የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2008 የበጀት ዓመት ከ7ቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች የሥራ ግምገማ መርሐ ግብር አካሄደ

5682

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት  በ7ቱ ክፍላተ ከተማ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተከናወኑትን ዝርዝር የሥራ ተግባራት አስመልክቶ አርብ ሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከ7ቱም ክፍላተ ከተማ ከመጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለአንድ ሙሉ ቀን የቆየ የሪፖርት ግምገማ አካሄደዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የግምገማውን መርሐ ግብር አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት “ማእረሩ ብዙህ ወገባሩኒ ህዳጥ ሰአልዎ እንከ ከመይወስክ ገባረ ለማዕረሩ” (ማቴ 9÷38) አዝመራው ብዙ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ለመከሩ ሠራተኞችን እንዲጨምር የመከሩን ባለቤት ለምኑት እንደተባለው ሥራና ሠራተኛ አልተገናኘም፤
ስለዚህ አዝመራውን በወቅቱ ለመሰብሰብ የአዝመራ ሠራተኛ ያስፈልጋል፤ አዝመራ ካልተንከባከቡት ተባይ ያጠፋዋል፤ አዝመራው ረግፎ እንዳይቀር ሠራተኛ ያስፈልገዋል፤ ሀገረ ስብከታችን ለሌሎች አህጉረ ሰብከቶች ሞዴል የሚሆን ነው፤ በሰለጠነ የሰው ኃይልም ብቸኛ ነው፤ የገጠሪቱ መምህራን ወደ አዲስ አበባ እንጀራ ፍለጋ እየመጡ ናቸው፤ አምራቹን ክፍል መንከባከብ ያስፈልጋል፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሀብት ብዙ ስለሆነ ተንከባካቢና ጠባቂ ያስፈልገዋል፤ ሀገረ ስብከቱ ሥልጣኑን ወደ ክፍለ ከተማ ማውረድና ማከፋፈል አለበት በማለት ሰፋ ያለ አባታዊ መመሪያና ትምህርት አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልም ዋና ሥራ አስኪያጁ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን መገምገምና የታዩ ችግሮችን አርሞ ለማለፍ ሪፖርቱ እንዲቀርብ ያደረጉ ሲሆን የመጀመሪያውን ሪፖርት የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አቅርቧል፤ በቀረበው ሪፖርት ክፍለ ከተማው 10 ሠራተኞችና 20 ገዳማትና አድባራት ያሉት ሲሆን በእነዚሁ ገዳማትና አድባራት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በተግባር እንዲውል ተደርጓል፤ በህገ ወጥ ሰባክያን ዙሪያ ማስተካከያ ተደርጓል፤ በሕገ ወጥ የሠራተኞች ዝውውር ላይ ዳኝነት ተሰጥቷል፤ ዓበይት በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ተደርጓል፤ የሰበካ ጉባኤ አባላት የአገልግሎት ዘመናቸውን ፈጽመው በሌላ እንዲተኩ ተደርጓል፤ ከመቼውም በበለጠ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ተደርጓል፤ የአንድነት ጉባኤው ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ በአንድ አንድ አድባራት የሥራ ኃላፊዎች ለስብከተ ወንጌል እንቅፋት መሆናቸው ተገልጿል፤ ለአብነት መምህራን አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጓል፤ በገዳማቱና በአድባራቱ 37 የአብነት መምህራን ይገኛሉ፤ በገዳማቱና በአድባራቱ የልማት ሥራዎች እየተፋጠኑ ይገኛሉ፤ በ2008 ዓ.ም 37 ሚሊዮን የፐርሰነት ገቢ እንዲመዘገብ የተደረገ ሲሆን  ካለፈው የ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት የ13 ሚሊዮን ብር ብልጫ ታይቷል፤ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ ለቀጣዩ 2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዕቅድ አቅርቧል፤ ከአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀጥሎ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት በክፍለ ከተማው 35 ገዳማትና አድባራት ይገኛሉ፤ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተደርጓል፤ “ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር እንድትሉ ወንጌልን እንሰብካለን” የተባለውን የመጽሐፍ ቃል መሪ በማድረግ ስለ ስብከተ ወንጌል መጠናከር ስብሰባና ውይይት ተደርጓል፤ በሰበካ ጉባኤና በአገልጋዮች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ ተደርጓል፤ የአብነት ትምህርት ቤት እንዲጠናከር ተደርጓል፤ ለክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የቢሮ ኪራይ ሀገረ ስብከተ ሲከፍል  ቆይቷል፤ የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ሕንጻ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረ ሲሆን ሕንጻው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የካቴድራል ማዕረግ ተሰጥቶታል፤ ሰባት አብያተ ክርስቲያን እንዲቋቋሙ እየተደረገ ሲሆን 5ቱ ተተክለዋል፤ በ2007 ዓ.ም 8 ሚሊዮን  የፐርሰንት ገቢ የተመዘገበ ሲሆን በ2008 ዓ.ም ደግሞ 14 ሚሊዮን 650 ሺህ በመመዝገቡ የስድስት ሚሊዮን ብር የገቢ ብልጫ ታይቷል፤ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ የ2009 ዓ.ም ዕቅድ አቅርቧል፤ በመቀጠልም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ባቀረበው ሪፖርት ክፍለ ከተማው 26 ገዳማትና አድባራት፣ 14 ሠራተኞች አሉት፤ ዐውደ ወንጌል ዘተዋሕዶ በሚል ርዕስ የአንድነት ጉባኤው ተካሄዷል፤ ፈቃድ አልባ አጥማቂዎችንና ሰባክያንን ተቆጣጥሯል፤ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት 20 ሚሊዮን 947 ሺህ የፐርሰንት ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነፃፀር  የ5 ሚሊዮን ብር የገቢ ብልጫ አሳይቷል፤ ክፍለ ከተማው ለ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቶ አቅርቧል፤ በገዳማቱና አድባራቱ ግለሰቦች በሐሰተኛ ሰነድ እንዳይገለገሉ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ነው፤ ልዩ ልዩ ዓበይት በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ተደርጓል፤ በመቀጠል የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ባቀረበው ሪፖርት በሁሉም ገዳማትና አድባራት መልካም አስተዳደር ሰፍኗል፤ ባለ ጉዳዮች እንዳይጉላሉ  በማድረግ የመስተንግዶ አገልግሎት ተሰጥቷል፤ አዳዲስ በሚተከሉ አብያተ ክርስቲያናት የመሥራች ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፤ ስብከተ ወንጌልም ተጠናክሮ ቀጥሎአል፤ ሳይማሩ ተምረናል ሳይላኩ ተልከናል በሚሉ ሕገ ወጥ ሰባክያን ላይ አስፈላጊው የቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል፤ በክፍለ ከተማው በሚገኙ በሠዐሊተ ምሕረትና በኆኅተ ብርሃን ቅ/ማርያም የአብነት ት/ቤቶች ጉባኤ ዘርግተው የመማር ማስተማር ሥራ እያከናወኑ ናቸው፤ በሰሚት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቱ እና በደብሩ አስተዳደር መካከል የነበረው አለመግባባት ተፈቷል፤ በአንድ አንድ ገዳማትና አድባራት የአዳራሽና የሕንጻ ግንባታ እየተከናወነ ነው፤ ሕገ ወጥ ጨረታ እንዲቆም ተደርጓል፤ የዘመኑ የፐርሰንት ገቢ ከ24 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከ2007 የበጀት ዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ የገቢ ብልጫ ታይቷል፤ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በቀጣዩ ካቀዳቸው ዕቅዶች መካከል የመኪና እና የቢሮ መስሪያ ቦታ ግዥ ይገኙበታል::
በመቀጠልም የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ባቀረበው ሪፖርት በክፍለ ከተማው 27 አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፤ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፤ ከወትሮው በተሻለ የስብከተ ወንጌል ሥራ ተሠርቷል፤ ፈቃድ ሳይኖራቸው በገዳማትና አድባራት እየዞሩ ጥናታዊ ጽሑፍ እናቀርባለን በሚሉ ሰዎች ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ ርምጃ ተወስዷል፤ ካህናት ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፤ የአንድነት ጉባኤው በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል፤ በክፍለ ከተማው በርካታ አዳዲስ ሕንጻዎች እየተገቡ ይገኛሉ፤ በ2007 ዓ.ም የተመዘገበው የፐርሰንት ገቢ 9 ሚሊዮን ሲሆን በ2008 ዓ.ም 15 ሚሊዮን በመሆኑ ከ6 ሚሊዮን በላይ የገቢ ብልጫ አሳይቷል፤ በመቀጠል የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ባቀረበው ሪፖርት እኛ ከፈጣሪ የተቀበልነው የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ነው የመኪና ቁልፍ የተሰጣቸው ሰዎች ቁልፉ በተመሳሳይ ይከፈታል በማለት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ያስተማሩትን ትምህርት የዘወትር የሥራ መመሪያ በማድረግ ተሠርቷል፤ ለአገልጋዮች ስልጠና  ሰጥቷል፤ የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን የሰበካ ጉባኤ አባላት በአዲስ አባላት እንዲተኩ ተደርጓል፤ በግጭት አፈታት ዘዴ ችግሮች ተፈትተዋል፤ የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ባልተፈቀደላቸው  ሰዎች  እንዳይደፈር ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጓል፤ አጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥን በተመለከተ ሰለንጽህና ትምህርት ተሰጥቷል፤ በክብረ በዓላት ለንግድ የሚመጡ ሰዎች ከሕገ ወጥ የንግድ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ተደርጓል፤ በኦሮምያ ክልል ውስጥ 10, ሺህ ካሬ ሜትር በመቀበል ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ቅድመ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፤ ሁለት አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ታንፀዋል፤ በከተማው የማረምያ ቤቶች የምዕመናን ምዝገባ ተደርጓል፤ በክፍለ ከተደማው ከሚገኘው ሕዝብ 80% ኦርቶዶክሳዊ መሆኑ በተገኘው አሀዛዊ መረጃ ተረጋግጧል፤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጥምቀተ ባህር የኢ.ኦ.ተ.ቤ ይዞታ እንዲሆን በተደረገው እልህ አስጨራሽ ክትትል የጥምቀተ ባሕሩ ቦታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ እንዲሆን ተደርጓል፤ ሶስት የሚድያ ተቋማትም  ከቦታው ድረስ በመምጣት ዘገባውን በሬድዮ አስተላልፈዋል፤ በጥምቀተ ባህሩ ቦታ የጋራ ውይይት እና ምክክር በተደረገበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተናገሩት “ሕዝብ ከሚያዝን የመንግሥት ጥቅም ቢቀር ይሻላል!!” ብለዋል፤  በክፍለ ከተማው የሚገኙ 8 አድባራት ዘመናዊ የገቢ ማስገኛ ፎቅ እየገነቡ ናቸው፤ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በክፍለ ከተማው እርዳታ ተሰብስቦ ወደ ሚመለከተው ተልኳል፤ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ከ8 ሚሊዮን በላይ የፐርሰንት ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን በ2007 ዓ.ም ከተመዘገበው የፐርሰንት ገቢ 6 ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ የገቢ ብልጫ እንዲመዘገብ ተደርጓል፤ የአዲስ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትም በ2008 ዓ.ም ከ25 ሚሊየን ያላነሰ የፐርሰንት ገቢ ያስመዘገበ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡