ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2009 ዓ.ም ዓቢይ ጾምን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

pp009

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በአተ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ወተስዐቱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በሀገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ
ፍጥረቱን በምሕረት፣ በይቅርታና በርኅራኄ የሚጠብቅ፣ የሚመግብና የሚያስተዳድር፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ኃያሉ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት መዋዕለ ጾም ዓቢይ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፣ ወኢይትኃፈር ገጽክሙ፤ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችኋልም፤ ፊታችሁም አያፍርም”፡፡ (መዝ 34፡5)
የሰው ልጅ ከዐራቱ ባህርያተ ፍጥረት በተገኘ ሥጋዊ ሕይወቱ፣ የዐራቱ ባሕርያት ውጤት የሆኑትን ማለትም እህልን ውሀን፣ ነፋስንና እሳትን የመሻት ፍላጎቱ የላቀ እንደሆነ ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር በተገኘ መንፈሳዊ ሕይወቱም እግዚአብሔርን የመሻት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፤
ከእግዚአብሔር የተገኘው ይህ ሀብተ ተፈጥሮ ከሰው ባህርይ መለየት የማይቻል በመሆኑ ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ከፈጣሪው ጋር ግንኙነት ለማድረግ ይጓጓል፡፡
ሰው ወደ ፈጣሪው ለመቅረብ ከሚፈልገው በላይ፣ ፈጣሪም ሰውን በእጅጉ ሊቀርበውና ማደርያው ሊያደርገው ይፈልጋል፤ በመሆኑም ሁለቱም ተፈላላጊ መሆናቸውን በሕገ ተፈጥሮም ሆነ በቅዱስ መጽሐፍ የታወቀ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ሁለቱም እንዳይቀራረቡ የሚያደርጉ መሠረታውያን ነገሮች እንዳሉ ሁሉ እንዲቀራረቡ የሚያደርጓቸውም አሉ፤ ሁለቱንም ሊያቀራርቡ ከሚችሉት መካከል አንዱ ጾም ነው፡፡
እግዚአብሔር በሁለመናው ንጹሕ ቅዱስ ፍጹምና ክቡር በመሆኑ ለባህርዩ ከማይስማሙ ድርጊቶችና ከአድራጊዎቻቸው ጋር ግንኙነት ሊያደርግ አይፈቅድም፤
ሆኖም ንሥሐ ሲገቡና ጥፋታቸውን አምነው ሲፀፀቱ በይቅርታ የሚቀበል ርኅሩኅ መሐሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው፤
ከዚህ አኳያ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ብሎም ለመዝጋት ንሥሐ ጾምና ጸሎት ቊልፍ መሣሪዎች ናቸው፤ እኛ ክርስቲያኖችም ጾምን የምንጾምበት ዋና ምክንያት ይኸው ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ መንፈሳዊ ኃይል ያስፈልጋል፤ መንፈሳዊ ኃይል የሚገኘው ደግሞ ሥጋዊ ኃይል ሲገታ ነው፡፡ ጾም ይህንን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ጾም ኃይለ ሥጋን በመግራት ኃይለ መንፈስ እንዲበረታ  ያደርጋል፣ ጾም ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለእግዚአብሔር እንድንገዛና ለቃሉ ታዛዥ እንድንሆን ያስችለናል፤ ጾም ሰከን ብለን ስለበደላችን እንድናስብና ለንሥሐ እንድንፈጥን ያደርገናል፣ ጾም የእግዚአብሔርን ቸርነት በማሰብ ፍቅሩን እንድናውቅና እንድናመልከው፣ ለሰውም ጥሩ የሆነውን ብቻ እንድናስብ ያደርገናል፡፡
እነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ሥርፀት ሲያገኙ ወደ እግዚአብሔር የመቅረቡና የመገናኘቱ ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ሆነን ስለምንሻው ነገር እግዚአብሔርን ብንጠይቅ መልሱ ፈጣን ይሆናል፤ ከዚህ አንጻር የነነዌ ጾም ያስገኘው ፈጣን መልስ ማስረጃችን ነው፤ በጾም ኃይል አማካኝነት ከፈጣሪ ጋር የተገናኙ እነ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራም በዚህ ተጠቃሽ መምህሮቻችን ናቸው፡፡
ርኩስ መንፈስን ድል ለማድረግ፣ ሊጀመር የታሰበውን ዓቢይ ተግባር በስኬት ለማጠናቀቅ በጾም ረድኤተ እግዚአብሔርን መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገባርና በትምህርት አሳይቶናል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህንን በተግባርና በትምህርት ፈጽመውታል፤ ከዚህ አኳያ ጾምና ሃይማኖት የማይለያዩ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
በመሆኑም ጾም ራሳችንን ለመቆጣጠር፣ የእግዚአብሔር ታዛዥ ለመሆን፤ ለጥያቄአችን ፈጣን መልስ ለማግኘት፤ ርኩስ መንፈስን ድል ለማድረግ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚያገለግለን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት
የጾም አስፈላጊነትና ውጤታማነት ከጥንት ጀምሮ በነቢያትና በሐዋርያት የታወቀ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ “በፍጹም ልባችሁ፣ በጾም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፣ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤ ቁጣው የዘገየ ምሕረቱ የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ፤ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ (ለዩ) ጉባኤውንም አውጁ፤ ሕዝቡንም አከማቹ፤ ማኅበሩንም ቀድሱ” ብሎ ጾምን በአዋጅ እንድንጾም አዞናል፤(ኢዩ 2፡12-18)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ርኩስ መንፈስ ሊሸነፍና ድል ሊሆን የሚችለው በጾምና በጸሎት እንደሆነ አስረግጦ አስተምሮናል፤(ማቴ 17 ፡ 14-21)
ይሁንና ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋም፣ መልስም፣ ኃይልም ሊያሰጥ የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማለትም እግዚአብሔር ባዘዘው ትእዛዝ መሠረት ሲከናወን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም እንዴት ያለ እንደሆነ እርሱ ራሱ እንዲህ ብሎናል “እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እሥራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፣ የተገፉትን አርነት ትሰዱ ዘንድ፣ ቀንበሩን ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን ? እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፣ ስደተኞቹ ድሆችን ወደቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቆተውን ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ያበራል ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር በላይህ ሆኖ ይጠብቅሃል” ብሎ ፈቃዱን ነግሮናል፡፡ (ኢሳ 58 ፡ 6-8)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
የጾም ዓቢይ ዓላማ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝና የተሰበረን ልብ መፍጠር፣ በጾም በጸሎት በንሥሐ በስግደት በተመሰጦ፣ በአንቃዕድዎ ለእርሱ መታዘዝና መገዛት እርሱንም ማምለክ ነው፡፡
ከዚህም ጋር ጥልን በይቅርታ ማስወገድ፣ ሰላምን በማረጋገጥ ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ማድረግ፣ ራስን መቆጣጠርና መግዛት፣ ኃይለ ሥጋን መመከት፣ ኃይለ ነፍስን ማጎልበት፣  የእግዚአብሔርን እንጂ የሰውን አለማየት፣ የርኩሳን መናፍስትን ግፊት በመቋቋም ክፉ ምኞትን ድል ማድረግ፣ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል፤ ኅሊናን ለእግዚአብሔር መስጠት፣ ያለንን ለነዳያን ከፍለን መመፅወት የመሳሰሉትን ሁሉ ዕለታዊ ተግባራችን በማድረግ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡
በመጨረሻም
የጾም ዋና ዓላማ ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደ መሆኑ መጠን ምድርን እንድናበጃትና እንድናለማት ያዘዘንን ትእዛዝ ተቀብለን አካቢያችንን በማልማት ሀገራችንን ውብና ለኑሮ የተመቸች በማድረግ እንደዚሁም ከኃጢአት መከላከያዎች መካከል ዋናውና አንዱ ያለ ዕረፍት በሥራ መጠመድ ነውና ሕዝቡ ሥራ ሳይፈታ ፈጣሪውን በጾም እያመለከ፣ የተቸገረ ወገኑን ካለው ከፍሎ እየረዳ፣ ልማትንም እያፋጠነ የሀገሩን ሰላምና ፀጥታ እየጠበቀ መዋዕለ ጾሙን እንዲያሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻ወ፱ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ