ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2009 ዓ.ም ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ዘዕሥራ ምዕት ወተስዐቱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
+ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ!!
+ እኛን ለክብርና ለምስጋና የፈጠረ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የጾመ ማርያም ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች ” (ሉቃ ፩ ÷ ፵፯ )
ይህንን የምስጋና ቃል የተናገረችው ወላዲተ እግዚአብሔር ቃልና ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን የአምልኮ ምስጋና ለእግዚአብሔር ስታቀርብ እርሱ ያደረገላትን ሦስት ዓበይት ምክንያቶች በመጥቀስ እንደሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ እናስተውላለን፡፡
እመቤታችን ይህንን ምስጋና ከማቅረቧ በፊት እግዚአብሔር ለታላቅ በረከትና ለፍጹም ደስታ እንደመረጣት፣ የእርሱ ባለሟልና ምልእተ ጸጋ እንዳደረጋት፣ ቅዱሱን የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ እንደምትወልድና እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር እንደሆነ በመልእክተኛ በቅዱስ ገብርኤል በኩል ነግሮአታል፡፡
እርሷም በቅዱስ ገብርኤል በኩል የተላከላትን የእግዚአብሔር ቃል ተቀብላ እነሆ የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ እንዳልከኝ ይሁንልኝ በማለት በታዛዥነትና በትሕትና ለደረሳት መለኮታዊ ጥሪ ተገቢውን የይሁንታ መልስ ሰጥታለች፡፡
በዚህ ጊዜ ቀዳማዊ ወልደ እግዚአብሔር በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ራሱን በማዋሐድ የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀንዋ አደረ፡፡
ጌታችን አምላካዊ ማንነቱን መግለጽ የጀመረው ከማኅፀን አንሥቶ ነውና እመቤታችን እሱን ፀንሳ ሳለች ኤልሳቤጥን እንዴት ነሽ ብላ የሰላምታ ድምፅን ስታሰማት በማኅፀነ ኤልሳቤጥ ያለው ፅንስ በማኅፀነ ማርያም ላለው ፅንስ በደስታ ሰግዶአል፡፡
ይህ አምላካዊ ምሥጢር በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ያለው ፅንስ የአምልኮ ስግደት የሚገባውና ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉንም ማድረግ የሚችል የባህርይ አምላክ መሆኑን አሳይቶአል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም የቅድስት ድንግል ማርያም የሰላምታ ድምፅ በኤልሳቤጥ ጆሮ በተሰማ ጊዜ በማኅፀንዋ ያለ ፅንስ በደስታ ሲሰግድ፣ በዚያ ቅፅበት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እግዚአብሔር በቅዱስ ገብርኤል በኩል የገለፀውን የእመቤታችን ክብርና ጸጋ፣ በረከትና ብፅዕና፣ የጌታ እናትነትና ባለሟልነት፣ የልጇ በረከትና አምላክነት በኤልሳቤጥ አንደበትም በድጋሚ እንዲነገር ማድረጉ የነገሩ ክብደትና ታላቅነት ምን ያህል እንደሆነ እንዲታወቅ አስችሎአል፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ ገብርኤልና በቅድስት ኤልሳቤጥ በኩል ስለ እርስዋ መናገሩና የእግዚአብሔር ወልድ በማኅፀኗ ማደሩ በዚህ ሁሉ እጅግ በጣም ከኃይል ሁሉ የበለጠ ታላቅ ኃይል በእርስዋ ላይ እንደተደረገ እመቤታችን በሚገባ አውቃለች፡፡
ይህ እጅግ በጣም ታላቅ የሆነ ጸጋ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚተርፍ ልዩ በረከትና የእግዚአብሔር የማዳን ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ለማመልከትም ካንቺ የሚወለደው ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ስለሆነ ስሙ ኢየሱስ ትይዋለሽ ተብሎ በመልአኩ ተነግሮአታል፤ እርስዋም አምና ተቀብላለች፤
ለዚህ ታላቅ በረከትና መዳን በመሣሪያነት እርሷ መመረጥዋንም ልዩ ዕድል መሆኑን አልዘነጋችም፡፡
እንግዲህ እነዚህ ዓበይት ነገሮች በእመቤታችን አእምሮ ውሰጥ ከፍተኛ ስፍራ ነበራቸውና ያለ ምስጋና ልታልፋቸው አልፈለገችም፡፡
በመሆኑም የሆነው ነገር በሙሉ ለእርስዋና ለሰው ልጆች ሁሉ መሆኑን በሚገልጽ ኃይለ ቃል የአምልኮ ምስጋናዋን ለፈጣሪዋ ለእግዚአብሔር ግሩም በሆነ ሁኔታ አቅርባለች፡፡
በምስጋናዋም “ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬና በመድኃኒቴ ደስ ይላታል፤ የባርያይቱን ውርደት አይቶአልና፤ እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል፤ እርሱ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና” የሚል ጥልቅ ምሥጢር ያለው ኃይለ ቃል ይገኝበታል፡፡
ይኸውም “ብዙኃ አበዝኆ ለሕማምኪ ወለፃዕርኪ፤ በሕማም ለዲ፤ ምጥሽን ጣርሽን እጅግ አበዛዋለሁ፤ በጭንቅም ትወልጂያለሽ የሚል መርገም ተሸክማ በመከራ የኖረችውና ይህንን መከራ ለልጆችዋ ያወረሰችው ሔዋን በእርስዋ ጊዜና መሣሪያነት ከመርገም ተላቃ ወደ ገነት የምትመለስበት ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱን ስታመለክት የባርያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች በማለት አመሰገነች፡፡
የሰው ልጅን በአጠቃላይ ከገጠመው ውድቀት ለመታደግ እግዚአብሔር በጀመረው ነገረ አድኅኖ ከኃይል ሁሉ የበለጠ ኃይል እግዚአብሔር ወልድ በማኅፀኗ ማደሩ፣ እንደዚህም እርስዋ ለዚህ የበቃች ቅድስት፣ ንጽሕት፣ ቡርክት፣ ልዕልት፣ ብፅዕትና ከሴቶች ሁሉ የተለየች ምልእተ ጸጋ፣ ሙኃዘ ፍሥሐ፣ የእግዚአብሔር ልዩ ባለሟልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አድርጎ መምረጡንና ማክበሩን ሁሉ ለእርስዋ የተደረጉ ታላላቅ ነገሮች መሆናቸውን በመገንዘብዋ እመቤታችን ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና መንፈሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ደስ ይላታል በማለት ፈጣሪዋን አመስግናለች፡፡
ከዚህም አይይዛ በእግዚአብሔር መልእክተኛ በቅዱስ ገብርኤልና መንፈስ ቅዱስ በሞላባት በቅድስት ኤልሳቤጥ የተገለፀውን ቅድስናዋና ብፅዕናዋ ዘመንና የስሑታን ትምህርት ሳይገቱት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይቋረጥ እንደ ወራጅ ውሀ እስከ ዕለተ ምጽአት እንደሚነገርና እንደሚተገበር በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታ ተናግራለች፤
ቤተ ክርስቲያናችንም የእመቤታችንን ብፅዕና አክባሪና ከአማላጅነቷ ተጠቀሚ ሆና መገኝቷ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በደምብ ያወቀችና ቃሉን በምልአት የተቀበለች መሆኗን ያረጋግጣል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ከቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና ቃል የምንማረው ብዙ ትምህርት እንዳለ ማስተዋልና መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ከሁሉ በፊት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩ ነገሮች በሙሉ ከፍጡራን መንጭተው የተነገሩ ሳይሆኑ ከእግዚአብሔር በቀጥታ ከተላከው መልአክ ከቅዱስ ገብርኤል፣ መንፈስ ቅዱስ ከሞላባት ከቅድስት ኤልሳቤጥና እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል ከተባለላት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩ በመሆናቸው ምንጫቸውና ተናጋሪያቸው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ መገንዘቡ አያዳግትም፤
ምክንያቱም ተላኪ የላኪውን፣ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት የመንፈስ ቅዱስን ቃል እንደሚናገር ለሁሉም ግልጽ ነውና፤ ቅዱስ መጽሐፍም እነዚህን በጥንቃቄ መዝግቦ መገኘቱ ይህንን እንድንገነዘበው ብሎ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡
ከዚህ አንጻር እግዚአብሔር ራሱ በፍጹም ክብር ያከበራትንና ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ እያሉ እንዲያመሰግኗት በቅዱስ መንፈሱ ያናገረላትን ቅድስት ደንግል ማርያምን ማክበርና ማመስገን፣ ብፅዕናዋንና ቅድስናዋን ማመን፣ መስበክና ማሰተማር የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ተረድቶ ለቃሉ መታዘዝና ለተግባራዊነቱ መቆም እንደሆነ ለሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ላደረገላት ታላቅ ነገር ሁሉ ምስጋናን አምልኮትንና ምስክርነትን በመስጠት ለእኛ መልካም አስተማሪና አርአያ መሆኗን ማስተዋል ከሁላችንም ይጠበቃል ፡፡
ሁላችንም ልብ ብለን ካየነው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ታላላቅ ሥራዎችን ያልሠራበት ቀን አይገኝም፤ ነገር ግን በየጊዜው ለሠራልን ሥራዎች ተገቢ ዕውቅና በመስጠትና በመመስከር እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም በደስታ የአምልኮ ምስጋናን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ስንት ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ብናነሣ መልሱ አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፤
ነገር ግን ድሮም የተፈጠርነው ለምስጋና ነውና እግዚአብሔር ያለሟቋረጥ ሁሌም ታላላቅ ነገሮችን እየሠራልን እንደሆነ አውቀንና አምነን ለእርሱ የሚገባ የአምልኮ ምስጋና ልናቀርብ ይገባል፡፡
ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በቀኖና ጸድቆ በጥንታውያንና በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እየተፈጸመ የሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ዓላማም፣ እግዚአብሔርን በምስጋና በቅዳሴ በውዳሴ ለማምለክ፣ ለቅዱስ ቃሉ ፍጹም ታዛዥ በመሆን ምሥጢረ ቊርባንን ለመቀበልና ከኃጢአት ሸክም ተላቀን ከእግዚብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔር ሞገስና ጸጋ አግኝተው ለቅድስና ደረጃ የበቁ ቅዱሳን ሁሉ ጸሎታቸውና፣ ተማኅጽኖአቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለዓለሙ ሁሉ እንደሚተርፍ ቅዱስ መጽሐፍ በትምህርትም ሆነ በተግባር ያረጋገጠውና የመዘገበው ነው፡፡
ይልቁንም “እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና ምልእተ ጸጋ ነሽ፤ደስ ይበልሽ ብሎ እግዚአብሔር በመልእክተኛው ያረጋገጠላት ቅድስት ድንግል ማርያም ባላት ከፍተኛ የእግዚአብሔር ባለሟልነት በጸሎቷ በአማላጅነቷና ወደ እግዚአብሔር በምታቀርበው ተማኅፅኖ ግዳጃችንን እንደምትፈጽም የቃና ዘገሊላው ምልጃዋና የተገኘው በረከት በቂ ማስረጃችን ነው፡፡
በመሆኑም የጾመ ፍልሰታ ሱባዔ እግዚአብሔርን በአባትነት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን በእናትነት የምናገኝበት ልዩ ወቅት በመሆኑ እግዚአብሔር በቃሉ የተናገረውን በመከተልና እንደ ቃሉ በመመላለስ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍቅርና ሰላም፣ መተጋገዝና መረዳዳት፣ ንሥሐና ጸሎት፣ ቅዱስ ቊርባንን መቀበልና ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን በማዳመጥና በመከተል መጾም ይኖርብናል፡፡
ይህ ጾም የሀገራችንን አንድነትና ነጻነት፣ የሕዝባችንን አብሮነትና የእርስ በርስ መተሳሰብ፣ እግዚአብሔርን የመፍራትና ድንግል ማርያምን የመውደድ፣ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን ሁሉ አዳብሮ ጥሩ ሰብእና ያለው ማኅበረ ሰብን ያፈራ፣ እንደ አሸንዳ የመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ባህሎችን የገነባ ጾም ስለሆነ፣ ለሃይማኖታችን መጠበቅ፣ ለሀገራችን መልካም ገጽታ ግንባታና ለልማት መፋጠን እንደዚሁም ለቱሪዝም ክፍለ አኮኖሚ መበልፀግ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ስለሆነ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሀገራዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
በመጨረሻም
የጾም ወቅት ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት፣ ርኅራኄና አዘኔታ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚያደርጉበት እንደመሆኑ መጠን፣ ምእመናን እጆቻቸውን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲዘረጉ፣ ስለ ሀገርና ስለ ዓለም ሁሉ ሰላም መጠበቅ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት እንዲያቀርቡ፣ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ዙሪያ መለስ የልማትና የዕድገት ሽግግር እንዲሠምር በፍቅርና በሰላም ቆመው በአንድነት ጸሎታቸውን ሁሉን ወደሚችል ወደ ኃያሉ እግዚአብሔር ለማቅረብ እንዲተጉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናሰተላልፋለን፡፡
ወትረ ድንግል ማርያም
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻ወ፱ዓ.ም.