ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2010 ዓ.ም ዘመን መለወጫን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

pp009

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወዐሠርቱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•በአገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
•ከአገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ
•የአገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
•በሕመም ምክንያት በየጠበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
•እንደዚሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችሁ በየማረሚያ ቤተ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የዘመናትና የፍጥረታት ፈጣሪ የኾነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማርቆስ ሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት በሰላም አደረሳችሁ፡፡
“አንሶስዉ እንዘ ብክሙ ብርሃን፤ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” (ዮሐ. ፲፪፥፴፭)
የብርሃን ጸጋ ለሰው ልጆች ወይም በአጠቃላይ ለፍጥረታት ዅሉ ከተሰጠው የእግዚአብሔር ስጦታዎች ትልቁ ነው፤ ብርሃን የሥራ መሣሪያ ነው፤ ብርሃን የመልካም ነገር ሁሉ ተምሳሌት ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ በባሕርዩ ብርሃን ከመኾኑም ሌላ በእርሱ ዘንድ የማይጠፋ ብርሃን እንዳለ በቅዱስ መጽሐፍ ተገልጿል፡፡ የሰው ልጅ ከወዲያ ወዲህ፣ ከወዲህ ወዲያ ተንቀሳቅሶ፣ ነግዶ፣ አርሶ፣ ሠርቶ፣ ተምሮና አስተምሮ ለኑሮው የሚያስፈልገውን ዅሉ ለማግኘት ብርሃን የግድ ያስፈልጋል፡፡
ከዚኽም ጋር ሙሉ ጤና፣ ቀና የኾነ አእምሮ፣ ሰላምና ፍቅር ለሰው ልጅ ብልጽግና ወሳኝ ቦታ አላቸው፡፡ እነዚህ በሰው ልጅ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ላይ ያላቸው ጸጋ እጅግ የላቀ በመኾኑ በቅዱስ መጽሐፍ አገላለጽ ብርሃን እየተባሉ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደዚሁም ዕድሜና መልካም ዘመን በተመሳሳይ አገላለጽ ብርሃን ተብሎ ይመሠጠራል፡፡ ምክንያቱም ብርሃን በሌለበት ኹኔታ ምንም ሥራ መሥራት እንደማይቻል ሰላማዊ ዘመን ከሌለም ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ አይቻልማና ነው፡፡ በመኾኑም ዕድሜና ዘመንም ሌላው ታላቁ የእግዚአብሔር ብርሃን ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” ሲል የዕድሜና የጊዜ ብርሃንነትን ማመልከቱ እንደ ኾነ ዐውደ ምንባቡ በግልጽ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም እርሱ በዚኽ ዓለም በመምህርነት የተገለጸበት ዘመን ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ በነበረበት ጊዜ የተናገረው ከመኾኑ ጋር ባለችው አጭር ጊዜ የትምህርት ዕድሜ ወይም ዘመን ሰዎች በእርሱ ብርሃንነት እንዲያም የቀሰቀሰበትና ያስተማረበት ትምህርት ነው፡፡ በእርግጥም ላስተዋለውና በሥራ ለተጠቀመበት ጊዜ ታላቁ ብርሃን ነው፡፡ ጊዜ ሲቀና ነገሩ ዅሉ ብርሃን ይኾናል፡፡ ጊዜው ከጨለመ ደግሞ ዙሪያው ዅሉ ጨለማ ይኾናል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት
ዕድሜያችን ወይም ዘመናችን በሕይወታችን ውስጥ ለልማትም ኾነ ለጥፋት፣ ለጽድቅም ኾነ ለኀጢአት፣ ለትንሣኤም ኾነ ለውድቀት መሣሪያነቱ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ዅሉም የሚሠራውና የሚከናወነው በጊዜው ነውና፡፡ በዘመናት ውስጥ ብርሃናውያን የኾኑ ዓመታት እንደ ነበሩ ዅሉ ጽልመታውያን የኾኑ ዓመታትም በአገራችንም ኾነ በሌላው ዓለም እንደ ነበሩ እናውቃለን፡፡ እነዚኽ ተቃራኒ የኾኑ ነገሮች በየፊናቸው ለሰው ልጆች ያተረፉት ስጦታም በስማቸው ልክ እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ ይኹን እንጂ ዘመናትን ብርሃውያን ወይም ጽልመታውያን እንዲኾኑ በማድረግ ረገድ የሰው ልጅ ሚና ትልቅ እንደኾነ የማይካድ ነው፡፡
የሰው ልጅ የማስተዋልና የመቻቻል፣ የመታገሥና የመወያየት፣ የፍቅርና የስምምነት፣ የሰላምና አንድነት ጠቃሚነትን ዘንግቶ በስሜትና በወቅታዊ ትኩሳት፣ እንደዚሁም እግዚአብሔርን የሰላም ድምፅ አልሰማ ብሎ በራስ ወዳድነትና በስግብግብነት ተሸንፎ ወደ ትርምስ ሲገባ ዘመኑ ጽልመታዊ መኾኑ አይቀሬ ነው፡፡ በሰው ችኩልና ደካማ አስተሳሰብ የተጨናነቀ ጽልመታዊ ዘመን ከውድመትና ከጥፋት በቀር አንዳችም ትርፍ እንደሌለው ከአገራችን ተሞክሮ የበለጠ መምህር አይኖርም፡፡
በሌላ በኩል ሰዎች ከእርስ በርስ ግጭት ተላቀው ሰላምንና ፍቅርን፣ አንድትንና እኩልነትን፣ መቻቻልንና መስማማትን፣ መወያየትንና መቀራረብን፣ ወንድማማችነትንና መከባበርን ያረጋገጠ፣ ትዕግሥትና አስተዋይነት የማይለየው የእግዚአብሔርን ድምፅ በመከተልና አእምሮን በማስፋት መኖር ሲጀምሩ ዘመኑ ብርሃናዊ እንደሚኾን፣ ልማቱና ዕድገቱም እንደሚፈጥንና እንደሚረጋገጥ አሁንም በአገራችን ወቅታዊ ተሞክሮ ተረድተዋል፡፡ ይኽ ዅሉ እውነታ የሚያሳየው የዘመን ብርሃንነትና ጽልመትነት የሚወሰነው እኛ ሰዎች በምናውጠነጥነው አስተሳሰብና በምናደርገው እንቅስቃሴ እንደ ኾነ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ለዚኽም ነው ሓላፊነቱም ተመልሶ ወደ እኛ የሚመጣው፡፡
ጌታችንም ምርጫውንና ውሳኔውን ለእኛ ትቶ “ብርሃን ስላላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” በማለት ገለጻውንና ትምህርቱን ብቻ መናገሩ ከዚህ የተነሣ እንደ ኾነ ማስተዋል ይገባል፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ የሚሻለንን መምረጥና መከተል የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ምርጫችን ሰላምና አንድነት ከኾነ ዘመኑ ብርሃን ነው፤ ተቃራኒው ከኾነ ደግሞ የኋልዮሽ ጉዞ ይኾናል፡፡ ስለ ኾነም ምርጫችን ሰላምና አንድነት እንዲኾን ዅላችንም ተስማምተን መወሰን አለብን፡፡
ማንም ሰው ብርሃንና ጨለማ ጎን ለጎን ቀርበውለት የትኛውን ትመርጣለህ የሚል ጥያቄ ቢቀርብለት ያለማመንታት ብርሃኑን እንደሚመርጥ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ችግሩ ሰዎች ይህን ግልጽና ጠቃሚ ምርጫ ተቀብለው ተጠቃሚ እንዳይኾኑ ብዙ የሚያታልሉና በድብብቆሽ የሚመላለሱ አካላት በመካከሉ ይገቡና ጨለማውን ብርሃን፣ ብርሃኑንም ጨለማ አስመስለው ሰውን ወደ ገደል መክተታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብርሃናዊና መልካም የኾነ ምርጫችንን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያድርጉታል፡፡ እኛ ሰዎች አእምሯችንን በሚገባ መጠቀም ያለብን እዚኽ ላይ ነው፡፡ ማለትም እኛው ራሳችን የሚጠቅመንና የማይጠቅመንን የመለየት ዓቅም ስላለን ዓቅማችንን ተጠቅመን ለዘላቂ ጥቅማችንና ለትክክለኛ ምርጫችን መወገን ይኖርብናል ማለት ነው፡፡
ሰዎች የኾን ዅላችን ባለ አእምሮዎች ኾነን ተፈጥረናል፡፡ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያመሳስለን ስለ ኾነ ከሀብት ዅሉ የበለጠ ሀብት ነው፡፡ ይህንን አእምሯችንን ካዳመጥነውና ከተከተልነው ሐቁን አይስትም፡፡ አመዛዝኖ፣ ገምግሞ፣ ለክቶ ጠቃሚውን ነገር ከልባችን ውስጥ ቁጭ ያደርግልናል፡፡ ነገር ግን ትዕግሥትን፣ ማገናዘብን፣ ቆም ብሎ ማሰላለሰልን፣ ምክንያታዊ መኾንን፣ ማመዛዘንን፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን፣ ፈቃደ እግዚአብሔርን መከተልን ይፈልጋልና እነዚኽን እንደ ግብአት አድርገን ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ይህንን መጠቀም ስንችል የዘመናችንና የዕሜያችን ብርሃን ዋስትና ይኖረዋል፡፡ ጨለማም አያሸንፈውም፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት
ለዐሥር ዓመታት ያህል የተጓዝንበት የሦስተኛው ሺሕ ወይም ሚሊኒየም ዓቢይ ዘመን ለኢትዮጵያ አገራችን ብርሃናዊ ዘመን የፈነጠቀበት ወቅት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያልተነካ ሀብታችን እርሱም የዓባይ ወንዝ ሀብታችንን ለመቋደስ የሚያስችል ግዙፍ የልማት ሥራ ተጀምሮ ወደ መጠናቀቅ እየተቃረበ ያለበት እጅግ ብርሃናዊ ዘመን በመኾኑ ነው፡፡
በሠለጠነው የምዕራቡ ዓለም ካልኾነ በቀር በአፍሪካ ምድር ለዚያውም በድርቅ፣ በረኃብና በጦርነት ትታወቅ በነበረችው ኢትዮጵያ ይኾናሉ ተብለው የማይታሰቡ እጅግ ግዙፍ የኾኑና የሕዝባችንን መሠረታዊ የዕድገት ለውጥ የሚያረጋግጡ የኮንስትራክሽንና የኢንዱስትሪ፣ የትምህርትና የጤና ተቅዋማት በፍጥነት እየገሠገሡ መገኘት በዚህ ብርሃናዊ ዘመን የዕለት ተዕት ትእይንት እንደ ኾኑ በዓይን እየታየ ነው፡፡ ይኽ ጸጋ እንዲሁ ያለ መሥዋዕትነት የተገኘ ሳይኾን እኛ ኢትዮጵያውያን ከዅሉ በላይ ሰላምንና ልማትን መርጠን በአንድነት ወደ ብርሃናዊ አስተሳሰብ ስለ ገባን ነው፡፡ እግዚአብሔርም “በብርሃን ተመላሱ” ያለው ይኽን ለማመልከት ነውና በዚህ ምክንያት ትክክለኛ ምርጫችንን እርሱ ስለባረከልን የልማትና የዕድገት ተምሳሌት መኾን እንደቻልን አንስተውም፡፡
ዛሬም ወደማንወደውና ወደማንመርጠው ጨለማ ሊከቱን የሚሹ እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ እንደዚሁም በሕዝባችን መካከል መለያየትና መቃቃር ሊያስከትሉ የሚችሉ አፍራሽ ድርጊቶች ብቅ ብቅ በማለት እየተፈታተኑን እንደ ኾኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ እነዚኽ ዅሉ በተግባር ያየናቸው የሕዝባችን ቀንደኛ ፀርና የጨለማ አበጋዞች፣ የልማታችንና የሰላማችን ዕንቅፋቶች ናቸውና ሕዝቡ በተለመደው ሃይማኖታዊና አርቆ ማሰብ ኀይሉ እንዲመክታቸው በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም
የዛሬ ዐሥር ዓመት “ታላቅ ነበርን ታላቅም እንኾናለን” በማለት ለሦስተኛው ሺሕ ወይም ሚሊኒየም ዓቢይ ክፍለ ዘመን የገባነውን ቃል በማደስ በአዲሱ ዓመት ካለፈው ዓመት በበለጠ ጠንክረን በመሥራት፣ ልማታችንንና ዕድገታችንን በፍጥነት በማሳደግ፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን ባለን የተሞክሮ አሠራር በመመከት፣ እንደዚሁም ሕገ ወጥ ዝውውርን፣ አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ድርጊትን በማክሸፍ፣ በሃይማኖትና በሰላም መርሕ በመመራት አዲሱን ዘመን ብርሃናዊ እንድናደርገው መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
አዲሱን ዘመን የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፩ ቀን ፳፻ወ፲ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ