የ2008 ዓ.ም የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ !!!

9090

የጌታችን የመድኃኒታቺን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በመላ ሀገሪቱ ተከብሮ ውሏል።በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ  በዮሃንስ እጅ ለመጠመቅ ወደ ባህረ ዮርዳኖስ የወረደበትን ዕለት ለማሰብ  የሚከበር ነው፡፡
በተለይም በዓሉ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት በድምቀት በተከበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳት ፣የአዲስ  አበባ  ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ  ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ገብረፃዲቅ ሀጎስ፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፤ከተለያዩ የሰንበት ትምህርት ቤት የተውጣጡ ተማሪዎች እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት  በዓሉ በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።
ቅዱስ ፓትሪያሪኩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በቅዱስ መፅሃፉ እንደተፃፈው ያለው ለሌለው በማካፈልና በመተዛዘን ሊኖር ይገባል፤ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለአገር ሠላምና ልማት በጋራ መስራትን ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው የዝናብ እጥረት ምክንያት ለድርቅ የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝና በመርዳት በዓሉን ማክበር ከህዝቡ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ገብረፃዲቅ ሀጎስ በበኩላቸው በዓሉ ከመንፈሳዊ ገጽታው ባለፈ የማህበራዊና ባህላዊ ማንነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በቅዱስ ፓትሪያሪኩ ቡራኬ የበዓሉ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

{flike}{plusone}