራዎችን በአግባቡ መምራት ስላላስቻለ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና ቃለ ዓዋዲውን የማሻሻል ሥራው በፍጥነት ተጠናቅቆ  ጸድቆ መታተም እንዳለበት ጉባኤው በታላቅ አክብሮት ለቅዱስ ሲኖዶስ እያሳስብን ይህ እስኪሆን ድረስ ባለው ቃለ ዓዋዲ መሠረት ሰበካ ጉባኤን ለማደራጀትና ለማስፋፋት ተግተን እሠራለን፡፡  
፫.፬. የአብነት ትምህርት ቤቶች
የቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የታላላቅ ሊቃውንትና የአገልጋዮች ካህናት መገኛ የሆኑ የአብነት ትምህርት ቤቶች የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዐተ አምልኮት፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የማንነት፣ የሀገር በቀል እውቀቶች መሠረትና ምንጭ ስለሆኑ የአብነት ትምህርት ቤቶች መዳከም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዳከም፣ የአብነት ትምህርት መጥፋትም የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት መጥፋት ነውና ትምህርት ቤቶቻችንን ለመጠበቅ፣ ለማሳደግና ለማስፋፋት ተግተን እንሠራለን፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው አምስት ከመቶና ከመንበረ ፓትርያርክ የተመደበው የአብነት ትምህርት ቤቶች በጀት ለአብነት ት/ቤቶች ለመምህራንና ተማሪዎች ብቻ እንዲደርስ እስካሁን እያደረግን ያለነውን ጥረት በተጠናከረ ሁኔታ እንቀጥልበታለን፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በዚህ ዓመት እንዳደረጉት በአካል ተገኝቶ ተማሪዎችንና መምህራንን በመጎብኘትና በማበረታታት የሞራል ድጋፍ ማድረግም ስለሚያስፈልግ ጉባኤ ቤቶችን በአካል በመገኘት የማበረታታት ሥራችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ 

፫.፭.መልካም አስተዳደር
የመልካም አስተዳደር ችግር የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተንና የምእመናንን ፍልሰት የሚያባብስ ከባድ ችግር መሆኑን የ፴፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ሁላችን በአንድነት ተገንዝበናል፤ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሠራተኞች በየደረጃው የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑ በጎ ጅምር ስለሆነና ዘመኑ ሲለወጥ የሰው ልጅ አስተሳሰብም መለወጥ ስለሚገባው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዐትና ትውፊት በመጠበቅ፣ የመልካም አስተዳደር ሥርዐቶችን መርህ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ልትደርስበት ወደሚገባት ደረጃ ለማድረስ ሊደረግ የሚገባውን መልካም ሥራ ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ተግተንና ነቅተን ለመሥራት ቁርጠኞች ነን፡፡ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ ከሁሉም አህጉረ ስብከት የሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ለማበልጸግና የሙስና ችግርን ከቤተ ክርስቲያናችን ለማስወገድ ቆርጠን በመነሳት ጠንክረን ለመሥራት የታቀዱ እቅዶችን በትጋት በመፈጸምና በማስፈጸም የቤተ ክርስቲያናቸችንን ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ ቁርጠኞች መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡
፫.፮.የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ ስለመቆጣጠር
ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ መሠረት የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ የሚያራምዱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከተወገዙና ከተለዩ በኋላ የተዳከሙ ቢመስልም ውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴው ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳ ያለ መሆኑን ጉባኤው ከምዕራብ ወለጋና ከቄለም ወለጋ አህጉረ ስብከት ከቀረበው ዘገባዎች ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያንና በአገልግሎቷ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ያለውን የተሐድሶ እንቅስቃሴና የሌሎችንም መናፍቃን ተጽእኖ ለመቋቋም ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና ምእመናን በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ በማስተማር ተግተን እንሠራለን፡፡
፫.፯. የቤተ ክርስቲኒቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ማሰልጠናዎች  ዘመኑ የሚጠይቀውን የተማረ የሰው ኀይል ለማፍራት  እያደረጉት ያሉው ከፍተኛ እንስቅቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ኮሌጆች የሚገቡ ደቀ መዛሙርት በምልመላ፣ በቅበላና በትምህርት ዝግጅት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ በታከለበት ሁኔታ እንዲሠራ፣ ለልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሀገራችን ብሔረ ሰቦች የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ልማት ይደርስ ዘንድ ከሁሉም ብሔረሰቦች ደቀ መዛሙረት እንዲገቡና እንዲማሩ የሚደረገው ጥረት የበለጠ ቢሰፋ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሁን ካሉት በተጨማሪ የቤተ ከርስረቲያንን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ በሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፉ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ተቋማቱን ለማስፋፋት የሚያደረገውን ጥረት ሁሉ ለማሳካት ተግተን እንሠራለን፡፡ 
፫.፰.የሰ/ት/ቤቶች አደረጃጀት
የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ሀብት የሆኑ ብሔራውያን በዓላትን  በማክበር፣ ወጣቶችን በትምህርተ ሃይማኖትና በሥነ ምግባር በማነጽና ለነገ ሀገር ተረካቢነት ትውልድን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ያሉት የሰ/ት/ ቤቶች በረጅም ጊዜ እቅድ የመመራታቸው ጠንካራ ጎን እንደተጠበቀ ሆኖ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የሀገሪቱን ብሔረ ሰቦች ብዙኅነት ከግምት ውስጥ ያስገባና በየእድሜ ደረጃቸው ሊማሩ የሚችሉበት ሥርዐተ ትምህርት በብሔራዊ ደረጃ ተቀርፆ ማስተማሪያ መጻሕፍትም በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተውና በማእከል ደረጃ በሊቃውንት ጉባኤ እየተመረመሩ ታትመው ቢሰራጩ ቤተ ክርቲያንን የተለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ጉባኤው ጠቁሞ መምሪያውና አህጉረ ስብከት በጋራ ለሚሠሩት ለዚህ ታላቅ ሥራ ሁላችን የበኩላችንን እንወጣለን፡፡    
፫.፱. ልማት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል ራሷን ለመቻል የራስ አገዝ ልማትን በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የሚከናውነውን ሀገራዊ ልማት በማገዝ በኩል ከፍተኛ አስተወፅኦ በማድረግ ላይ እንዳለች ጉባኤው ገምግሟል፤ የቤተ ክርስቲያን ልማት ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ስለሆነ የሀገር ባህልን፣ ቅርስን፣ የሕዝብ ሥነ ምግባርን፣ ብሔራውያት ዕሴቶችን፣ በዓላትን፣ የአብነት ትምህርትን በአጠቃላይ የኅበረተሰቡን ሁለንተናዊ የሕይወት ጤንነት ማረጋገጥን መሠረት ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለብን ሃይማኖታዊ ብሔራዊ ኀላፊነት ለመወጣት ጠንክረን እንሠራለን፡፡ የራስ አገዝ ልማታችንን ከማከናወን ጎን ለጎን ታላቁ የሕዳሴው የኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ ግድብ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ደርስ የምናደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡   
፫.፲.ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶቻችንን መጠበቅ
ቅርሶቻችን የሃማኖታችን አገልግሎት መፈጸሚያዎች፣ ብሔራውያትና ዓለም አቀፍ ሀብቶቻችን ናቸው፤ ነገር ግን በየጊዜው የዘረፋ፣ የቃጠሎ፣ የብልሽት ችግሮች ይከሠቱባቸዋል፤ ይህ ችግር አሁንም እንዳልቀረ ለዚህ ጉባኤ የቀረቡ የዚህ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ዘገባዎች ያመለክታሉ፤ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ከማስተማርና ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ዘራፊዎችን በሕግ የመጠየቅና የማስቀጣት፣ ቅርሶች የማስመለስና በቦታቸው በጥንቀቃቄ እንዲያዙ በማድረግ ከጠ/ቤ/ክ/ ቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እስከ አጥቢያ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት እንተጋለን፡፡ ነባር ቅርሶችንና ንዋያተ ቅድሳትን ከመጠበቅም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት እየተዘጋጁ ያሉት አልባሳትና ንዋያተ ቅድሳት የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት የማይጠብቁ ከመሆናቸውም በላይ ምእመናን በነጋዴዎች እንዲበዘበዙ እያደረጉ ስለሆነ በማእከል ደረጃ የራሷ ማምረቻና መከፋፈያ ድርጅቶች እንዲጠናከሩና እንዲደራጁ ቅዱስ ሲኖዶስ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉባኤው ይጠይቃል፡፡
.፲፩.የቤተ ክርስቲያን ገቢ ማደግ 
በሳንቲም ደርጃ አስተዋፅኦ በመሰብሰብ የተጀመረው የሰበካ ጉባኤ ገቢ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የአቅም ማደግ፣ የራስን አገልግሎትና የልማት እቅዶች በራስ አቅም የመፈጸም አቅሟን እያሳደገው ስለሆነ የጉባኤው ተሳታፊዎች በተገኘው ውጤት እጅግ ተደስተናል፤ መሰብሰሰብ ብቻ ሳይሆን የተገኘውን የእግዚአብሔርን ገንዘብ በተገቢው የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት በጥንቃቄ በመያዝና ለሚገባ አገልግሎትና ልማት በማዋል እንሠራለን፤ በዚህ ዓመት ከተገኘው የተሻለ ገንዘብ ለሚቀጥለው የቤተ ክርስቲያን እድገትና አገልግሎት መሰብሰብ ስለሚያስፈልግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የቤተ ክርስቲናችንን የፋይናስ አቅም ለማሳደግና በራሷ ምእመንና ልማት ላይ የተመሠረተ ሉዓላዊ ክብሯን ለመጠበቅ ተግተን እንሠራለን፡፡
፫.፲፪.ሥራን በእቅድ ስለማከናወን
የመ/ፓ/ጠ/ቤተ ክህነት የእቅድና ልማት መምሪያ ሁሉንም መምሪያዎች በማስተባበር እቅዶች እንዲዘጋጁ ከማድረጉም በተጨማሪ በአህጉረ ስብከት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በቤተ ክርስቲያኒቱ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲሁም “ልማት በቤተ ክርስቲያን” በሚል ርእስ መምሪያው ባዘጋጀው መጽሔት  እያስተዋወቀና እያበረታታ ሰለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው በጎ ጅምር መሆኑን ጉባኤው ተመልክቷል፡፡
የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት ጽ/ቤት፣ በሥሩ ያሉ መምሪያዎች፣ ድርጅቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና አንዳንድ አህጉረ ስብከት ሥራዎቻቸውን አስቀድሞ ማቀድ፣ በእቅድ መፈጸም፣ እንዲሁም አፈጻጸማቸውን በእቅድ ግምገማ ሥርዐት መሠረት የመገምገም ጅምር ሥራዎችን እያከናወኑ ስለሆነ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሁሉም አህጉረ ስብከት  እንዲከናወን የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
፫.፲፫.ስልጣነ ክህነናትና ምንኩስና የሌላቸው አንዳንድ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጥሯቸውን ችግሮችን ስለመቆጣጠር
ስልጣነ ክህነትና ምንኩስና የሌላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ወደማይታወቁበት ሀገረ ስብከት በመሄድ “ስልጣነ ክህነት ተቀብለናል”፤ “መንኩሰናል” በማለት በተለያዩ አህጉረ ስብከት ችግሮችን እየፈጠሩ መሆኑን ለጉባኤው ከቀረቡ የአህጉረ ስብከት ዘገባዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ አይነት ተግባር ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ስለሆነ እኛ የዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች ይህን አይነት ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ተግባር የሚፈጽሙ ሰዎችን የመቆጣጠር፣የማረምና የማሰተማር ኃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡
፫.፲፬.ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ለጉባኤው ካስተላለፉት አባታዊ  መልእክት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ከባድ ችግር ተገንዝበናል፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታ ያለብን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ተስፋ እንዲያደርጉና ሠርተው ራሳቸውን ተግተው በመሥራት ድህነትን ማሸነፍ እንዲችሉ የሥራ ፍቅርን የሚያዳብሩ የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርቶችን ለምእመናን ለማስተማር ቃል እንገባለን፡፡
፫.፲፭.በሽታዎችን በተመለከተ
ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ በተደረገው ሀገራዊ ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተችውና አሁንም ይህን አስተዋፅኦዋን አጠናክራ በመቀጠል ላይ ያለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በአጠቃላይ፣ በአፍሪቃ በተለይ የሰው ልጆችን ሕይወት እየቀሠፈ ያለውን እጅግ በጣም አሰቃቂ የሆነ የኢቦላ በሽታን በተመለከተ በመላ የኢትዮጵያ ገዳማትና አደባራት ጸሎትና ምህላ እንዲደረግ  ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ያስተላለፉትን አባታዊ መልእክት የጉባኤው ተሳታፊዎች ከልብ ከመነጨ ታላቅ ርኅራኄ ጋር ተቀብለነዋል፤ ስለሆነም በበሽታው እየተጎዱ ያሉ አፍሪቃውያን ወገኖቻችን በእግዚአብሔር ርኅራኄ ከመከራው ዕረፍት ያገኙ ዘንድ በጸሎትና በምህላ እናስባቸዋለን፤ በሽታው ወደ ሀገራችን እንዳይገባ መንግሥት እያደረገው ያለውን የመከላከል ሥራም በጸሎትና ሕዝቡን በማስተማር እናግዛለን፡፡
፫.፲፮. የሕትመት ስርጭቶችን በተመለከተ
በግለሰቦችና በቡድኖች የተዘጋጁና “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ሥርዐትና ቀኖና የጠበቀ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ደንብ መሠረት የተዘጋጀ” የሚል ጹሑፍ ያለባቸው ነገር ግን በሊቃውንት ጉባኤ ያለተመረመሩና በማእከል ደረጃም ሆነ በአህጉረ ስብከት ደረጃ ያልፈቀደላቸው ጽሑፎች፣ የድምፅና የድምፅ ወምስል ሕትመቶች በምእመናን አእምሮ የስሕተት ትምህርቶችን እየዘሩ መሆኑን ከቀረቡ ዘገባዎች መረዳት ተችሏል፤ ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለና ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ትውፊትን፣ ቀኖናንና ሥርዐትን ሊለውጥ ስለሚችል በአህጉረ ስብከት የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እዲደረግ በማእከል ደረጃ ደግሞ የሊቃውንት ጉባኤ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የሕዝቡን ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ሊመልስ በሚችል መልኩ እያደራጀ ታትመው እንዲሰራጩ ቢደረግ መልካም መሆኑን ከማስገንዘብ ጋር፣ በግለሰቦችና በቡድኖች የሚታተሙ መጻሕፍትም ሳይመረመሩ እንዳይሰራጩ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ የወሰናቸው ውሳኔዎች በተግባር እንዲውሉ ተግተን እንሠራለን፡፡   
፫.፲፯. ሁሉም መምሪያዎች፣ድርጅቶችና አህጉረ ስብከት በፋይናንስ ሥርዐትና ሕግ መሠረት በየዓመቱ የሂሳብ ምርመራ በማድረግ ሥራቸውን በአግባቡ ሊያከናውኑ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በመሆኑም በዘንድሮው ዓመት የቁጥጥር መምሪያ ባደረገው የጥቂት አህጉረ ስብከት የሒሳብ ምርመራ ጉድለት ለታየባቸው እንዲያርሙና እንዲያስተካክሉ፣ጥሩ የሒሳብ አሠራርን ላሳዩ ምስጋና እንደሚገባቸው በዘገባው አስቀምጧል፡፡  የምርመራው ሂደት መቀጠል ያለበት በመሆኑ ሁሉም አህጉረ ስብከት በየዓመቱ በዋናው መሥሪያ ቤት የቁጥጥር መምሪያ ሒሳባቸውን ሊያስመረምሩ ይገባል፤በየዓመቱ ምርመራ ከተደረገ ጤናማ የሒሳብ አሠራር ከመኖሩም በተጨማሪ ሙስናን ለመቆጣጠር ስለሚያስችል የቁጥጥር መምሪያው  በሰጠው መግለጫ መሠረት ሁላችንም በየዓመቱ የሂሳብ ምርመራ በማድረግና በማስደረግ ተግተን እንሠራለን፡፡
፫.፲፰. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር መምሪያ በተለይም ማዕከል ሳይጠብቁ የሚመጡትን ባለጉዳዮች የአህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሩት ጉባኤ እንዲታዩና ውሳኔ እንዲሰጠው እያደረገ ያለው በጎ ጅምሩ ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብሎም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም በበጀት ዓመቱ ካለፉት ጊዜያት እየተንከባለሉ የመጡትንና በበጀት ዓመቱ የቀረቡለትን ማኅደረ ጉዳዮች በአስተዳደር ጉባኤ እየታዩ ለሁሉም መልስ በመስጠት በበጀት ዓመቱ በማጠናቀቅ እያደረገ ያለው ሊመሰገንና ሊበረታታ የሚገባው ሆኖ ስላገኘነው ይህ አሠራር በሁሉም አህጉረ ስብከት ጭምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
፫.፲፱.የማኅበራትን እንቅስቃሴ በተመለከተ
ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አግኝተውም ሆነ ፈቃድ ሳይኖራቸው በተለያየ መልኩ ተደራጅተው በማገልገል ላይ ያሉ ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የራሳቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው መሆኑ ይታወቃል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ችግሮች እየተፈጠሩና የቤተ ክርስቲያን ሰላም እየደፈረሰ ይገኛል፤ የዚህ ዐይነት ችግሮችን ለማስቀረት እንዲቻል ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት መርምሮ አስፈላጊ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉባኤው እየጠየቀ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስነውን ውሳኔ በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅሮች ውስጥ ለማስፈጸም ሁላችንም ዝግጁዎች መሆናችንን በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናረጋግጣለን፡፡

፫.፳. ይህ የ፴፫ተኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ያወጣው አቋምና የሰጣቸው የውሳኔ አሳቦች በቅዱስ ሲኖዶደስ ጸድቀው ለሁሉም አህጉረ ስብከት ከተላኩ በኋላ የውሳኔው አፈጻጸም በሚቀጥለው ዓመት ፴፬ኛው አጠቃይ ስብሰባ እንዲገመገም ይደረግ ዘንድ ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፫.፳፩. በመጨረሻም ይህ ጉባኤ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የረዳንን አምላችን እግዚአብሔርን እያመሰገንን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያው ይህ ዐቢይ ጉባኤ በዚህ መልኩ አምሮና ደምቆ እንዲጠናቀቅ ላደረገው ጥረት ሁሉ ያለውን አድናቆት በመግለጥ እግዚአብሔር ለ፴፬ተኛው አጠቃላይ መደበኛ ስብሰባ በሰላም ያደርሰን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት በማድረግ አቋማችንንና የውሳኔ አሳባችንን በዚህ እናጠቃልላለን፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ማጠቃለያ መልእክት
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በሰጡት የማጠቃለያ መልእክት “በየደረጃው የምትገኙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥሪ አክብራችሁ በየዓመቱ ለሚደረገው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ የተሳተፋችሁ በሙሉ እንኳን ለ፴፫ኛው ስብሰባ አደረሳችሁ! ስለ ቤተ ክርስቲያናችሁ የሥራ ውጤትና ያስገኘው ፍሬ ላይ ተወያይታችሁ ለዚህ ፍጻሜ በመድረሳችን ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
ለቤተ ክርስቲያናችን ያላችኋት ሀብቶች እናንተ ናችሁ፤እናንተው እንደየአቅማችሁና እንደየሁኔታው ወጥታችሁና ወርዳችሁ የተሠራው ሥራ በቀረበው ፐርሰንት ከፍተኛ እድገት መመዝገቡ ሊያስመሰግንና ወደፊትም ሊበረታታ ይገባል፡፡
በተለይም በዘገባ አቀራረብ በኩል እግዚአብሔር በሰጠን ህሊና ውስጥ አንድ ዳኛ ያለን ስለሆነ በእውነት በሠራነው ሥራ ላይ ሳይጋነን ቢቀርብ የቀረብንን የሥራ ውጤት ይታያል፡፡
በተለይም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የደረሰው ከፍተኛ ችግር አሳዛኝ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ይህም በጣም ቤተ ክርስቲያናችንን ያሳዘነ ሁኔታ መፈጸሙ ለወደፊቱ እንዳይከሰት እንደተለመደው ልንጸልይ እግዚአብሔርን በአንድነት ሆነን ልንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ከዚሁ ጋር የምእመናን እንደ ጥንቱ ቤተ ክርስቲያናቸውን እና እምነታቸውን አጠንክረው እንዲይዙ በስብከተ ወንጌል መጠናከርና መስፋፋት ላይ የበለጠ ልንሠራ ይገባል፡፡
ከዚህም ሌላ መልካም አስተዳደር ምንጊዜም ቢሆን ከህሊናችን መጥፋት የለበትም፡፡ ሥችንንም በኃላፊነት፣በተጠያቂነት፣ በንጽሕናና በቅድስና መሥራት አለብን፡፡ ከስደት የተመለሱ ወገኖቻችንንም አንዳንዶቹ ያን መከራ ረስተው ወደ አልተፈለገ ፈተና በድጋሚ ለመሄድ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው እየተነገረ ስለሆነ በሀገራቸው ሠርተው መክበር እንዲችሉ ማስተማር አለብን፡፡

በአጠቃላይም በዓለም ላይ ተከስቷል ስለተባለው በሽታ ስለ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተሳትፎ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም ስለሚደረገው የሥራ እንቅስቃሴ፣በገንዘብ ምክንያት አስተዳደሯ በሁለት በኩል ሊከፈል አይገባውም፤ከልጆቻችንም በግል ጥላቻ የለንም በአሠራር ግን በቤተ ክርስቲያናችን ሀብታቸውና ንብረታቸው ተመዝግቦና ታውቆ እንዲሠራ ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ የጋራ ኃላፊነት ነው” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው በጸሎት ተዘግቶ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል፡፡ 

ጥቅምት ፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም
አዲስ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ {flike}{plusone}