በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የ2008ዓ.ም የደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ(MA)
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የቤተክርስትያኒቱ ርዕሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትርያርክ ፤ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ የአዲስ አባባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን ፤የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ልብሰተ ክህኖ የለበሱ ካህናት፤መዘምራንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የእምነቱ ተከታዮች ምእመናንና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች በተገኙበት ነው በዓሉ የተከበረው።
በደመራው ክብረ በዓል ላይ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ የመስቀል በአል የደህንነት ፤ የፍቅር እና የወዳጅነት ምልክት ተደርጎ ይከበራል ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል የግብጹ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትርያርክ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ባለበት ወቅት እና የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት በተመዘገበበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ቆይታ የሁለቱን ሀገራት ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክርም ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገልፀዋል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ በበኩላቸው መስቀል በቀደሙት ጊዜያት የቅጣት እና የመከራ ምልክት እንደነበር አስታውሰው ኢየሱስ ክርስቶስ አዓምን ለማዳን በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ግን የሃይል፣ ደስታ እና የፍቅር ምልክት ሆኗል ብለዋል።በዓሉ ፍቅር እና ወደጅነትን ይፈጥራል ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ፥ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማንያን መልካም በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ባደረጉት ንግግርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሃይማኖት አገልግሎቶች በተጨማሪ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት፣ ያደገችና የበለጸገች አገር እንድትሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሁንም ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ ፤፤ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ በተገኙበት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ደመራውን በማዕዘን ባርከው የደመራ መለኮስ ሥነ ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ በዓሉ ተፈጽሟል።
{flike}{plusone}