የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን አንድነት ጉባኤ የ3ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በታላቅ ድምቀት አከበረ
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፤ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንገዶች ፤ተመራቂ ደቀ መዛሙርት፤ የኮሌጁ መምህራንና ደቀ መዛሙርት በተገኙበት ግንቦት 10/2006 ዓ.ም በጠቀላይ ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የአንድነት ጉባኤ የምስረታ በዓሉ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
በዓሉ በተከበረበት ወቅት ከዝግጂት ክፍሉ የቀረበውን ጠቅላላ ሪፖረት እንደሚከተለው አቅረበነዋል፡፡
“ወአዲ እብለህክሙ ለእመ ኃብሩ ክልኤቱ አዉ ሠለስቱ እምኔክሙ በውስተ ምድር በእንተ ኩሉ ግብር ዘሰዓሉ ይትገበር ሎሙ በኀበ አቡየ ዘበሰማያት እስመ ፤ እስመ ኀበ ሀለዉ ክልኤቱ ሠለስቱ በስምየ ህየ እሄሉ አነ ማዕከሌሆሙ” ማቴ. 18÷19፡20
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሉኝ ከምትላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል በብዝኃ ዘመኑ የቀዳማዊነቱን ሥፍራ ይዞ የሚገኘው ተዋቂውና አንጋፋው የሰዋስዎ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ነው፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የብዙ ሊቃውንት ምንጭ የሆኑ ብዙ አይናማ ሊቃውንትን በማስተገኙ የሚነገርለት ይሄው ኮሌጃችን ነው፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በአሳለፈቻቸው የታሪክ ጉዞ ውስጥ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ በራሷ ፊደል፣ በራሷ ቋንቋ፣ በራሷ ሊቃውንት፣ በተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት ሀልዎተ እግዚአብሔርን ስትመሰክርና ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ሥርዓቷንና ትውፊቷን ጠብቃ እስከ ዘመናችን ድረስ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ባለ ውለታ ሆና የቆየች ጥናታዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን ስለመሆኗ ሲታሰብ በዋነኝነት የሚጠቀሱት የታሪክ አሻራዎቿንና የማንነቷ ምስክሮች የአብነት ት/ቤቶችና መምህራን መሆናቸው አይዘነጋም፡፡
ከፋሺስት የኢጣሊያ ወረራ በኋላ በ1933 ዓ.ም ቤተክርስቲያናችን ከአቋቋመቻቸው 3 የትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው የሰዋስዎ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቤተክርስቲያናችን ካሏት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ልዩ የሚያደርገው ከየአህጉረ ስብከቱ በስልጠና የሚመጡ ደቀመዛሙርት እና የኮሌጁ መምህራን ጭምር አብዛኛዎቹ መሠረታዊ በሆነው የአብነት ት/ቤት በአንዱ እና ከአንድም በላይ የጉባኤ መምህራን ናቸው፡፡ ለዚሁ ሐሳብ ዋና ማስረጃችን ደቀመዛሙርቱ ገና ወደ ት/ቤቱ ለመግባት በሚሰጣቸው የእውቀት መመዘኛ ፈተና ብዙዎቹ ሲታዩ “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ ለመማር የመጡ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ለመማር የመጡ መምህራንም ጭምር ስለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው” ት/ቤቱ ከተመሰረተበት ዘመን ጀምሮ ወደ ት/ቤት የሚገቡት ደቀመዛሙርት ሁለገብ ባለሙያዎች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን በኃላፊነትም ሆነ ለአስተማሪነት የሚመደቡት ሙሁራን የቤተክርስቲያኗ አሉ የሚባሉ ሊቃውንት መካከል እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል፤ ዛሬም በተግባር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከነዚህ ተዋቂ ሊቃውንት መካከል ዛሬ በሕይወት የሌሉትን ለመዘከር ያህል፡- ብፁዕ አቡ መርሐ ክርስቶስ፣ ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፣ እነ የኔታ ገ/ሥላሴ ዘሞጣ፣ እነ የኔታ ስብሐት፣ እነ መምህር እንባቆም፣ እነ መምህር ሰይፈ ስላሴ፣ እነ መምህር መንግሥቱ ቀጸባ፣ እነ ዶክተር የማነ ወዘተርፈ
ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ት/ቤት የተመረቁት የደቀመዛሙርት ብዛት 1085 ሲሆን ከነዚህ መካከል 9 ሊቃነ ጳጳሳት ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ሠዓት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የቤተክርስቲያኗ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚገኙት አብዛኛዎቹ የዚሁ ኮሌጅ ተመራቂዎች ናቸው፡፡
የዚሁ ኮሌጅ ምሩቃን ት/ቤቱ በአዳሪ ት/ቤት ከተመሰረተበት ዘመን ጀምሮ ቤተክርስቲያናችን አሁን በደረሰችበት የስብከተ ወንጌል የእድገት አቅጣጫ መሠረትና የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞች ፊተኞች ሆነው ቢስተዋልም እውነታው አይዘነጋም እና “እብን ዘመነንዋ ነደቅት ወኢኮነት ውስተ ርዕሰ ማዕዘነት” ተብሎ እንደተጻፈው፡፡
ኮሌጃችን ልዩ ልዩ ሀብተ ጸጋ ያላቸውን በእውቀት ደረጃቸውም የላቁትን በማሕጸኗ ወልዳና ኮትኩታ ያሳደገች እውነተኛ ወላጅ እናት ስትሆን በእውቀታቸውና በመንፈሳዊ ብቃታቸው የታወቁ ምሁራንን ያፈራች ሆና ሳለ የወላድ መካን የመሆኗ ሁኔታ ለምሩቃኑ የሕሊና ስቆቃ ሁኖብን ቆይቷል፡፡
ት/ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመረቅ ከጀመረበት አንስቶ ተመርቀው ወደመጡበት ከተሰማሩ በኋላ እንደማንኛውም የኮሌጅ ምሩቃን በማእከል ተሰባስበው የወንድማማችነት ሕብረት ለመመሥረት እና አቅም በሚፈቅደው መጠን ት/ቤቱን ለማሳደግ በየዘመናቸው እቅድና አላማ ቢኖራቸውም እንኳ ምቹ ምክንያታዊ ሁኔታ ከማጣታቸው የተነሣ ለብዙ ዘመናት የጨው ዘር ሆነው ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ለቤተክርስቲያኗም ትልቁ ኪሣራ ብዙ ሀብቷንና ንብረቷን አፍስሳ ከአስተማረቻቸው ደቀመዛሙርት አንዳንዶቹ ወደተጠሩበት ዓላማ የሚያሰማራቸው አጥተው ሥጋዊ ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ከእናት ቤተክርስቲያናቸው ጉያ ወጥተው የተሰደዱ የመኖራቸውን ሁኔታ ስናስብ ከሞኝ ጓሮ ሞፈር ይጎረጣል እንዲሉ ለቤተክርስቲያናችን ትልቅ ጉዳት ስለሆነ ወደፊት እንዲህ አይነቱ ልምድ እንዳይቀጥል ሊታሰብበት ይገባል እንላለን፡፡
ይህንና ይህን የመሰለውን ሁሉ ስናስበው ጉዳዩ እንቅልፍ የሚነሳ ከመሆኑ የተነሳ ቢያንስ በማዕከል በመሰባሰብ በመንፈሳዊ ወንድማማችነት በመተሳሰብ መረዳዳቱ እና የቤተክርስቲያኗ ተልዕኮን መፋጠኑ ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቅ ጥበብ መሆኑን በመረዳት ለብዙ ዘመናት ስናስበውና ስናልመው የነበረው የመሰባሰባችን ጉዳይ እግዚአብሔር ፈቅዶና ወዶ የዘመኑ ቀጠሮ ሲደርስ መስከረም 8 ቀን 2003 ዓ.ም 16 የኮሌጁ ምሩቃን በራሳችን ተነሳሽነት “የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የነገረ መለኮት ምሩቃን አንድነት ጉባኤ” በሚል ስያሜ ዛሬ ላይ የሚታየውን ዓመታዊ በዓል ለማክበር ችለናል፡፡ በቀጣይነትም በረከታቸው የደረሰን እና በወቅቱ የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ለነበሩት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ደረጃውን በመጠበቅ ቅድመ እውቅና ለማግኘት ጥያቄ አቅርበን ስለነበር ቅዱስነታቸውም ከአዳሪ ተማሪነት እስከ ዲንነት ያገለገሉበት ት/ቤት እንደነበረ አስታውሰውን እስከ አሁን መዘግየታችን ስንፍና እና ምንደኝነት መሆኑን ነግረውን እኔም አባል ነኝ፤ በውጪ ሀገርም የተማርኩበት ኮሌጅ አባል ሆኜ እስከ አሁን ድረስ ወርሃዊ መዋጮ እከፍላለሁ ስለዚህ አላማው የተቀደሰ ስለሆነ በርቱበት በማለት አባታዊ ምክርና ሞራልን ከሰጡን በኋላ ወደሚቀጥለው አካል ትዕዛዝ ሰጥተውበታል፡፡ ከዚህ የተነሳ እስከ አሁን ላሳለፍነው ጉዞአችን ብርታት ሆኖን በአላማችን ጸንተን እንገኛለን፡፡
የምሩቃኑ አንድነት ጉባኤ የወደፊት ዓላማ ራእይና ግብ ኑሮት የተመሰረተ ስለሆነ በሶስት ዓመታት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ የዛሬውን የመጀመሪያ ዞር የምሥረታ በዓል ለማክበርና የት/ቤቱ 71 ዓመታት የመማር ማስተማር ጉዞውን ለመዘከር በቅተናል፡፡
1. የምርቃኑ አንድነት ጉባኤ በሶስት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ካከናቸው አበይት ተግባራት
• የምሩቃን አንድነቱ ጉባኤ የሚመሩ 9 አባላትን ያቀፈ ጊዜያዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መርጦ ሥራውን እንዲመሩ አድርጓል፡፡
• ባለ 12 ገጽ እና ባለ 25 አንቀጽ ውስጠ ደንብ በማዘጋጀት በሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡
• የምሩቃኑን አንድነት ጉባኤ እውቅና እንዲያገኝ በየደረጃው በተደረገው ጥረት ለዚህ ታላቅ ዓመታዊ በዓል ለመድረስ በቅተናል፤
• ከኮሌጁ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በኮሌጁ ግቢ በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ቋሚ ስብሰባ እንድናካሄድበት ማስፈቀድ ተችሏል፡፡
• ከአባላቱ የሚሰበሰበው ወርሃዊ መዋቸጮ በሕጋዊ ደረሰኝ የተሰበሰበ በምሩቃኑ አንድነት ጉባኤ ለተከፈተው የባንክ አካውንት ገቢ ይደረጋል፡፡
• የራስጌና የግርጌ ማሕተም በማህበሩ ስም ከትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በማስቀረጽ በሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
• በየአሕጉረ ስብከቱ የሚገኙ የኮሌጁ ምሩቃን በማዕከል ለማሰባሰብ ጥረት ተደርጓል፡፡
• በየአመቱ ጥቅምት ወር ላይ በሦስት ጊዜያት ጠቅላላ የአባላት ጉባኤ ለማካሄድ ተችሏል፤
• በጠለቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ቋሚ ቢሮ እንዲሰጠን አውንታዊ ምላሽ በማግኘት በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡
• የንብረትና የገንዘብ ብክነት እንዳይከሰትና በአባላቱ መካከልም አለመተማመን እንዳይጠር ለንብረትና ለገንዘብ መሰብሰቢያ ሕጋዊ ደረሰኝ በማህበሩ ስም ማሳተም ተችሏል፡፡
• ከማህበሩ አባላት መካከል በተደረገ የማስተባበር ሥራ አንዲት በጎ አድራጊ 4 ኮምፒዩተር ከነ ፕሪንተሩ ለኮሌጁ በእርዳታ መስገኘት ተችሏል
• ለማኅበሩ አባላት ቋሚ የመታወቂያ ካርድ እንዲኖራቸው ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
• የኮሌጁ የ71 ዓመት የማስተማርና የመማር ታሪካዊ ጉዞ የሚዳስስና የተለያዩ ሊቃውንት የተሳተፉበት “ኆኅተ ብርሃን” በሚል ስያሜ በልዩ ህትመት የተዘጋጀው መጽሔት በዛሬው በዓል ለማቅረብ ተችሏል፡፡
• የኮሌጁን የረጅም ጊዜ ጉዞ አጠቃሎ የያዘ ዶክመንተሪ ፊልም በዲ/ን የማነ ዘመንፈስ አዘጋጅነት በዚሁ በዓል ቀርቦ እንዲመረቅ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በዲ/ን የማነ ዘመንፈስ በዚህ ጉባኤ ፊት ታላቅ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
2. የማህበሩ የወደፊት ዓላማና ራዕይን በሚመለከት፡-
• በዋናነት ኮሌጃችን በተፈለገው የግብ ደረጃ ላይ ለማድረስ የእውቀት፣ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እገዛ ማድረግ፤
• በኮሌጁ ውስጥ በመማር ላይ ለሚገኙ ደቀመዛሙርት እና ለመምህራኑ ሞራላዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግ፤
• የቅዱስ ቤተክርስቲያናችንን ዶግማና ቅኖና በጠበቀ መልኩ እስከ ጠረፏ ቤተክርስቲያን ድረስ ከምን ጊዜውም በላይ በስፋት እና በፍጥነት ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስ ምሩቃኑን ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፤
• በቤተክርስቲያኗ ማእከላዊነት በሚዘጋጁ ታላላቅ ጉባኤያት ላይ በስብከተ ወንጌል እና በዝማሬ የሚያገለግሉ መምህራንን ማሠማራት፤
• ስብከተ ወንጌልን በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በኤሌክትሪኒክስ ሕትመት በሚዘጋጁ የትምህርት ውጤቶች በተገልጋዩ ክፍል በስፋት እንደዳረስ ማድረግ፤
• ቅድስት ቤተክርስቲያናችንንና መንጋዎቿን ለመንጠቅ በልዩ ልዩ የመናፍቅነት እና ክህደት ሴራቸው የሚፈታተኗረትን አጽራረ ቤተክርስቲያን ወቅቱ በሚጠይቀው መንፈሳዊ ጥበብ መከላከል፤
• የብሉያቱ፣ የሐዲሳቱ እና የሊቃውንቱ ትርጓሜ፣ የዜማው፣ የአቋቋሙ፣ የቅኔውና የቅዳሴው ምንጭ የሆኑትን የአብነት ት/ቤቶች ለማጠናከር እና ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ሙያዊና ኢኮኖሚያዊ እገዛ ማድረግ፤
• በየጠረፉ አገልጋይ ካህናትና ነዋየ ቅድሳት አጥተው የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናትን በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ለመርዳት ጥረት ይደረጋል፡፡
• ከቤት እስከ ሆስፒታል ድረስ በልዩ ልዩ ደዌ ለሚሰቃዩ ሕሙማንን መንፈሳዊ የምክር አገልግሎት በመስጠትና ልዩ ልዩ እገዛ በማድረግ እናጽናናለን፤
• ኮሌጃችን ለቤተክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት እና የደም ስር መሆኑን መንፈሳዊ ቅናት ላደረባቸው በጎ አድራጊዎች በማሳወቅ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን በኮሌጁ ግቢ ለማከናወን ከኮሌጁ አስተዳደር ጋር በጋራ መንቀሳቀስ፡፡
• ቤተክርስቲያኗን አስተምሮ የጠበቀ ቋሚ መጽሔት በማህበሩ ሰም በየጊዜው እያሳተሙ ለአንባቢያን ማሰራጨት፡
• ከሌሎቹ የኮሌጅ ምሩቃን ማሕበር ጋር በጋራ ዓላማችን ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ግንኙነትን መፍጠር፡፡
• በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ኮሌጅ ምሩቃን በማሰባሰብ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡና በማእከልም እየተሰባሰቡ ማህበሩን እንዲያጠናክሩ ማስቻል፤
• በውጪው ዓለም ከሚገኙ የኮሌጁ ምሩቃን ጋርም የኢሜል፣ የኢንተርኔት፣የስልክ ግንኙነት በመዘርጋት በገንዘብና በማቴሪያል በሐሳብም ጭምር አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፡፡
• ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን ተቆርቋሪ የሆኑትን በጎ አድራጊ ምሁራንንና ባለሀብቶችን ዓላማውን በጥልቅ በማሳወቅ ለኮሌጁ ሙያዊ እና የኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስቻል፡፡
• የብዘ ሊቃውንት ስብስብ የሆነውን ይህንን የምሩቃን አንድነት ጉባኤ በገንዘብ፣ እውቀት፣ በማቴሪያልና በመሳሰለው ሁሉ በስፖንሰርነት ሊያግዙ የሚችሉ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ማፈላለግ፤
• እንግዲህ ማህበራችን እግዚአብሔር ቢፈቅድና ቢረዳን ከዚህ በላይ የዘረዘርናቸውንና እነዚህን የመሰሉትን ሁሉ ለማከናወን ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ከወዲሁ አበክረን ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡
ማጠቃለያ፡-
ብፁዕ ወቅዱ አባታችን፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ክቡራን እንግዶቻችን!! በመጨረሻው የመደምደሚያ ሐሳባችን ላይ ልናሰምርበት የምንፈልገው ይህ የማህበራችን አንድነት ጉባኤ በበጎ ፈቃደኝነትና ልባዊ በሆነ፣ መንፈሳዊ ወንድማማችነት የተመሠረት ከመሆኑ በላይ 9 ብፁዓን አባቶችን ጨምሮ የብዙ ሊቃውንት ስብስብ ስለሆነ በቤተክርስያናችን የሚሰጠው ጠቀሚታ እጅግ የጎላ ነው ብለን እናምናለን፡፡ አንድነት ጉባኤያችን ዓላማ፣ ራእይና ተልእኮ ኖሮት የሚንቀሳቀስ ከመሆኑም ባሻገር ለቤተክርቲያኗ የቁርጥ ቀን ልጆቿ የሆኑ ምሁራን አንድ የሆኑበት ስብስብ ስለሆነ ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ሥርዓቷን እና ታሪኳን ጠብቆ የሚያስጠብቅ መሆኑን እና ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ቅዱስ አባታችን እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኙት የቤተክርስቲያኗ ተቋማት የሚተላለፈውን የሥራ መመሪያ በፀጋ ተቀብሎ የሚጓዝ እና ከምንም በላይ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ልማታዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ግንባር ቀደም ሆኖ የራሱን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለመፈጸም እና ለማስፈጸም ተግቶ የሚሠራ መሆኑ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው፡፡
በቅዱስ ወንጌል “ማዕረሩሰ ብዙሕ ወገባሩኒ ሕዳጥ ተሰአልዎ ለባዕለ ማዕረር ከመ ይወስክ ገባረ” ማቴ.9÷37 ተብሎ እንደተጻፈው፡፡ በዚህ ዘመን የቤተክርስቲያኗ አገልግሎት እጅግ ሰፊ ሆኖ ሳለ አገልጋዮቹ ደግሞ ጥቂት በመሆናቸው በዚህ ዘመን ምንደኛ ያልሆኑ እና ራሳቸውን ብቻ የማያሰማሩ ትጉህ እረኞች ለቤተክርስቲያናችን እንደሚያስፈልጓት ለአባቶቻችን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡
እውነቱን ለመናገር ይህ የምሩቃን ማሕበር የሊቃውንት ስብስብ እንደመሆኑም መጠን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መደበኛውን የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት በማስቀደም ታማኝ ሐዋርያ ሆኖ የጎደለውን በመሙላት፣ የጠመመውን በማቅናት፣ አባጣ ጎባጣውን በማስተካከል ያለውን አእምሮታዊ እና አካላዊ አቅሙን አስተባብሮ ሌት ተቀን ለማገልገል እና ለመታዘዝ ቁርጠኝነቱን በቅዱስ አባታችን እና በዚህ ታላቅ ጉባኤ ፊት ያረጋግጣሉ፡፡
ስለሆነም ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ተብሎ እንደተጻፈ የጉባኤያችን ሕብረት እንደማንኛውም ኮሌጅ የድኅረ ምረቃ ስብሰባ መሆኑ ታውቆ አብዛኛዎቹ ምሩቃን በቤተክርስቲያኗ በታላላቅ ኃላፊነት ያሉ ከመሆናቸው አኳያ ለኮሌጃችን የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ እና ተዋቂነቱም ይበልጥ ለማጉላት እንጂ ሌላ ሥጋዊ ሀብት ለማካበት ማሕበራዊ ጥቅም ለመፍጠር አለመሆኑን ሊሠመርበት ይገባል፡፡
በመጨረሻም ከላይ በግልጽ ለማሳየት የሞከርናቸውም ዓላማችን፣ ራዕያችንና ተልእኮአችን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን እንችል ዘንድ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ጸሎና አባታዊ የሥራ መመሪያ፣ የብፁዓን አባቶቻችን ምክርና ተግሳጽ፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ የክብር እንግዶቻችን ሁላችሁም በቀጣይነት ለምናከናወነው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሞራል፣ የሐሳብ፣ የሙያ፣ የገንዘብ፣ የማቴሪያል እና የመሳሰለው ድጋፋችሁ እንዳይለየን ከምስጋና ጋር ጥያቄያችንን እያስቀደምን ሪፖርታችንን በዚህ እናጠናቅቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
“ለዘአፈጸመነ ዛተ ዓመተ” የሰዋስዎ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን አንድነት ጉባኤ ግንቦት 10 ቀን 2006 ዓ.ም
{flike}{plusone}