ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2010 ዓ.ም ጾመ አርባአን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ፣ መሐሪና ይቅር ባይ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት የጾመ ኢየሱስ ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ!!
ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ ጾምን ለዩ ምህላንም አውጁ፣ (ኢዩ 2፤15)
ሁሉን ያስገኘ ፣ ሁሉንም ባርኮ ለፍጥረቱ ያደለ ፣ የምሕረትና የበረከት አምላክ እግዚአብሔር፣ ለፍጥረቱ ምግብ የሚሆን ፍሬ በረከትን በየዓይነቱ በምልአት እንደሰጠ ዓይናችን ያያል፣ እጃችን ይዳስሳል፣ ኅሊናችንም ያውቃል፡፡ እግዚአብሔር ተንቀሳቃሽ የሆኑትን ሕያዋን ፍጥረታት ወደ ህልውና ከማምጣቱ በፊት ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በገጸ ምድር ፣ በከርሠ ምድር፣ በዐውደ ምድርና በጠፈረ ሰማይ አስቀድሞ ፈጥሮአል ፤ እግዚአብሔር ሕያዋን ፍጥረታትን በምድር ላይ ከፈጠረ በኋላ ለፍጥረታቱ እነሆ ይህንን ሁሉ ሰጥቻችኋለሁ ፣ ብሉ፣ ብሎ ባርኮ ሰጥቶአቸዋል፣ ከዚህም ጋር መጥኖ መመገብ፣ የሚጠቅመውንና የማይጠ ቅመውን ለይቶ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳው ቆአል ፡፡
ይሁን እንጂ ፍጡራን በተለይም ሰዎች ይህንን ትእዛዘ እግዚአብሔር ባለመጠበቃቸው ለውድቀት መዳረጋቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ እግር የተፈጠረው ለመራመድ ነው ተብሎ በገደልና በባህር በእግር መራመድ እንደማይቻል ሁሉ ሆድ የተፈጠረው ለመብላት ነው ብሎ ሁሉን፣ አግበስብሶ መብላት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚበልጥ በስካር፣ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በመቃምና በማጤስ በተሸነፉ ወገኖች የሚታየው የሕይወት ምስቅልቅልና የኢኮኖሚ መቃወስ አፍ አውጥቶ የሚመሰክር ማስረጃ ነው፤ ሰው ይቅርና እንስሳት እንኳ ከመጠን በላይ ከተመገቡ ብዙ ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ በሌላም ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ያደርሳሉ፤ በመሆኑም ሰዎች ከጉዳት፣ ከስሕተትና ከውድቀት ይድኑ ዘንድ የማይጠቅመውን መተው፣ የሚጠቅመውንም መጥኖ መመገብ አስፈላጊ መሆኑ ከማንም የተሠወረ አይደለም፣ ለዚህም ተመራጩ ዘዴ ጾምን መጾም እንደሆነ በተግባር የሚታይ ነው፤ መጥኖ መመገብ ሰውን ወደ ትዕግሥት፣ ወደ ማስተዋል፣ ወደ ዕለታዊ የግልተግባር፣ወደመቻቻል፣ ወደርኅራኄ፣ ወደ ሰላምና ወደ ፍቅር፣ ፈጣሪንና ሕጉን ወደማሰብ ይገፋፋል፣ ሰው መጥኖ በተመገበና በጠጣ ቊጥር በብዙ መልኩ ከግብረ ኃጢአት ባርነት ነጻ የመውጣት ዕድሉ ሰፊ ነው፣ በተጨማሪም መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃይልን ከፍ የማድረጉ ጉዳይ፣ እንደዚሁም ጤንነቱን ከበሽታ የመከላከል ዓቅም ከፍ እንደሚል የጤና ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፤ ስለሆነም ጾም ከሃይማኖታዊ ጥቅሙ ባሻገር ለሰው ልጅ የተሟላ ጤንነት ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ እንደሆነ እናስተ ውላለን፡፡
ጌታችንም በመዋዕለ ጾሙ ያስተማረን ይኸው ነው፤ እሱ ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት ጹሞ በተራበ ጊዜ ፈታኙ ጠላት በተለመደ መሣሪያው በምግብ በማስጎምጀት ሊፈትነው ሲሞክር ከፍ ባለ ሞራላዊና መንፈሳዊ አቋም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ብሎ ሐሳቡን ውድቅ በማድረግ አሳፍሮ መልሶታል፡፡ ጌታችን በዚህ አምላካዊ ትምህርቱ ዲያብሎስንና የጥፋት መሠሪያዎቹን ሁሉ መመከት የሚቻለው በምግብ ኃይል ሳይሆን በጾም ኃይል መሆኑን በተግባርም በትምህርትም አሳይቶናል ፡፡
ከዚህም የተነሣ ክርስቶሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ከክርስቶስ ባገኘችው ትምህርት የጾም ወቅቶችን ለይታ ጸሎተ ምህላን በማድረስ ፣ መጥኖ በመመገብ ፣ ለግብረ ኃጢአት የሚያነ ሣሡና ወደጥፋት የሚገፋፉ ምግቦችን በመተው፣ ጾምን፣ ጸሎትን፣ምህላን፣ ምፅዋትን፣ ምሕረትን ፣ ይቅርታን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን ፣ መደበኛ ተግባር አድርጋ ሰባቱን አጽዋማት በየዓመቱ ትጾማለች ፤ በዚህም ወደፈጣሪዋ ወደ እግዚአብሔር በምታቀርበው ጸሎት ፣ አምልኮና ስግደት የእግዚ አብሔር በረከትና ጥበቃ እየታደጋት በአንድነትዋ፣ በነጻነትዋና በገናናነትዋ ጸንታ ለሦስት ሺሕ ዘመናት ዘልቃለች ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ወርኃ ጾም መንፈሳዊ ኃይላችንን የምናጎ ለብትበት፣የፈቃደ ሥጋ ውጤቶች የሆኑ ጥልን፣ መለያየትን፣ የርስ በርስ መጠራጠርን የምናደክምበት፣ብሎም መንግለን የምንጥልበት፣ በአንጻሩም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ይቅር ይቅር መባባልን፣ አርቆ ማየትን የምንለማመድበት፣ ስለጥቃቅን ጊዜያዊ ችግሮች ሳይሆን፣ ስለሃይማኖትና ስለሀገራዊ ዘላቂ ጥቅሞች አብዝተን የምናስብበትና መፍትሔ የምናበጅበት ጊዜ ነው፤ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችን አንድነት ፈተና፣ ለሕዝባችን ልማትና ብልፅግና እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተከሠቱ ብዙ ወገኖች ሀብታቸው፣ ንብረታቸው ከሁሉ በላይ ደግሞ መተኪያ የሌለው ሕይወታቸው ጉዳት እየደረሰበት ነው፤ እንደዚህ ያለው ድርጊት የክርስቶስ ወንጌለ ሰላም ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያለመቋረጥ በተሰበከባት በኢትዮጵያ ምድር መከሠቱ ከሃይማኖታችን ዕድሜ ጠገብ ጸጋ ጋር የማይሄድ ነው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ አሳዛኝ ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለ በራስ ወገን ላይ መሆኑ እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡ እየጎዳም ያለው ራሳችንን ነው፤ የሚወድመው ንብረትም፣ የሚጠፋው ሕይወትም የእኛው የራሳችን ነው ፤ እነዚህ ጎጂ ድርጊቶች በፍጥነት ካላረምናቸው ባለፉት የሰላምና የልማት ዓመታት የታዩት ተስፋዎች እንደገና እንዲጨልሙና የኋልዮሽ እንድንጓዝ የሚያደርጉን አደገኛ አዝማሚያዎች ናቸው፣
በመሆኑም መላው ሕዝባችን በተለይም ወጣት ልጆቻችን በዚህ ቅዱስ ወርኃ ጾም ወደ ልባችሁ መለስ በሉና ነገሮችን በአርቆ አስተዋይነትና አእምሮን በማስፋት ተመልከቷቸው፣ እየተከሠቱ ያሉ ስሕተቶች የምንወዳት ኢትዮጵያን ይጎዱ እንደሆነ እንጂ በምንም ተአምር አይጠቅሟትም ፤ ስለሆነም የችግሩን ጉዳት በማገናዘብ በየአካባቢው ያላችሁ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በአጠቃላይ፣ ሕዝባችን ተደጋጋሚ ስሕተቶችን በመፈጸም ወገንንና ሀገርን እንዳይጎዳ በዚህ ቅዱስ የጾም ወቅት የሰላም አጀንዳን ዕለታዊ ሥራ አድርጋችሁ ወጣቱን ትውልድና ሕዝቡን እንድትመክሩ፣ እንድታስተምሩ ቤተክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ስም ጥሪዋንታስተ ላልፋለች፡፡
በ መ ጨ ረ ሻ ም
መላ ኢትዮጵያውያን በተለይም ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህ ጾም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ወይም የተለየ ጊዜ እንደመሆኑ መጠን የተራበውን በማጉረስ፣የተራቆተውን በማልበስ፣ የተጠማውን በማረስረስ፣ በኅብረተሰቡ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልንና ይቅር ይቅር መባባልን በማንገሥ፣ጾሙን ልዩ የይቅርታ ጊዜ አድርገን እንድንቀበለውና እንድንጾመው፣ ካህናቱም ስለ ሀገር አንድነትና ስለሕዝብ ሰላም እያሰባችሁ በየቤ ተክርስቲያኑ ጸሎቱንና ምህላውን በኃዘን ወደ እግዚአብሔር እንድታቀርቡ አባታዊ መልእክ ታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር የይቅርታ ጾም ያድርግልን
የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ያጽናልን
‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር››
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ