የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አቀረቡ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰባቱ የክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤቶች የ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ ዕቅድን አስመልክተው የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ እና የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተገኙበት ረቡዕ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም ለግማሽ ቀን የቆየ የሥራ ዕቅድ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የ2009 ዓ.ም ባቀረቡት የሥራ ዕቅድ መሠረት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከመንግሥት ተቋማት፣ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር በተለያዩ አስተዳደራዊና ልማታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ለመሥራት፣ የአገልግሎት ጊዜአቸውን ያጠናቀቁ የሰበካ ጉባኤ አባላትን በአዳዲስ አባላት ለመተካት፣ ከገዳማትና አድባራት የሚሰበሰበውን የፐርሰንት ገቢ ከፍ ለማድረግ፣ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ ፈቃድ የሌላቸውን ሰባኪያነ ወንጌል በመቆጣጠር፣ የአንድነት ጉባኤያትን ለማጠናከር የሰንበት ት/ቤቶችን ለማስፋፋትና ገቢአቸውን ለመቆጣጠርና ዕድሜአቸው ከ30 ዓመት ያለፋቸውን ወጣቶች ወደምዕመናን ህብረት ለማምጣት፣ የምግባረ ሰናይ ሥራዎችን ለማከናወን ልማትን ለማጠናከር፣ ህፃናትና አዛውንቶች የሚረዱበትን መንገድ ለማመቻቸት ቅፅ ሀና ቅፅ ለ በተባሉት ሰነዶች ላይ አስፈላጊውን መጠይቅ ለመመዝገብ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር፣ በመዘምርነት መደብ የተቀጠሩ የአብነት መምህራን የማስተማር ሥራቸውን የሚአከናውኑበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት በሚሉት ሐሳቦች ዙሪያ ቀጣይ የሥራ ዕቅድ ቀርቧል፡፡
በቀረቡትም ዝርዝር የሥራ ዕቅዶች ዙሪያ የሀገረ ስብከቱን የሥራ እንቅስቃሴ ወደተሻለ ዕድገት ለማሸጋገር፣ ሁሉም በተሰጠው ሀላፊነት መሠረት ጠንክሮ መሥራት አለበት፣ በሥራ ዕቅዱ ውስጥ ተጨማሪ አዳዲስ አማኞች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ለማድረግ፣ የሚቀርቡት ዝርዝር የሥራ ዕቅዶች ተተንትነውና ተብራርተው እንዲቀርቡ በማለት ሰፋ ያለ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
በመቀጠልም የሀገረ ስብከቱ የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀትጉኃን ታጋይ ታደለ ባቀረቡት የእቅድ አዘገጃጀት ሪፖርትና ማንዋል የዕቅድ መግለጫዎች እቅዱ በዘፈቀደ የማይዘጋጅ መሆኑን፣ የዕቅድ አፈጻጸም፣ የዕቅድ አይነቶች፣ የረጅም የመካከለኛና የአጭር ጊዜ እቅድን በሀብት ቅደም ተከተል ማስቀመጥ የሪፖርት አዘገጃጀት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም፣ የገቢና የወጪ ዕቅድ እና የመሳሰሉትን በዝርዝር ለተሰብሳቢው አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባስተላለፉት መልእክት በተመደብንበት የሥራ ዘርፍ መሥራታችን ፣መውጣት፣ መውረዳችን እና መድከማችን ካልቀረ ሥራችንን አቅደን መሥራት ይገባናል፡፡ ፐርሰንት ስናስከፍል አስተምረንና አሳምነን ማስከፈል አለብን፡፡ ዕቅዳችን በወረቀት ላይ የሰፈረና የተለካ መሆን አለበት፡፡ ይህን አቅደናል፣ ይህን እንሠራለን ብለን ካቀድን የማስፈጸሚያ በጀት የማግኘት ዕድል አለን፡፡ ከነበረው አሠራር ወደተሻለ የአሠራር ለውጥ መሸጋገር ይኖርብናል፡፡ ሥራችንና አስተሳሰባችን እየሰፋና እያደገ መሄድ አለበት በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡