ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2008 ዓ.ም የትንሣኤን በዓል አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

01610

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
•ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
•የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
•በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
•እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ የተነሣው፣ የሕይወት ራስና የሁሉ ፈጣሪ የሆነው፣ ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ !!
‹‹ዓይቴ እንከ ቀኖትከ ሞት፤ ወዓይቴ እንከ መዊዖትከ ሲኦል፤
ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?
ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?›› /1ቆሮ. 15፡55/፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ሞትና መቃብር የኃጢአትና የበደል ውጤቶች እንጂ የተፈጥሮ ዕድል ፈንታ ሆነው ለሰው የተሰጡ አይደሉም ፡፡
ሰው በራሱ ምርጫ ካልሆነ በቀር የሚሞት ሆኖ እንዳልተፈጠረ ቅዱስ መጽሐፍ ሲገልጽ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- ‹‹ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ›› ይላል፤ (ዘፍ.2፡16-17)፡፡
ሔዋንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መሠረት አድርጋ ስትናገር፣ ‹‹እግዚአብሔር እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም›› ብሎናል ብላ አረጋግጣለች፤ (ዘፍ.3፡3)፡፡
ከዚህ አምላካዊ ቃል መረዳት እንደሚቻለው አዳም አትብላ የተባለውን ዛፍ ባይበላ ኖሮ አይሞትም ነበር ማለት ነው፤ ከዚህ አንጻር የሞትና የመቃብር ምንጩ ሕገ ተፈጥሮ ሳይሆን ግብረ ኃጢአት ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡
በመሠረቱ ግብረ ኃጢአት የሚመነጨው ለእግዚአብሔር ካለመታዘዝ እንደሆነ ከዚህ መረዳት እንችላለን፤ ምክንያቱም አዳምና

ሔዋን ሁለት ምርጫዎች ቀርበውላቸዋል፤ ማለትም በአንድ በኩል ‹‹መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብሉ፤ ከበላችሁ ግን ትሞታላችሁ›› የሚል የእግዚአብሔር ትእዛዝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ብትበሉ ሞትን አትሞቱም፤ ነገር ግን ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ ይከፈታሉ፤ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ›› የሚል የእባብ ወይም የሰይጣን ምክር ቀርቦላቸዋል ፡፡
በዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ገሸሽ በማድረግ የእባቡን ምክር ተቀብለው ዛፉን በሉ፤ በዚህም ከባድ በደልን ፈጸሙ፡፡
አዳምና ሔዋን በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን ሐሰተኛ አድርገውታል፤ ምክንያቱም የእርሱን ትእዛዝ ትተው የእባቡን ምክር ሲቀበሉ፣ እግዚአብሔርን እንደ ሐሰተኛ፣ እባብን እንደ እውነተኛ አድርገው መቀበላቸው እንደሆነ ግልፅ ነውና ፡፡
ኃጢአትን ወልዶ፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ከባድ የሞትና የመቃብር ቅጣትን ያስፈረደ በደል፣ ይህ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝና የተሳሳተ ምርጫ ነው፤ የሞት ቅጣቱ ድሮውም ከዛፉ በበላህ ቀን ትሞታለህ ተብሎ በግልጽ የተነገረ ስለነበረ አዳም ዛፉን በበላ ቀን ቅጣቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ ሆኖአል፤ ማለትም አዳም ‹‹ዛፉን እንደበላ ወዲያውኑ ራቁቱን ወጥቶአል›› በመራቆቱም ከእውነተኛው ልብስ ከእግዚአብሔርና ከጸጋዎቹ መለየቱ በዚህ ተረጋግጦአል፤ ሞት ማለት መለየት ማለት ነውና፡፡
በአዳም ላይ የተፈረደው፣ ሞት ብቻ ሳይሆን ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ›› ተብሎም በሞት ላይ ርደተ መቃብርን ተፈርዶበታል፤ (ዘፍ. 3፡19)፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰው ከእግዚአብሔር በመለየቱ ሞትና መቃብር ተረክበውታል ፡፡
በይቀጥላልም ሰው ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ልምዱን አጠናክሮ ሲቀጥልበት፣ ዲያብሎስም በኃጢአት ጦር ሰውን እየወጋ ሲገድል፣ መቃብርም ሙታንን እየተቀበለ ሲማግድ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት አለፉ ፡፡
ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመዓቱ አንጻር ምሕረቱን አያርቅምና በዲያብሎስ ምክር ድል ሆኖ የተሸነፈውን ሰው የሚታደግና ዲያብሎስን ድል የሚያደርግ ብርቱና ኃያል ዘር ከጊዜ በኋላ ከሴት እንደሚወለድ በመግለጽ ወዲያውኑ ተስፋ ድኅነትን ሰጥቶአል፤ (ዘፍ. 3፡15)
ይህ ዘር የጠላት ዲያብሎስን ደጅ በድል አድራጊነት እንደሚወርስ ‹‹ዘርህ የጠላትን ደጅ ይወርሳል›› ተብሎ፣ የምድር አሕዛብ ሁሉ በዚህ ዘር እንደሚባረኩና እንደሚድኑ ‹‹በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ›› ተብሎ በትንቢት እየተብራራ፣ እየተገለፀና እየተነገረ ቆይቶአል፤ (ዘፍ. 22፡17)፡፡
ይህ ድል አድራጊ ዘር እንደ ትንቢቱ ቃል ከሴት ማለትም ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በዚህ ዓለም ተገለፀ፤ ቅዱስ ወንጌልን እያስተማረ በዚህ ዓለም በተመላለሰ ጊዜም፡-
•ሕሙማን በመፈወስ፣
•ዕውራንን በማብራት፣
•ለምጻሞችን በማንጻት፣
•ሓንካሳንን በማቅናት አዳኝነቱን አስረዳ፡፡
በፈጣሪ ሥልጣን ካልሆነ በቀር በፍጡር ሊደረጉ የማይችሉና ከአእምሮ በላይ የሆኑትን ዓበይት ተአምራት በማድረግ ሁሉን የሚችል አምላክ መሆኑን አሳየ፡፡
ዲያብሎስ በጾሙ ወቅት ያቀረበበትን ፈተና በመበጣጠስ፣ እንደዚሁም አንተ ሰይጣን፣ ከእርሱ ውጣ!! እያለ ከሰዎች በማስወጣት፣ ኃጢአትህ ተሠርዮልሃል እያለ ኃጢአትን በማስወገድ ሥልጣነ መለኮቱን ገሐድ አደረገ፤
‹‹አልአዛር አልአዛር ና ውጣ ከመቃብር›› እያለ ሙታንን በማስነሣት በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው መንሥኤ ሙታን መሆኑንም በተግባር አረጋገጠ፤
በአጠቃላይ በኃጢአት፣ በዲያብሎስ፣ በሞትና በመቃብር ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለው ድል አድራጊ ዘር መሆኑን በተጨባጭ አሳየ፡፡
የማስተማር ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ፣ በሰው ፈንታ ተሰቅሎ፣ ሞቶና ተቀብሮ የሰውን ዕዳ-ኃጢአት በመክፈል አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን ሙሉ በሲኦል የነበሩትን ነፍሳት ወደጥንተ ቦታቸው ወደ ገነት መልሶ አስገባ፤ (1ኛ ጴጥ. 3፡18-19፣ ሉቃ. 23፡43) ፡፡
እርሱም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በራሱ መለኮታዊ ሥልጣን ተነሣ፤ በዚህ ጊዜ የሞት መውጊያ የሆነው ኃጢአት ተሻረ፣ ሞት ተሸነፈ፣ መቃብርም ድል ሆኖ ባዶውን ቀረ ፡፡
በጌታችን ትንሣኤ የተበሠረው የሞት መሸነፍና የመቃብር ድል መሆን፣ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ ለሰው ዘር ሁሉ እውን ይሆናል፤ ያን ጊዜ ሞትና መቃብር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ህልውናቸውን አጥተው ያከትማሉ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ሁሉ ትንሣኤ በኩር ሆኖ ተፈጽሞአል፤ በመሆኑም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ‹‹ክርስቶስ ተነሣ›› ብለን የምሥራች በመናገር ብቻ ሳይሆን እኛም እርሱ በተነሣው አኳኋን እንነሣለን እያልን ተስፋ ትንሣኤያችንን በማብሠርና በማስተጋባት ጭምር ሊሆን ይገባል፤
የእኛ ትንሣኤ በክርስቶስ ተጀምሮ አሁን በሂደት ላይ ያለ ሲሆን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ሲመጣ የሁላችን ትንሣኤ እውን ይሆናል፤ የሰው የመጨረሻ ዕድሉ ሞት ሳይሆን ትንሣኤ መሆኑንም በዚያን ጊዜ ይረጋገጣል ፡፡
በዚህም ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ለዘለቄታው ተሸናፊ ሳይሆን በአምላኩ ቸርነት በመጨረሻ አሸናፊ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ዛሬም ቢሆን የሰው አሸናፊነት በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ሕይወቱ በግልጽ የሚታይ ነው ይኸውም፡-
በሥጋዊ ሕይወቱ በኩል ከጥንት ጀምሮ በተፈጥሮ ሀብት ላይ በሚያደርገው የምርምርና የተግባር ጥረት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና ድል በድል እየተጓዘ ዛሬ ለደረሰበት የቴክኖሎጂ ብልፅግና በቅቶአል ፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወቱ በኩልም ከአምልኮ ጣዖት ተላቆ በአንድ እውነተኛ አምላክ በማመንና ከእርሱ ጋር ግንኙነት በማድረግ በሞራል፣ በሥነ ምግባርና በሃይማኖት የበለጸገ ማኅበረ ሰብ በዓለም እንዲኖር አስችሎአል ፡፡
ስለሆነም ዲያብሎስን፣ ኃጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን የሚያሸንፉ መስተጋድላንና መዋዕያን ቅዱሳን በብዛት እንዲገኙ አድርጎአል፤ አሁንም በዓለም ዙሪያ ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንፈሳውያን አርበኞችና ድል አድራጊዎች አሉ፤ ባለፈው ዓመት በሊቢያ የተሰዉ ልጆቻችን በዚህ መንፈሳዊ አርበኝነት የቅድስና ድልን የተጎናጸፉ ተጠቃሽ ሰማዕታት ናቸው ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቸቻችን ምእመናንና ምእመናት፣
የምንኖርባት ዓለም የትግል ሜዳ ናት፤ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ሁሉ በትግል የተሞላ በመሆኑ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኑሮአችን ከትግሉ ማምለጥ አንችልም፤ እውነቱ ይህ ከሆነ የሚያዋጣው ከትግሉ መሸሽ ሳይሆን ታግሎ ማሸነፍ ነው፡፡
የጌታችን ነገረ መስቀልም የሚያስተምረን ‹‹ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ያጥብዕ ወይንሣእ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ፤ ወዘኢፆረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ ወኢይደሉ ሊተ፤ ሊከተለኝ የሚወድ መስቀለ ሞቱን ይዞ በቆራጥነት ይከተለኝ፤ መስቀለ ሞቴን ተሸክሞ የማይከተለኝ ሊያገለግለኝም የኔ ሊሆንም አይችልም እያለ ነው፤ (ማቴ 10፡38)፡፡
በዚህ ክርስቶሳዊ የተጋድሎ ጥሪ ቅዱሳን ሐዋርያትና ቅዱሳን ሰማዕታት በአጠቃላይም ክርስቲያኖች ሁሉ ወደትግሉ ሜዳ ተቀላቅለውና በድል አድራጊነት ግዳጃቸውን ተወጥተው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠች ሃይማኖትን አስረክበውናል ፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ፣ ዲያብሎስንና ኃጢአትን፣ በትንሣኤው ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ እንደተነሣ፣ የእርሱ ተከታዮች የሆኑ ቅዱሳን ክርስቲያኖችም በዚያው ፍኖተ መስቀል እየተጓዙና ድልን እየተቀዳጁ ከኛ ዘንድ ያደረሱትን ሃይማኖታዊ ተልእኮ በተለመደው መንፈሳዊ ትግል በመጠበቅ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የእኛ ፈንታ ነው ፡፡
የሃይማኖት ትግል በየወቅቱ የሚለዋወጥ ከሚሆን በቀር የሚቆም አይደለም፤ የዘመናችን ትልቁ የሃይማኖት ተግዳሮት ቴረሪዝም፣ ሴኩላሪዝምና ግሎባላይዜሽን በማንነትና በሃይማኖት ህልውና ላይ እየፈጠሩት ያለ ከባድ ጫና ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ በአጠቃላይም በሀልዎተ እግዚአብሔር የሚያምኑ ሁሉ ሃይማኖትና ዕሴቶቹ የፈጠሯቸው የማንነት ጸጋዎችን አጽንተው በመያዝ ካልመከቱ በቀር የሴኩላሪዝምና የግሎባላይዜሽን ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡
ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ረገድ ማለትም ሃይማኖቱንና ከሃይማኖት የተወረሱ ዕሴቶቹን፣ እንደዚሁም የተቀደሰ ባህሉን እየጠበቀ ለሃይማኖቱና ለማንነቱ እንዲቆም ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ትመክራለች፣ ታስተምራለችም፡፡
እኛ ክርስቲያኖች በሱባኤው ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በምፅዋት፣ በንሥሐ፣ በቅዱስ ቁርባን፣ ፍቅርንና ሰላምን ገንዘብ በማድረግ ዲያብሎስንና ኃጢአትን ስንታገላቸው እንደቆየን ሁሉ፣ አሁንም በበዓለ ፋሲካው ቀን ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናት፣ በድርቅ የተጎዱትን ወገኖች በተለይም በአሁኑ ወቅት የግድያና የአፈና ሰቆቃ ደርሶባቸው በኃዘንና በችግር ላይ የሚገኙት የጋምቤላ ብሔረ ሰብ ልጆቻችንና ወገኖቻችን በሁሉም ነገር ከጎናቸው ሆነን በማገዝ፣ በመመገብ፣ በማጠጣትና በማልበስ፣ በሽተኞችን በመጠየቅና በመርዳት ፍጹም የደስታና የድል ቀን አድርገን ማክበር ይገባናል፤ በዚህ መልካም ሥራችንም የትንሣኤ ልጆች መሆናችንን ማስመስከር ይኖርብናል ፡፡
በመጨረሻም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓለ ትንሣኤን ሲያከብር ማስታወስ ያለበት የክርስቶስን አሸናፊነት ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ አሸናፊዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል፤ አሸናፊነታቸውም በሃይማኖትና በልማት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ሕዝቦች በአጠቃላይ በድህነት ላይ የጀመሩትን ትግል በድል ማጠናቀቅ ይችሉ ዘንድ ሰላማቸውንና አንድነታቸውን በመጠበቅ የሀገራችንን ሕዳሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፣ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 23 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ