የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የ2008 ዓ.ም በዓለ ጥምቀትን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
ከሁሉ በማስቀደም የሁላችንም አስገኚና የሕይወት ምንጭ እግዚአብሔር አምላካችን በሕይወትና በጤና ጠብቆ ለብዓለ ልደቱና ጥምቀቱ ስላደረሰን ምስጋና ይግባው፡፡
አምካችን እግዚአብሔር ከዘመን መለወጫ የቅዱስ ዮሐንስ በዓል እስከ ልደቱና ጥምቀቱ ድረስ በሰጠን ጊዜ በርካታ ነገሮችን አከናውኖልናል፡፡
የጀመርነውን የሒሳብ አሠራር ለውጥ ለማስፋት ሁለተኛ ዙር የሒሣብ ሠራተኞች ሥልጠና በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቅነው ባለፈው አጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሀገረ ስብከታችን ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን በሚሰጠን መመሪያ መሠረት ለተለያዩ አህጉረ ስብከት እና መንፈሳዊ ኮሌጆች ልማት ከፍተኛ እገዝ ያደረግንበት ወቅት ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስፋፋት በቀጣይ ዘመን በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚያገለግሉ ካህናት ለማፍራት የጀመርነውን ጥረት ወደ ተግባር በመቀየር ከጋምቤላ ክልልና ከደቡብ ሱዳን 21 ወጣቶችን በማምጣት በደ/ም/ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል የአብነት ት/ቤት ትምህርት እንዲጀምሩ የተደረገው በዚህ ወቅት ነው፡፡ በባሕረ ጥምቀት ቦታዎች አያያዝ ችግር የተፈጠረብንን ተግዳሮት በሰላማዊ ሁኔታ ከከተማችን አስተዳደር ጋር በቅርበት በመሥራት መፍትሔ ያገኘንበት ወቅት ነው፡፡
ባለፈው ወቅት በሀገረ ስብከታችን ለተከናወኑ እጅግ በርካታ ተግባራት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሰጡን ግልፅ አባታዊ መመሪያና የቅርብ ድጋፍ ትልቅ አቅም ስለሆነን ቅዱስ አባታችንን ለሰጠን ለአምላካችን እግዚአብሔር የምሥጋና መስዋዕት እናቀርባለን፡፡
በባሕረ ጥምቀት ጉዳይ ላይ ያቀረብነውን ጥያቄ መንግሥት በቀና ልቦና ተመልክቶ አዎንታዊ ምላሽ ስለሰጠን በዚህ አጋጣሚ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ድሪባ ኩማ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እና በልዩ ሁኔታ በመከታተል ጥያቄው የሕዝበ ክርስቲያኑን ፍለጎት በሚያሟላ ሁኔታ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረጋቸው ለክቡር ከንቲባውና ለአስተዳደራቸው በቅ/ቤተ ክርስቲያናችንና በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ስም ምስጋና እናቀርባለን፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ ያነሣውን ጥያቄ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት መዋቅርን ጠብቆ በሰላምና በሕጋዊ አግባብ ጥያቄውን በማቅረብና በመከታተል ላሳየው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርና አርአያነት ያለው የዜግነት ተግባር ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
መጪው የጥምቀት በዓል መንፈሳዊና የአምልኮ ሥርዓታችንን የምንፈጽምበት፤ ስብሐተ እግዚአብሔር የምናደርስበት ቢሆንም በርካቶች መንፈሳዊ ሥርዓታችንን ለመመልከት የሚመጡበት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ79 ባሕረ ጥምቀትና በ179 አብያተ ክርስቲያናት እጅግ በደመቀ ሁኔታ ነው በዓለ ጥምቀት የሚከበረው፡፡
ስለሆነም መንፈሳዊነቱንና ብሔራዊ ቅርስነቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መላው ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩበት አደራ እላለሁ፡፡
በዓላችንን የሰላምና የበረከት በዓል እንዲያደርግልን እመኛለሁ!!
ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
{flike}{plusone}