የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ሦስተኛ ዓመት በዓለ ሢመት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 3ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳሳት፤ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማዕምራን የማነ  ዘመንፈስቅዱስ  ፤የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያና የየድርጅቱ ኃላፊዎች ፤አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት  ልዩ  ልዩ የሥራ ኃላፊዎች፤ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤አቶ ሙሉጌታ የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ፤አቶ ተወልደ ገ/ፃድቃን በአዲስ አበባ ከተማ የኢአዴግ  ጽ/ቤት ኃላፊ ፤ኮማንደር መኮንን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የፍትህ ቢሮ የስራ ሂደት ኃላፊ እና ልዩ ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት ዛሬ ሐሙስ የካቲት 24/2008 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል::

0071

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀን ወስና፣ በዓል አድርጋ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ አንዱ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና በአንደኛው መቶ ክ/ዘመን (በ34) ዓ.ም በጃንደረባው ባኮስ አማካኝነት ክርስትናን እንደተቀበለች በታላቁ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ “የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደሆነ መንገድ ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ሔደ፤ እነሆም “ህንደኬ”  የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቡዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፤ መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤ ፊልጶስም ሮጦ  የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፤ እርሱም “የተረጐመልኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” አለው፤ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነብበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፣ እንደበግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፤ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና” ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ እባክህ ነቢዩ ይህን ስለማን ይናገራል ስለራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ አለው፤ ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡
በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው?” አለው፡፡ ፊልጶስም  “በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል” አለው፤ መልሶም  “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ”  አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፤ አጠመቀውም፤ ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና” (የሐዋ. ሥ. ፰÷፳፮-፴፱)  በማለት ወንጌላዊው ሉቃስ እንደተረከው የክርስትና እምነትና ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34ዓ.ም. በኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሕንደኬ ጃንደረባ በባኮስ አማካይነት ነው፡፡ ያጠመቀውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወንጌላዊው ፊልጶስ ነው፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ” የሚለውን የእምነት ቀመር በመናገር የጀመረና ለዓለም ያበረከተም ኢትዮጵያዊው ባኮስ ነው፡፡

0028

በዚህም በዓለማችን ካሉ ሀገራት ክርስትናን ቀድማ የተቀበለች ሀገር ኢትዮጵያ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እስከ 1921 ዓ.ም ባለው ረጅም ጊዜ ውስጥ ከራሷ ሊቃውንት መርጣ ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም ባለመቻሏ ከግብፅ (እስክንድርያ)  ሲኖዶስ እየተላኩ በሚመጡ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ነበር አገልግሎት ስታገኝ የነበረው፡፡
ከመጀመሪያው ጳጳስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን፣ (ፍሬምናጦስ) ማለትም ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ ግብፃውያን አባቶች ከእስክንድርያ እየተላኩ ኢትዮጵያን በሊቀ ጵጵስና ሲያገለግሉ መኖራቸውን ታውቛል።
አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን የሚል ስያሜ ከወጣላቸው ፍሬምናጦስ ጀምሮ ከእሳቸው በኋላ እየተሾሙ የመጡት አባቶች ቡራኬ በመስጠት የኦርቶዶክስ እምነትን ያስፋፉ ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ እንዲላክላት ያልገበረችው የወርቅ አይነት፣ ያላሳለፈችው መከራ እና ያልከፈለችው መሥዋዕትነት የለም።
ይህም ብቻ አይደለም፣እንደ ዛሬው መጓጓዣ አመቺ ባልነበረበት ሰዓት እና ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ለመሄድ አጋሰስ እና የእግር ጉዞ ብቻ የመጓጓዣ መሣርያ በሆኑበት ዘመን አባቶቻችን የግብፅን በረሐ ባዶ እግራቸውን ለብዙ ወራት በመጓዝ ጉዳይ ለማስፈጸም ከኢትዮጵያ ወደ እስክንድርያ ሲመላለሱ ለመኖራቸው የታሪክ ምሁራን ምስክሮች ናቸው።
ቤተ ክርስቲያናችን ከ1921 ዓ.ም ጀምሮ ከእራስዋ ልጆች ጳጳሳት ተሹመውላት ሃይማኖቷን በመጠበቅና በማስጠበቅ ብትኖርም ከሁሉ የበለጠውና በገናናው የዛግዌ ሥረወ መንግሥት፣ በንጉሥ ሐርቤይ ዘመን ተጀምሮ የነበረው ኢትዮጵያ ከራሷ ሊቃውንት ጳጰሳትን የመሾም ሕልሟ የተፈታው ግን ሰኔ 21/1951 ዓ.ም በግብፃዊ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ መልካም ፈቃድ፣ በኋላ ከራሷ ልጆች መካከል የመጀመሪያ ፓትርያርኳን አቡነ ባስልዮስን ስትሾም ነው።
ታሪክ እንደሚነግረን ከንጉሥ ሐርቤ ዘመን ጀምሮ ያለማቋረጥ ኢትዮጵያውያን ከእስክንድርያ እየተሾሙ የሚመጡትን ጳጳሳት ስለሁኔታው አስፈላጊነት ሲጠይቁና ሲሞግቱ ኖረዋል።  የብዙ ዓመታት ትግል መልስ ያገኘችው ግን በፈቃደ እግዚአብሔር በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥረት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከ40 ጊዜ በላይ የተወሳች ሲሆን ከክርስትና በፊት የብሉይ ኪዳንን እምነትና ባህል ተቀብላ እግዚአብሔርን ታመልክ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።
በዚህ መሠረት በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካበረከቱ ቅዱሳን መካከል ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከጃንደረባው ባኮስ በመቀጠል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “ቅዱስና ያለ ተንኰል የሚኖር የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባኛል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡
በወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን ራሱኑ ሾሞ ላከው፡፡

3001

ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በመጀመሪያው ምዕት ዓመት ይሁን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በአራተኛው ምዕት ዓመት “በ330 ዓ.ም.” ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት የክርስትና ሃይማኖት በዐዋጅ ተሰብኳል፡፡ አባ ሰላማም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ፡፡በዚሁ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ይነግረናል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ኸያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በግብፃውያን አባቶች ስትመራ የነበረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ1921 ዓ.ም የግብፅ ቤተ ክርስቲያን የጵጵስና ማዕረግ የመስጠት ልማዳዊ መብቷን ለኢትዮጵያውያን አለቅም በማለቷ ብዙ ድርድር ከተደረገ በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ፤ አቡነ ባስልዮስ ተብለው ከሌሎች አራት ኢትዮጵያን ወንድሞቻቸው ጋር በእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ ተሾሙ፡፡
እንደገናም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በግብፅ ቤተ ክርስቲያን መካከል ብዙ ጊዜ የወሰደ ክርክርና ድርድር ተደርጎ በመጨረሻም ከስምምነት ላይ በመደረሱ እሑድ ሰኔ 21 ቀን በ1951 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው በመመረጣቸው የእክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ የሥርዓተ ሲመቱን ጸሎት አድርሰው የፓተርያርክነቱን ዘውድ አቀዳጅተዋቸዋል፡፡
በዚህም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በግብፅ ፓትርያርክ እጅ ተቀብተው የተሾሙ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአቡነ ባስልዮስ እስከ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ስድስት ፓትርያርኮችን ያስመረጠች ሲሆን ስድስተኛውም ፓትርያርክ በ2005 ዓ.ም የካቲት 21 ቀን ከመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ተወክለው በመጡ ካህናት ምዕመናንና የሰንበት   ት/ቤት ተወካይ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ድምፅ የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ናቸው፡፡
በቅዱስነታቸው የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ከኢትዮጵያ ካህናትና ምዕመናን በተጨማሪ ከግብፅ ካይሮ የመጡ በብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን አቃቢ መንበረ ፓትርያርክ የተመሩ ልዑካን ተሳትፈው ነበር፡፡
ቅዱስነታቸውም ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ የጐዳደለውን በመሙላታቸው እና የጠመመውን በማቅናታቸው በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ከፍተኛ ለውጥ በመምጣት ላይ ነው ለውጡም የሚታይና የሚዳሰስ ለውጥ ነው፡፡
በተለይም ልዩ ሀገረ ስብከታቸው የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቅዱስነታቸው በሚሰጡት አባታዊ መመሪያ በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሙዳዬ ምጽዋት ከመጠበቅ ለመላቀቅ በሚያደረጉት ትግል፣ ዛሬ በአዲስ አበባ ሀገር ስብከት በልማት ላይ ያልሆኑ አብያተ ክርስቲያን ማግኘት ወደማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡
በተጨማሪም ቅዱስነታቸው ከበዓለ ሲመታቸው ዕለት ጀምሮ ቁርጥ አቁም የወሰዱበት፣ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ስሟ ስም በማሰጠት የቤተ ክርስቲያኗን ልጆች በውስጥም በውጭም ሲያሸማቅቅ የነበረው ብልሹ አሠራር ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በቅዱስነታቸው ተመድበው በመጡት ከዘርና ከሙስና ነፃ በመሆናቸው እና ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት በሚያደርጉት ጥረት ከብዙ ካህናትና የቤተ ክርስቲያኗ ማህበረሰብ አድናቆት የተቸራቸው፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በሚሰጡት በሳል አመራር የተወገደ በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያን የሰላም ዘመን ነው በማለት የሚያደንቁት ብዙዎች ናቸው፡፡
አሁን የአዲስ አበባ ሀገር ስብከት ከራሱ አልፎ ሌሎች ችግር ያለባቸውን አህጉረ ስብከቶች ችግር በመፍታት ላይ የሚገኝ ሀገረ ስብከት ሆኗል፡፡ሀገረ ስብከታችን ካከናወናቸው በርካታ አኩሪ ተግባራት መካከል ሃይማኖት ካልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ከጋምቤላ ክልል እና ከደቡብ ሱዳን በሀገረ ስብከታችን ሥራ አስኪያጅ አማካይ መጥተው በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት በመከታተል ላይ ያሉት ደቀ መዛሙርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ የሆነው ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ሥራ ያቀላጥፋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በገንዘብ ምክንያት ግንባታው እንዳይስተጓጐል ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የገንዘብ ድጋፍ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ሀገረ ስብከታችን የቅዱስነታቸው ልዩ ሀገረ ስብከት ከመሆኑም በላይ በሀገራችን መዲና አዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ ስለሆነ በየጊዜው ከአዳዲስ እና ዘመናዊ አሠራር ጋር ከሌሎች አህጉረ ስብከቶች ቀድሞ መተዋወቁ እውን ነው፡፡ በዚህም ሀገረ ስብከቱ እስከ አሁን የነበረውን ልማዳዊ የሒሳብ አያያዝ ዘዴ ወደ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ የቀየረው በዚሁ በያዝነው ዓመት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሦስተኛውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዓለ ሢመት የምታከብረው በዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ድልና ስኬት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስኬቶች ሀገረ ስብከቱ በቅዱስነታቸው አመራር ሰጪነት ከሠራቸው እጅግ በርካታ በጐ ሥራዎች የተወሰኑት ናቸው፡፡
ስለዚህ በዓሉ የቤተ ክርስቲያን ነውና የቤተ ክርስቲያን የሆነው ሁሉ በየችሎታው ሊያከብረው ይገባል፡፡ አባቶቻችን ይህንን ለማስገኘት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ከንጉሥ ሐርቤ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ባደረጉት እልክ አስጨራሽ እና የመንፈስ ቆራጥነትን የሚፈታተን አድካሚ ተግባር የተገኘው እድል ዛሬ ላይ በእጅ የያዙት ወርቅ እንዳይሆን፣ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ምክንያቱም የቅዱስ ፓትርያርክ በዓለ ሢመት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በተወሰኑ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ከሚተዳደሩ ገዳማት እና አድባራት እንዲሁም ካቴድራሎች በሚመጡ አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ መዘምራን እና ዲያቆናት ብሎም ለቤተ ክርስቲያን ካላቸው ፍቅር የተነሳ በሚመጡ ጥቂት ምእመናን ብቻ ታስቦ መዋሉ የበዓሉን ታላቅነት አይመጥንም፡፡
ስለዚህ ይህ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከደረሰችበት ቦታ ሁሉ በዝማሬ እና በምስጋና መከበር ያለበት በዓል ስለሆነ ሁላችንም ልናስብበት ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

{flike}{plusone}