የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የ2009 ዓ.ም በሰባቱ ክፍላተ ከተማ ዓመታዊ የሥራ ግምገማ አካሄደ

a0017

ሀገረ ስብከቱ ከሰባቱ ክፍላተ  ከተማ ቤተ  ክህነት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር  በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተከናወኑትን የልማትና የፐርሰንት ገቢ አስመልክቶ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ባደረገው አጠቃላይ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ የተመሠረተ የምክክርና የመገማገም ሥራ  አከናውኗል፡፡
ሀገረ  ስብከቱ  በዚሁ ወር መግቢያ  በፐርሰንት  አሰባሰብ ዙሪያ  ሰፋ  ያለ  ውይይት  እና  ግምገማ ያካሄደ መሆኑ  ይታወቃል፡፡ በሰባቱም  ክፍላተ ከተማ  በየተራ  ከአድባራትና ገዳማት የሥራ ኃላፊዎችና  ሠራተኞች ጋር   ለሙሉ ቀን የቆየ  የምክክር እና  ግምገማ  ጉባኤ  አካሂዷል፡፡
በሁሉም ክፍላተ ከተማ በተደረገው  ዐቢይ  የምክክር እና የመገማገም  ጉባኤ የተነሱ ሀሳቦችን በተመለከተ  በአሠሪና  ሠራተኛ መካከል የሚፈጠረው  ችግር፣ የስብከተ  ወንጌል እንቅስቃሴ  መዳከም፣ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታ ጉዳይ፣ የፐርሰንት  ክፍያ፣ የህገ ወጥ  ሰባክያን  የአድማ ቅስቀሳ፣ የምዕመናን ቁጥር  መቀነስ እና የመናፍቃን ወረራ ተግባር በዋናነት  የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህን ዘርፈ ብዙ  ችግሮች  ለማስወገድ አሠራሮችን ማስተካከል  ይገባናል  ብለዋል፡፡ የጉባኤያቱ  ዋና መሪና አስተባበሪ የሆኑት መምህር  ጎይቶም  ያይኑ በሰጡት  ሐሳብ ሕገ ወጥ  ሰባኪያን  በዐውደ ምህረት ቆሞ ለመስበክ በመጀመሪያ ፈቃድ ሊኖረው  ይገባል፡፡
የቤተ ክርስቲያን አባል ያልሆኑ እና የቤተ ክርስቲያን ተቆርቆሪ  ያልሆኑ ሰዎች  ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፤ በቲፎዞ ምክንያት ጠቃሚ የሆኑ  ሰዎችን  እያጣን  ስለሆነ  ይህንን አሠራር  መፈተሽ  አለብን፤ አደገኛ  የሆነ  አስተሳሰብ  እየመጣ ነው፡፡ ከሕዝብ  ተለይተው  ብቻቸውን  የሚኖሩ  አሉ፤ ብዙ  ተከታይ ካፈሩ በኋላ ከመድረክ ቢወርዱም  በሕዝብ  ልብ  ውስጥ ጠልቀው ገብተዋልና በእንቃሴያቸው ዙሪያ ሊታሰብበት  ይገባል፡፡
ስለምዕመናን ቁጥር መቀነስ በተለያየ መልኩ ይነሳ  እንጂ ምን ያህል ቁጥር እንደቀነሰ በትክክል ማወቅ  ይገባል፡፡ በአሠራር ብልሽት  እና በኢኮኖሚ ጫና ያጣናቸው ሰዎች ሊኖሩ  ይችላሉ፡፡ በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው የሚያስረክቡ ምዕመናንም አሉ፡፡
በአጠቃላይ ስንመለከት  ግን ሥራችንን  በአግባቡ  መሥራት አለብን፡፡ የሚጠበቅብንን የሥራ ድርሻ መወጣት  አለብን፡፡ ሐሳባችን  የጥቅም ጉዳይ አይሁን፡፡ በአግባቡ  ሠርተን  በአግባቡ ልንጠቀም  እንችላለን፡፡ የቤተክርስቲያን ገንዘብ  በአግባቡ  ገብቶ  በአግባቡ መውጣት አለበት፡፡  ስለምንሠራው ሥራ አስቀድሞ  መረጃ  ሊኖረን  ይገባናል፡፡
ለሥራው የሚመጥን ሠራተኛ ከሥራው ጋር ማገናኘት አለብን፡፡ ስለ ውሉ  ስለጨረታው  በቁርጠኝነት መሥራት አለብን፡፡ ሁላችንም  በአንድ ልብ  መሥራት  ካልቻለን  መሪው  ብቻውን የሚያመጣው  ለውጥ የለም፡፡ ሕዝቡና ካህናቱ ችግር  አለ እያሉ እየጮሁ የሚቀርበው ሪፖርት  ግን  ከዚህ  የተለየ ሊሆን አይገባም፡፡
የገዘፈ ችግር ካለ እርምጃ መውሰድ የግድ ነው፡፡ አለቃም ሆነ ጸሐፊ የገዘፈ ችግር  ካለባቸው ወደታች አውርዶ ማሠራት የግድ ነው፡፡ በቀረበው ሪፖርት መሠረት የተቀጣ ሰው በጥፋቴ ነው ብሎ ሊፀፀት ይገባዋል፡፡ ሠራተኛው በአንድ ቦታ ችግር ሲፈጥር ወደሌላው ቦታ  ይዛወራል፡፡ ይህ ግን  መፍትሔ  ሊሆን አይችልም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ችግር ሊፈታ የሚችለው በሰበካ  ጉባኤ ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤ  ሊጠናከር ይገባዋል  በወገንተኝነት  የሚሠራ  የሕዝብ  ተወካይ ሊኖር አይገባም፡፡ በምዝገባ ጊዜ ክትትል ሊደረግ ይገባል፡፡ በካርድ ስለተመረጠ ትክክለኛ ኮሚቴ ተመረጠ ማለት አይደለም፡፡ በየዓጥቢያው የተሟላ የሰበካ ጉባኤ አባል መኖር አለበት፡፡
የተመረጡት  የሰበካ ጉባኤ አባላትም መብታቸውንና ግዴታቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ለወደፊቱ ከሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር የመመካከር እና የውይይት ተግባር  ያካሂዳል  በየክፍላተ ከተሞች  ባደረግነው  የምክክርና  የመገማገም ጉባኤ እንደተረዳነው በሰበካ  ጉባኤው እና በካህናት መካከል  ተግባብቶ መሥራት  አይታይም፡፡ በአብዛኛው  አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ  የሰበካ  ጉባኤ አባላት  የአገልገሎት  ዘመናቸውን ሲጨርሱ ተመስግነው አይወርዱም፡፡
ይህም የሚያሳየው ያሳለፉት የሥራ ዘመን ባለመግባባት ስለሚሰራ ነው፡፡  በአንድ አንድ አበያተ ክርስቲያናት ከሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር የሚፈጠረው  ችግር  የቤተ ክርስቲያን  ሀብት  ከመጠበቅ አንጻር ነው፡፡ ይህ አይነት የምክክርና የመገማገም ሥራ በየስድስት ወራት ሊቀጥል  ይችላል በማለት መምህር  ጎይቶም ያይኑ መልእክታቸውን  ካስተላለፉ በኋላ ለሙሉ ቀን ያህል ሲካሄድ የዋለው የምክክር እና የመገማገም ጉባኤ ባለ26 ነጥብ የአቋም መግለጫ  እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የአቋም መገልጫ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት  በ2009 ዓ.ም  የበጀት ዓመት  በየክፍላተ  ከተማ ቤተ ክህነት  በበጀት ዘመን ሲከናወኑ የቆዩትን ተግባራት በየክፍለ ከተማው ሲገመግም ከቆየ በኋላ    የዓመቱን ማጠቃለያ በአዲስ አበባ  ሀገረ  ስብከት  ዋና ሥራ  አስኪያጅ  በመምህር  ጎይቶም  ያይኑ  ሰብሳቢነት በክፍለ ከተማ  ቤተ ክህነት  ሥራ አስኪያጅ  የቢሮ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በሙሉ  በየክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የቀረበውን  ሪፖርት  በማዳመጥ እጅግ  ጥቅልና  አመርቂ ውይይት  ከተደረገ በኀላ  የሚከተለውን የጋራ  የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1.በየክፍላተ ከተማው አድባራትና  ገዳማት ሲደረግ የነበረው ውይይት አመርቂና ውጤታማ  በመሆኑ  ቀጣይነት  እንዲኖረው አስፋላጊውን  ትብብር እናደርጋለን፡፡
2.ከሪፖርቱ በቀረበው መሠረት ጠንካራ ጎን በመውሰድ ለቀጣይ ዓመት  የበለጠ እንዲሠራ አስፋላጊውን እንቅስቃሴ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
3.ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ ያሉት እንቅስቃሴዎች መልካም ቢሆኑም ወቅቱን የጠበቀና ሀገረ ስብከቱ በሚያስተላልፈው መመሪያ ተመርኩዘን  ካለፈው በተሻለ  እንቅስቃሴ እንዲደረግ  ተግተን  እንሠራለን፡፡
4.ትምህርት ወንጌል ከቤተ ክርስቲያን፣ ከከፍለ ከተማውና ከሀገረ ስብከቱ ዕውቅና  ውጪ የሚንቀሳቀስውን አካል በተመለከተ ክትትል ተደርጎ ትክክለኛ አስተምህሮ እንዲሰፍን  ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
5.ሰበካ ጉባኤን በሚመለከት ሀገረ ስብከቱ ያስተላለፈው መመሪያ እንዲከናወን መደረጉ አግባብና ውጤት ያለው በመሆኑ በቀጣዩም ተጠናክሮ እንዲቀጥልተግተን እንቀጥልበታለን፡፡
6.ተመራጭ  የሰበካ ጉባኤ አባላት ከተመረጡ  በኋላ  ስልጠና  እየተሰጣቸው ወደ ሥራ  እንዲገቡ  ለማድረግ  ተግተን  እንሠራለን፡፡
7.የልማት ሥራን  በተመለከተ የሚታዩት ጅምሮች፣ በጎ ቢሆኑም ግልጽነት ባለው አሠራርና በጨረታ ሂደቱም  በጥንቃቄ  እንዲከናወን ሕጉን ጠብቆ እንዲሠራ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
8.በበዓላት የሚገኙ ገቢዎችንና ንዋየተ ቅድሳት በሚመለከት  ከሀገረ ስብከቱ  በሚወጣው  መመሪያ  መሠረተ  የጨረታ ሂደቱን፣  የሙዳየ ምጽዋት  ቆጠራውን  በሕጉ መሰረት  እንዲከናወን  ለማድረግ  ቃል እንገባለን፡፡
9.ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ በመጣችበት የታሪክ ጉዞዋ  ሁሉ ምሰሶ በመሆን  ለዛሬ ያበቁዋት  ሊቃውንት አግባባዊ ክብር  እንዲሰጣቸው ለማድረግ ቃል  እንገባለን፡፡
10.ቤተ ክርስቲያን በቱሪስት መስህብ ልታገኝ የሚገባትን ገቢ ከፍ ያለ እንዲሆን ለማድረግ ቃል  እንገባለን፡፡
11.የ2009 ዓ.ም  የበጀት ዘመን የገቢው አሰባሰብ የተሳካ እንዲሆን ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ  የተሰጠውን ስልትና መመሪያ በመከተል ከወትሮው  በተለየ መልኩ  የተገኘው  ለውጥ  እጅግ ከፍተኛ  በመሆኑ  በሚቀጥለው  የ2010 ዓመተ  ምህረት  የበጀት ዓመት  በተሻለ አሠራር  ለመቀጠል ቃል እንገባለን፡፡
12.ካህናቱ የንሰሀ ልጆቻቸውን በትምህርተ ሃይማኖት  የሚይዙበትን ስልት  በመቀየስ አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ  ለማድረግ ተግተን እንሠራለን፡፡
13.የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ትምህርት እየተኮተኮቱ እንዲያድጉ  የእዝ ሰንሰሉትን በመጠበቅ ከማኅበራትም ጫና እንዲላቀቁ በማድረግ እና ተጠናከሮ  እንዲቀጥሉ  ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
14.በሀገረ ስብከቱ ተጀምሮ ሲሠራ የቆየው ስልጠና ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩላችንን ጥረት አናደርጋለን፡፡
15.የሚተከሉት አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ከተሠሩ በኀላ እንዳይፈርሱ አስፋላጊውን ጥንቃቄ በማድረግና ከሚመለከተው አካላት ጋር በመነጋገር ተፈጻሚነት እንዲአገኝ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
16.የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ካርታ ያላገኙ አድባራትንና ገዳማትን  ካርታ  እንዲያገኙ እና በጥቅምተ ባህር  የማደሪያ ይዞታዎች እንዲከበሩ  ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
17.በቤተ ክርስቲያን ስም በመደራጃት በፉካና በጉዞ ማኅበራት የተሰማሩ አካላት ቤተ ክርስቲያን ማግኘት  የሚገባትን ገቢ ሳይሰጡ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ ስለሆነ ይህ ድርጊት ለወደፊቱ በቤተክርስቱያኑ ብቻ እንዲሠራ ለማድረግ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
18.በዘንድሮው የበጀት ዘመን  ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ዕድገቱ እንዲመዘገብ ያደረገው  የሀገረ  ስብከቱና የየክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ያላሳለሰ  የሥራ  ክትትል በመሆኑ የሠራተኛው ደመወዝና ጥቅማቸውም እንዲስተካከል ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል  በአክብሮት  እንጠይቃለን፡፡
19.የክፍላተ ከተማ ቤተ ክሀነተ  አሁን ባለው አካሄድ እየተጠቀሙበት ያለው ቢሮ የሀገረ ስብከቱን ወጪ እያስወጣ በመሆኑ የራሳችንን ቢሮ ለማሠራት የበለጠ ተግተን እንሠራለን፡፡
20.ያለበጀት ከሥራ ማስኬጃና ከደመወዝ ውጪ በልዩ ልዩ ምክንያት  የሚወጣው ወጪ  የቤተ ክርስቲያናችን ኢኮኖሚ  በእጅጉ እየጎዳው በመሆኑ በፀደቀው  በጀት ብቻ እንዲመራ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
21.በወርኃዊና ዓመታዊ ክብረ  በዓላት  ላይ  ማንንም ሳያስፈቅዱ  በወንጌል አገልገሎት በቅዳሴ ጊዜ በየመግቢያው ላይ ልዩ ልዩ ሸቀጣሸቀጦችን በማቅርብ ወከባ በሚፈጥሩት ወገኖች ላይ  አስፋላጊውን ቁጥጥር ተደርጎ እንዲወገዱ ለማድረግ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡
22.ከቤተ ክርስቲያኗ ወጥተው እየሄዱ ያሉ  ምስጢራትን ከመጠበቅ አኳያ ምዕመናንን  በመጠበቅ ጉዳይ ላይ  ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን፡፡
23.የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ  በማጠቃለያ ንግግራቸው በአዲስ አበባ  የተፈጠረው የመደማመጥ፣ የመረጋጋትና ፍትሐዊ አስተዳደር ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ሥር ነቀል  ለውጥ ለማምጣት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
24.ምዕመናን ስለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ስለሆነ የተሻለ ሥራ  በመሥራት በንሰሀ  አባቶቻቸው አማካኝነት  ትምህርቱ እንዲሰጣቸውና የምዕመናን ቁጥር ምን ያህል እንደደረሰ አስፋላጊውን አቅጣጫ ለመቀየስ ቃል እንገባለን፡፡
25.በበጀት ዓመቱ  የተከናወኑ አበይት  ተግባራት እጅግ በጣም የሚበረታቱ መሆናቸውን በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ በየክፍላተ ከተሞች የተደረገውን ውይይት የዛሬውን አጠቃላይ የሥራ ግመገማና ውይይት እያደነቅን ቀጣይነት እንዲኖራቸው እያሳሰብን ሌት ተቀን ተግተን ለመስራት ቃል እንገባለን፡፡