ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያናችንን የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት የሙከራ ስርጭት ባርከው ከፈቱ

0164

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
‹‹አማን አማን እብለክሙ ዘይሰምዕ ቃልየ ወየአምን በዘፈነወኒ ይረክብ ሕይወተ ዘለዓለም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሄድም›› (ዮሐ. 5፡24)
በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ!
የመልካም ስጦታ ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በእርሱ ቅዱስ ፈቃድ ቃሉን በዚህ ሚድያ በምልአት ለመስማት ስላበቃን ክብርና ምስጋና፣ አምልኮትና ስግደት ለእርሱ ይሁን፡፡
እናንተም ለረጅም ጊዜ በጉጉት ስትጠባበቁት የነበረውን የታላቋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ እግዚአብሔር ለፍጡራን በሰጠው አእምሮ በተሠራ በዚህ መገናኛ ብዙኃን ለመስማት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ!!
የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በላይ ነው፤ ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩትና ጸንተው የቆሙት በእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ዘላለማዊ እንደመሆኑ ሕያው ነው፤ ፍጡራንም በእርሱ ሕይወትነት ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሰዎች ከፍርድ ነጻ ሆነው የዘለዓለምን ይሕወት የሚያገኙ ይህንን ቃል በመመገብ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የሆነ ሕይወት ሊኖር አይችልምና ፡፡
ይህ እውነት የታወቀውና ሊታወቅ የሚችለው በእግዚአብሔር መገለጥ ብቻ ነው፤ የእግዚአብሔር መገለጥ በሦስት ነገሮች ታይቶአል፤ ይኸውም፡-
1.እግዚአብሔር በፍጥረቱ አማካይነት ተገልጦአል፤
2.በመረጣቸው ቅዱስን ሰዎች አማካይነት ተገልጦአል፤
3.ሰው ሆኖ በመገለጥ ራሱን ለዓለም ገልጦአል ፡፡
ከዚህ አንጻር የክርስትና ሃይማኖት መሠረትና መነሻ የእግዚአብሔር መገለጥ እንጂ ፍልስፍና፣ ወይም ሌላ አመክንዮ አለመሆኑን እዚህ ላይ ማስተዋል ያስፈልጋል ፡፡
ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚና ዓቢይ ተልእኮ በእርሱ የተገለጠውና የማይለወጠውን ሕያው ቃል ለዓለም ሁሉ ማድረስ እንጂ በየጊዜው የሚለዋወጠውን፣ በሕፀፅ የተሞላውና የሰዎች ቁሳዊ መላምት የሆነውን ጥበበ ሰብእ አይደለም፤ በተለይም ኢትዮጵያ ሀገራችን፤
-ቀደም ሲል በሕገ ልቡና (በሕገ ተፈጥሮ)
-ቀጥሎም በሕገ ኦሪት (በቅዱሳን ነቢያት በኩል)
-በኋላም በሕገ ወንጌል (በሥግው ቃል) የሆነውን የእግዚአብሔር መገለጥ መሠረት አድርጋ ከብዙ ዘመናት በፊት አምልኮተ እግዚአብሔርን የተቀበለች ሀገር ናት፤ ይህ ሃይማኖታዊ እውነታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ለዘመናት ተጠብቆ የኖረ፣ ያለና የሚኖር እንደሆነ ከቃሉ በተጨማሪ ታሪካችንና ቅዱሱ ባሕላችን በግልፅ እየመሰከሩት የሚገኝ እውነት ነው ፡፡
ታላቋና ገናናዋ ቤተ ክርስቲያናችን ከብዙ ተጋድሎ ጋር ለረጅም ዘመናት ጠብቃ ያቆየችውን ነገረ ሃይማኖት ዛሬም ባለበት ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለማስፋፋት የዘመኑ መሣሪያ መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ጥርጥር የለውም ፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን ያልደረሰችበት ክፍለ ዓለም የለምና በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኙ ልጆችዋ ሁሉ በእርስዋ በኩል በቀጥታ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔር ቃል በምልአት ያዳምጡና ይሰሙ ዘንድ እነሆ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በሰሜን አሜሪካና በላቲን አሜሪካ ያሉትን ምእመናን ሁሉ ሊያዳርስ የሚችል ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት›› እውን አድርጋለች ፡፡
ይህ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗ ልዕልና መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ምእመናን ሁሉ ድጋፋቸውን በመስጠት ወደከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድጉት፣ ሊንከባከቡትና እንደ ዓይን ብሌን ሊጠብቁት ይገባል፤ ጣቢያው የምእመናን ድጋፍ ከታከለበት ሃያ ዐራት ሰዓት በሙሉ መጠቀም የሚያስችል ቻናል እንደሆነም ከወዲሁ መግለፅ እንወዳለን ፡፡
በዚህ ሚድያ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዓተ አምልኮን፣ ደማቁ የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክን ስትማሩ ኢትዮጵያንም እዚያው ታገኙአታላችሁ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ ናቸውና በአንድ ወንጭፍ እንደሚባለው ስለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትማሩ ስለ ኢትዮጵያም የግድ ትማራላችሁ ማለት ነው ፡፡
በመጨረሻም፤
ቤተ ክርስቲያናችን ከሌላው ሥራ ሁሉ ለሚድያ አገልግሎት ቅድሚያ መስጠቷ አዋቂውም ሆነ ወጣቱ ትውልድ ስለሃይማኖቱና ስለታሪኩ፣ ስለሀገሩና ስለማንነቱ፣ ስለባህሉና ስለትውፊቱ ማወቅ የሚገባውን አውቆ የባለቤትነትና የታሪክ ጠባቂነት ኃላፊነትን እንዲሸከም በማድረግ፣ በዚህች ሀገር ሃይማኖታዊ ሰብእና ያለውን ጤናማ ማኅብረሰብ ለመገንባት ታስቦ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል ፡፡
ስለሆነም ሁላችሁም ምእመናን ወምእመናት በተለይም ወጣቶች ትምህርተ ቤተ ክርስቲያናችሁን በንቃት እንድትከታተሉ፤ ድጋፋችሁንም አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አደራ ጭምር አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እያስተላለፍን፤ ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት ሙከራ በይፋ የተጀመረ መሆኑን እናበስራለን ፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ