የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ ለ፳፻፰ ዓ.ም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
እንኳን ከ ፳፻፯ ዓ.ም ወደ ፳፻፰ ዓ.ም ሁላችንንም በሰላምና በጤና ጠብቆ አደረሰን!!
ያለፈውን ዓመት በእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ፈቃድ በጤናና በሰላም አሳልፈነዋል ፤ ያለፈው ዓመት በሀገረ ስብከታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰጡት የመጨረሻ አመራር መሠረት በርካታ የለውጥ ሥራዎችን የጀመርንበት ዓመት በመሆኑ መልካም ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡
ባለፈው አጭር የሥራ ጊዜ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ በሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ በሰበካ ጉባኤ አባላት ፣ በካህናትና በምዕመናን የተጀመሩ ሥራዎች ከፍተኛ ድጋፍና ማበረታቻ አድርገውልናል ፤ ይህም ታላቅ የሞራል ስንቅ ሆኖን ለመጀመር አዳጋች የሆኑ ሥራዎችን ጀምረንበታል ፤ ለቀጣዩ አዲስ ዓመት ጥሩ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለን ሁኔታ መኖሩን ያረጋገጥንበት ዓመት ነው፡፡
በዚህ ዓመት በሀገረ ስብከቱ ታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለው የሀገረ ስብከት 20% ድርሻ ከገዳማትና አድባራት ገቢ የሰበሰብንበት ፣ የለውጥ ሥራዎችን በተለይም የበርካታ ችግሮች ምንጭ የሆነው የገንዘብ እንቅስቃሴያአችን በባንክ አሠራር እንዲያልፍና የቁጥጥር ሥርዓታችን እንዲሻሻል ፣ የንብረት አያያዝ አመዘጋገብና አወጋገድ ስርዓታችን አሳታፊ እንዲሆን ፣ የሰው ኃይል ቅጥር ስርዓታችን በግልጽ ውድድርና በባለሙያዎች መልማይነት እንዲፈጸም ፣ የሒሳብ አያያዛችን ዘመኑ በደረሰበት የሒሳብ አሠራር ዘዴ እንዲሆን ፣ የሰው ኃይል ሥልጠና እንዲሰጥ ቅድመ ሁኔታ ያደረግንበት ነው፡፡
በቀጣዩ ፳፻፰ ዓ.ም የጀመርነውን ሥራ በማስፋት፡- የገንዘብ አሰባሰብ ሥርዓታችን ሙሉ በሙሉ በባንክ እገዛ የሚካሄድበት ፣ የንብረት አያያዝ ሥርዓታችንን የምናዘምንበት ፣ የተጀመረውን ሥልጠና አጠናክረን የአስተዳደር ሥራችንን በተሻለ አቅም የምናካሂድበት ፣ የሰው ኃይል አስተዳደራችንን ዘመናዊ ለማድረግ አስፈላጊ ጥናቶችን በማድረግ የአሠራር ማንዋሎችን በማዘጋጀት በሰፊ ውይይት አዳብረንና ሥልጠና ሰጥተን የምንተገብርበት ፣ ለረጅም ጊዜ እየተሞከረ ግን ሳይነካ የቀረውና በርካታ አበው ካህናት ቤተሰቦቻቸውን ለጉዳት የዳረገውን የማህበራዊ ዋስትና ጉዳይ እልባት እንዲያገኝና ካህናቶቻችን የጡረታ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሥራ የምንሠራበት እንዲሆን ተግተን እንሠራለን፡፡
በዚህ ሁሉ ጥረታችን ለቤተ ክርስቲያናችን የራሳችንን አስተዋጽ ማድረግ እንድንችል ወሳኙ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድና እርሱ የሚሰጠን ኃይል ነው፡፡
መላው ካህናትና ምዕመናን የሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከጎናችን እንዲሆኑ ፣ ባለፈው ዓመት በሥራችን በጎ አስተዋጽኦ ያልነበራቸው ወገኖች በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ተላብሰው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ፤ ጥሬን አቀርባለሁ፡፡
ባለፈው ዓመት በነበረን አጭር የአገልግሎት ጊዜ በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ያለፍን በመሆኑ ፈጣን አገልግሎት ያላገኛችሁ እና በውሳኔአችን ቅር የተሰኛችሁ ወገኖች በሚቀጥለው ዓመት በምንሰጠው አገልግሎት የምትደሰቱበት እንዲሆን በጸሎትና በይቅርታ እንድታስቡን አሳስባለሁ፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን መጪው ዓመት የሰላም ፣ የጤና ፣ የሥራና የውጤት ፣ የስኬትና የብልጽግና ዓመት ያድርግልን፡፡
ሊቀማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
ጳጉሜን ፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም
{flike}{plusone}