የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የ3 ቀናት ሥልጠና በአቋም መግለጫ ተጠናቀቀ!!

0107

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሚገኙ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የምክትል መምሪያ ኃላፊዎችና አጠቃላይ ሠራተኞች ሒሳብና ሥራ አመራር፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ሥራና መንፈሳዊ ሕይወት፣ ሥራ ፈጠራ፣ ሒሳብና ንብረት ላይ የተመሠረተ የሦስት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት የመመሪያ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ብዛት 336 እንደሚደርስ ተረጋግጧል፡፡ የስልጠናው ዝግጅት አቅራቢዎች ታዋቂ ምሁራንና የረጅም ጊዜ የማስተማር ልምድ ያላቸው መሆናቸው ተነግሯል፤ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ከሰልጣኞቹ የሚከተለው ባለ 12 ነጥብ አቋም መግለጫ ቀርቧል፡፡
የአቋም መግለጫ
ሥልጠናውን የወሰድነው እኛ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች ም/ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ከመጋቢት 19-21 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በተሰጠን የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰፊ እውቀትና ግንዛቤ የገበየን በመሆኑ ለወደፊት ሥራችን የተሳካ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1.የክርስቲያናዊ ሥነ ምግበር መገኛዋ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች እኛ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ለመልካም ሥነ ምግባር ቀዳሚ ሆነን ለመገኘት ቃል እንገባለን፡፡
2.የቤተ ክርስቲያኗን ጥንታዊነትን፣ ታሪካዊነትን፣ በተለይም ለሀገር ያበረከተችውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አስጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚቻለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያለውን ትውልድ በማፍራት ስለሆነ ይሄንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ሁላችንም በተሰማራንበት የሥራ መስክ ለመተግበር ቃል እንገባለን፡፡
3.በየትኛውም መስክ የተገኘ እውቀት በሥነ ምግባር ካልተነፀ ውጤታማ ስለማያደርግ እኛ የስልጠናው ተሳታፊዎች የቤት ክርስቲያናችንን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በተቋማችን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ተጠብቆ እንዲሠራ ብርቱ ጥረት እናደርጋለን፡፡
4.ሥራና መንፈሳዊ ሕይወት የማይነጣጠሉ መሆኑን በመረዳት መንፈሳዊ ሕይወትን በሥራ፣ ሥራን በመንፈሳዊ ሕይወት በመተርጎም አጣጥሞ የቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊ አገልግሎት (የእግዚአብሔርን መንግሥት) ለማስፋፋት የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
5.እኛ በዋናው መ/ቤት የምንገኝ አጠቃላይ ሠራተኞች የሥራን ክቡርነት በመረዳት በየደረጃው ላሉ የበታች መሥሪያ ቤት ሠራተኞች አርአያ በመሆን የሥራን ክቡርነት ተግብሮ ለደማስተግበር ቃል እንገባለን፡፡
6.ዓለም የሚለወጠው በማንበብና በእውቀት በመሆኑ ሥራን ፈጥሮ ለመሥራትና መንፈሳዊ ሕይወትን ለማሳደግ ማንበብ ትልቁ ቁልፍ ተግባር መሆኑን በመረዳት ባለን ትርፍ ጊዜ የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን የማንበብ ልምዳችንን ለማሳደግ ቃል እንገባለን፡፡
7.የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ አገልግሎት የተሟላ አድርጎ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ለሥራ ተነሳሽና መፍትሔ አምጪ በመሆን በተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጃችንና በየደረጃው ካሉ የሥራ  ኃላፊዎቻችን ጋር ተባብሮ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
8.ብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወደዚህ ታላቅ ኃላፊነት በመጡበት ጊዜ ከወርሃ ግንቦት 2008 ዓ.ም ጀምሮ የቤተክርስቲያኗን መብትና ጥቅም ለማስከበር እያደረጉ ያለውን ቆራጥ አመራርና ክትትል እያደነቅን ለወዲቱም ለተያዘው እቅድና ተግባራዊነት እኛ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ም/ኃላፊዎችና አጠቃላይ ሠራተኞች ከጎናቸው እንቆማለን፡፡
9.በዋናው መ/ቤታችን የተሰጠን ይህ የአቅም ግንባታ ስልጠና በቂ እውቀትና ግንዛቤን  የሰጠን ስለሆነ እንደዚህ አይነቱ የስልጠና መርሐ ግብር በየጊዜው ቢሰጠን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገን እናረጋግጣለን፡፡
10.እኛ በአመራር ወይም በኋላፊነት ደረጃ ያለን የሥራ ኃላፊዎች ለቤተ ክርስቲያኗ እድገት ተመሪዎችን ብቻ ሳይሆን መሪዎችንም ጭምር ለማፍራት በርትተንና ተግተን የተጣለብንን የሥራ ኃላፊነት ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
11.በተሰጠን የንበረት አመዘጋገብና አጠባበቅ ስልጠና ባገኘው ሰፊ ግንዛቤ ያለንን ልምድና ተሞክሮ በማጠናከር ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት ከብክነትና ከጥፋት በመታደግ በተገቢው ሥርዓትና ክብር በመጠበቅ እየተገለገልን ወደ ትውልዱ እንዲተላለፍ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡
በመጨረሻም በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጃችን ጥረትና አመራር ሰጪነት የተጀመሩት አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗ የልማት ሥራዎች ቤተ ክርስቲያኗን ላቅ ወደ አለ ደረጃ የሚያሸጋግራትና ከድህነት የሚያወጣት ተግባር በመሆኑ ለልማት ሥራው ስኬት ሁላችንም በተሰማራንበት ሥራ ተግተን ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
12.ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚሰጠንን አባታዊ የሥራ መመሪያ ለመፈጸምና ለማስፈፀም ቃል እንገባለን፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት አባታዊ ትምህርት የሰው ልጅ በአሁኑ ጊዜ በስልጠና አእምሮውን እያሰፋ በሚገኝበት ጊዜ የቤተ ክህነት ሠራተኞችም ስልጠና እንዲሰጣቸው በማሰብ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሐሳቡን አመንጭተው ይህን ስልጠና በማዘጋጀታቸው በጣም እናመሰገናቸዋለን፤ አሠልጣኞቹንና ሠልጣኞችንም እናመሰግናቸዋለን፤ እግዚአብሔር ይባርካቸው!!
ቤተ ክርስቲያናችን ከሁሉ በፊት አስተማሪ፣ መካሪ፣ አሰልጣኝ ሆና ከመሠረቱ ጀምሮ  ብዙ ሥራ የሠራች ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዩኒቨርስቲ ሆና የቆየችው ቤተ ክርስቲያን ናት፣ በመጀመሪያ ፊደል ቀርጻ መጻሕፍትን በእጅ ጽፋ ስታሰለጥን የቆየች ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ይህ አሠራር ለረጅም ጊዜ ሳይቀጥል በመቅረቱ ነው ብዙ ነገር የተበላሸው፤ ስልጠና እጅግ አስፈላጊ ነው፤ አእምሮን ማስፋፋት፣ የሥራ ተነሳሽነትን ማበልጸግ አስፈላጊ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ሀብታምና ባለ ፀጋ ናት እንጂ ድሀ አይደለችም፤ ከሥራ ተነሣሽነት አለመኖር ይልቅ በሌላ ነገር መዋጥ ብዙ ችግር ፈጥሯል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ሀብቷ ምዕመናን ናቸው፤  ምዕመናኖቻችንም በርካታ ናቸው፤ በርካታ የሆኑትን ምዕመናንን በስብከተ ወንጌል ባለማጠናከራችን የተነሣ ምዕመናን በልዩ ልዩ መንገድ እየተወሰዱ ናቸው፡፡
ሁለተኛው የቤተ ክርስቲያን ሀብት ይዞታዋ ነው፤ ይዞታዋም ሰፊ ነው፤ ይህ ሁሉ ንብረት እያለ ግን በአግባቡ የሚሠራ አልተገኘም፤ እየተዘዋወርን ይዞታችንን በጎበኘንበት ወቅት ሰፋፊ ይዞታ ያለን መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡
ስለዚህ ሁሉም ችግር የሚፈታው የሰው አእምሮ በስልጠና ሲለወጥ ስለሆነ በየጊዜው ይህ  ስልጠና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ አባታዊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡