ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2008 ዓ.ም የልደት በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

01610

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ  ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደት  ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
->በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
->ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
->የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
->በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
->እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የርስተ መንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ የወለደን እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ !!
‹‹ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው በእንቲአሁ፤ የእግዚአብሔር ፍቅሩ በዚህ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደዓለም ልኮታልና፤ (1ዮሐ.4፡9)፡፡
የእግዚአብሔር ባሕርይ ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይስማማውም፤ ጽድቅ እንጂ ሐሰት አይዋሐደውም፤ ብርሃን እንጂ ጨለማ አይቀርበውም፤ ሕይወት እንጂ ሞት በእርሱ ዘንድ የለምና በፍጹም ፍቅሩ እኛን ለመፈለግ ሥጋችንን ለብሶ በመካከላችን ስለተገኘ ለእርሱ የሚገባ የአምልኮ ምስጋና እናቀርባለን ፡፡
እግዚአብሔር ፍጹም በሆነ ፍቅሩ ሰማያትንና ምድርን እንደዚሁም በውስጣቸው የሚገኙትን፣ የሚታዩና የማይታዩትን ፍጥረታት ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶአል፤ ወይም አስገኝቶአል፣
ፈጣሬ ፍጥረታት የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን በየዓይነቱ የፈጠራቸው ፍጥረታት በእርሱ ዘንድ ከሚታወቁ በስተቀር በፍጡራን ዓቅም ተቆጥረው የሚዘለቁ ባይሆኑም በጥቅሉ የሚታዩና የማይታዩ፣ ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ተብለው ሊመደቡ ይችላሉ ፡፡
ከፍጡራን መካከል ሕይወት ያለውና በግዙፋኑ በኩል ሊታይ የማይችለው የቀደመ ስሙ ሳጥናኤል የኋላ ስሙ ሰይጣን፣ ወይም ዲያብሎስ የተባለ ረቂቅ መልአክ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ነጻ ፈቃድ ለክፉ ነገር በመጠቀም በፈጸመው ትልቅ በደል ለፍርድና ለቅጣት ተዳርጎአል (ኢሳ. 14፡12-15፤ ይሁ1፡6) ፡፡
ይህ ስሑት ፍጥረት በራሱ ስሕተት ሳያበቃ ሕያው ሆኖ በግዘፍ የሚታየውን ሰው በማሳሳት እንደእርሱ ለፍርድና ለቅጣት እንዲጋለጥ አደረገ (ዘፍ 3፡1-24፤ ራእ፣ 12፡7-9)
በዚህም ምክንያት ሰው ሕይወቱን አጣ፤ ሕይወት ማጣት ማለት እግዚአብሔርን ማጣት ወይም ከእግዚአብሔርና ከመልካም ስጦታው መለየት፣ መራቅ፣ መወገድ ማለት ነው፡፡
ዲያብሎስ በዘረጋው ወጥመድ ተሰነካክሎ የወደቀውና ሕይወቱን ያጣው ሰው ለድርብ የሞት ፍርድ ተዳረገ፤
በዚህ ፍርድ መነሻነትም አዳም ከነልጆቹ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ወይም ሥጋው በመቃብር ነፍሱ በገሃነም እንዲቀጣ ተፈረደበት (ዘፍ.2፡17፤3፡ 16-20)
ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱ ነው፤ ከእግዚአብሔር የተለየች ሕይወት ለጊዜው ያለች እንኳ ብትመስል ለዘለቄታው የለችምና በቁም ሳለች የሞተች ናት ፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ከግንዱ የተለየ ዛፍ ፍሬን ማፍራት እንደማይችል ሁሉ በእኔ የማይኖርም እንደቅርንጫፍ ወደውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፣ በእሳትም ያቃጥሉታል›› ሲል ያስተማረን ከእግዚአብሔር ውጭ የሆነ ሁሉ ሕይወትን ጨምሮ ምንም ምን ሊያገኝ የማይችል መሆኑን ለማስረዳት ነው (ዮሐ15፡4-6)፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ከሰው ልጅ ቀዳማዊ ታሪክ በመነሣት የተፈጸመውን እውነታ ስናስተውል ሰው የሕይወት ራስ የሆነውን እግዚአብሔርን በማጣቱ ከባድ የሆነ የሞት ቅጣት እንዳጋጠመው እናያለን፡፡
ከዚህ በኋላ የተነሣው ጥያቄ ሰው ከዚህ የሞት ቅጣት እንዴት ሊድን ይችላል? የሚለው ነው፡
እግዚአብሔር በልጁ በኩል መልሱን እንደነገረን ሰው ሊድን የሚችለው በፍቅረ እግዚአብሔር ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ‹‹እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እስከዚህ ድረስ ወዶታል›› ብሎ የድኅነት መነሻውና መድረሻው ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነ ነግሮናልና ነው (ዮሐ.3፡16-18)
የጌታችን ደቀመዝሙር የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደዓለም ልኮአልና የእግዚአብሔርን ፍቅር በዚህ ዓውቀናል፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል››ሲል የሕይወታችን ማግኛ ቁልፍ ነገር ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነ ያረጋግጣል፤ (1ዮሐ4፡16)
ሁሉን የፈጠረና ሁሉን የሚችል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን ስቦና ጎትቶ ወደኛ ያመጣው ሌላ ባዕድ ኃይል ሳይሆን በባሕርዩ ውስጥ ያለው ፍጹም ፍቅር ነው ፡፡
ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ፍቅር ምክንያት ወደእኛ መጣ፣ መጥቶም ሥጋችንን ከማይሞተው አካለ መለኮቱ ጋር በማዋሐድ መለያየትን አስወግዶ ወደእርሱ አቀረበን፡፡
የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ መጋቢት 29 ቀን በማኅፀነ ማርያም ሲፈጸም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባሕርየ መለኮት፣ ባህርየ ሥጋን ገንዘብ አደረገ፤ ባህርየ ሥጋም፣ ባህርየ መለኮትን ገንዘብ አደረገ፤ በዚህም መሠረት የአምላክና የሰው ተዋሕዶ ተፈጸመ፡፡
ሰው የሆነው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በተፀነሰ በዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን፣ በታሕሣሥ ወር፣ በዛሬው ዕለት ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም ተወለደ፤
በዳዊት ከተማ በቤተልሔም የተወለደው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋችንን ተዋሕዶ በፈጸመው የኃጢአት ካሣ፣ እኛ ከሞት ፍርድ ነጻ ወጥተን ወደ ሕይወት ለመሸጋገር በቅተናል፤ ይህም የሆነው በፍቅረ እግዚአብሔር ነው ፡፡
በመሆኑም ዛሬ በማክበር ላይ የምንገኘው ዓቢይ በዓል በእግዚአብሔር ፍቅር ተመሥርቶ ሰውን ለማዳን የተፈጸመው የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ነው፤ (ሉቃ.2፡6-20)
የልደተ ክርስቶስ በዓል የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነጻነትና የእኩልነት በዓል ነው፤ በዚህ ዕለት ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን እረኞች በአንድነትና በፍቅር ‹‹በምድርም ሰላም ይሁን›› እያሉ ስለ ሰላምና ደስታ ዘምረዋል፤
ይህ ዕለት ምድራውያን ነገሥታትና በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ እረኞች ፈጣሪያቸውን በእኩልነት ያዩበትና የሰገዱበት፣ በሰማያውያንና በምድራውያን ማለትም በእግዚአብሔርና በሰዎች፣ በሰዎችና በመላእክት መካከል ልዩ ግንኙነት እንደተፈጠረ የተገለፀበት፣ የተበሠረበትና የተዘመረበት ቀን በመሆኑ በዓሉ የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነጻነትና የእኩልነት በዓል ተብሎ ይታወቃል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
የዚህ በዓል ዓቢይ መልእክት ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚል መሆኑን በውል መገንዘብ አለብን (ሉቃ. 2፡14)
እግዚአብሔር ጥላቻን፣ መነቃቀፍን፣ መለያየትን፣ ራስ ወዳድነትን አይወድም ባህርዩ ፍቅር የሆነ እግዚአብሔር እነዚህን የማይወድ መሆኑን በማወቃቸው ነው ሰማያውያኑና ምድራውያኑ በአንድነት ሆነው ሰላም በምድር ይሁን ብለው የዘመሩ፤
ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም ደረጃ ወይም አካባቢ ይኑር፣ ከሰላም ውጭ ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችል የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ በሰላም ውስጥ ሆኖ ግን ሁሉንም ማግኘት እንደሚቻል ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ የታየው ውጤት ምስክር ነው፡፡
ዛሬም ዓለማችንም ሆነ ሀገራችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች በቀላሉ ማምለጥ የሚችሉት ከሁሉ በፊት ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ይዘው ሲጓዙ ነው፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተመላልሶ ሰውን ከሞት ያዳነው ማንንም ሳይጎዳ በሰላም ጎዳና ብቻ ተጉዞ ነው ፡፡
ጥላቻና ራስ ወዳድነት ሲያፈርሱና ሲያጠፉ እንጂ ሲያለሙና ሲገነቡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ታይተውም፣ ተሰምተውም፣ በታሪክ ሲደገፉም አይተን አናውቅም፤
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በልማትና በዕድገት እየገሠገሠች ያለች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነገ ብሩህ ተስፋ ትሆናለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሀገር ነች፤
ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ባርኮልን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም ወዘተ ሳንለያይ መላ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ያስገኘነው የልማት ፍሬ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
የተገኘው ፍሬ ልማት እየበረከተና እየደለበ ወደፊት እንዲቀጥልና እንዲያድግ እንጂ በማናቸውም ምክንያት ወደኋላ እንዲመለስ ሕዝባችን መፍቀድ የለበትም፡፡
መላው ሕዝባችን በሚገባ ማጤን ያለበት ነገር ቢኖር ምንጊዜም የችግር መፍትሔ ሰላምና ልማት እንጂ ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሌለ መሆኑን ነው፡፡
ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ሕዝቦች የገናን የሰላም መዝሙር እየዘመሩ ለጋራ ዕድገትና ለእኩልነት፣ ለሕዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት በጽናት መቆም ይኖርባቸዋል ፡፡
ሰላም ትልቁ የገና ስጦታ ነው፤ ልማትም የህልውና ማረጋገጫ ጸጋ ነው፤ ሁሉንም በእኩል እንጠብቃቸው፡፡
በመጨረሻም
በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት ለምግብ እጦት የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችን የወገንን እጅ በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፤
እነዚህ ወገኖች ግማሽ አካላችን መሆናቸውን ተገንዝበንና ጌታችን እኛን ለመፈለግ ወዳለንበት የመጣበትን ፍቅር አብነት አድርገን፣ እኛም እነርሱ ወዳሉበት በፍቅር በመሄድ በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና አለን ከጎናችሁ ልንላቸው ይገባል፤
አነሰ ሳንል በወቅቱ ፈጥነን እጃችንን ልንዘረጋላቸውና በአጠገባቸው ሆነን ልናበረታታቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር ሁላችንን እንደወደደን እኛም ወንድሞቻችንን በመመገብ፣ በማልበስና ችግራቸውን ሁሉ በመጋራት ለእግዚአብሔርና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ዛሬውኑ በተግባር እንድናሳይ መልእክታችንን በእግዚአብር ስም እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ
መልካም የልደት በዓል ያድርግልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታሕሣሥ 28 ቀን 2008 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

{flike}{plusone}