የ2007ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባለ8 ነጥብ መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

0139

ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዘንድሮውን መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያካሒድ ሰንብቷል፡፡
በዚሁ መሠረት የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዐሉ ዋዜማ ከጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ለ15 ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፎአል ፡፡ ከተላለፉት በርካታ ውሳኔዎች መካከልም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው ፡፡
1.    የጥቅምቱ 2007 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቅዱስ ፓትርያርክ የመግቢያ ንግግር ከተከፈተ በኋላ ሠላሳ ሦስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያቀረበው የጋራ መግለጫ የ2007 የበጀት ዓመት የሥራ መመሪያ ሆኖ እንዲሠራበት ወስኗል ፡፡  
2.    በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው አርቃቂ ኮሚቴ ያቀረበው ረቂቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ ለምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ገጽ በገጽ ከተነበበና እርማት ከተደረገ በኋላ ይኸው ሕግ እንዲሠራበት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ አጽድቋል ፡፡
3.    የግንባታው ሥራ እየተካሔደ ለሚገኘው ለታላቁ የዓባይ ሕዳሴ ግድብ ማከናወኛ አገልግሎት ይውል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል ከሃያ ሦስት ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማድረጓ የሚታወስ ነው፤ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች የተገኘውን በድምሩ ብር 16,403,091.01 (ዐሥራ ስድስት ሚሊዮን ዐራት መቶ ሦስት ሺህ ዘጠና አንድ ብር ከዜሮ አንድ ሳንቲም) ገቢያደረግን ስለሆነ ይኸው ታውቆ የሕዳሴው ግድብ ለሀገራችን የዕድገት ታሪክ ምዕራፍ ከፋች ይሆናል ተብሎ ስለታመነበትሁሉም ኅብረተሰብ ጠቀሜታውን ከወዲሁ በበለጠ በመረዳት አስፈላጊውን ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም እንዲረባረብ በዚህ አጋጣሚ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
4.    በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን በተለይም በምዕራብ አፍሪካ ዙሪያ እየቀሰፈ የሚታየው ‹‹ኢቮላ›› በመባል የሚታወቀው አዲስ ቀሳፊ በሽታ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባና ከዓለም ዙሪያ እንዲጠፋ ከወዲሁ መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በመከላከሉ ረገድ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ይደመጣል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የኅብረተሰቡ አገልጋይ ከመሆኗ አንፃር የበኩሏን ድርሻ ልትወጣ የሚገባት ስለሆነ፤ በየአህጉረ ስብከቱ በየአንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምህላ ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡
5.    በጀትን በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለ2007 ዓ.ም. ተጠንቶ የቀረበውን በጀት አጽድቋል ፡፡
6.    የሰዎች ሕገ ወጥዝውውር የሀገርን ክብር የሚፈታተን ተተኪትውልድን የሚያሳጣ ድርጊት በመሆኑ ይህን ሕገ ወጥ አሠራር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ እየተነገረ ነው፤ቤተክርስቲያኒቱም ቅድሚያ ለሀገርና ለወገን ክብር በመስጠት ይህን በተመለከተ በማንኛውም የቤተክርስቲያኒቱ ዐውደምሕረትሁሉ አስፈላጊው ትምህርት እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
7.    በጋምቤላናበቤንችማጂ ክልል በነዋሪው ሕዝብ መካከልስለተከሰተውአለመግባባት ጉዳይ ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ ለሀገሪቱ ሰላም ለልማትና ለዕድገት ዕንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች እንዲወገዱ፣ኅብረተሰቡ በሰላምና በመግባባት እንዲኖር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መልእክቱን አስተላልፏል ፡፡
8.    ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው እርቀ ሰላም ተጠናክሮ መቀጠሉ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር የሚበጅ መሆኑ ስለታመነበት አሁንም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስለ ቀጣዩ ሰላም በሰፊው ተነጋግሮ በቤተ ክርስቲያናችን በኩል የሰላሙ ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጠል ጉባኤው ወስኗል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ውይይቱን በመቀጠል፤
–    ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ በማስጠበቅ፤
–    በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር አመራር ሰጭነት የተጀመሩት ልዩ ልዩ የልማት ድርጅቶች ለውጤት በቅተው አገልግሎትን እንዲሰጡ ለማስቻል፤
–    በሀገር ውስጥና በውጭው አህጉረ ስብከት ተመድበው በሚሠሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አማካይነት የተካሔደውን ሐዋርያዊ ተግባር በመገምገም፤
–    ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንና አረጋውያት የሚጦሩበት፤አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት እየተማሩ የሚያድጉበት የምግባረ ሠናይ ተቋማት በየአህጉረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ ለማድረግ፤
–    ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት የሚበጀውን ሁሉ መፈጸም የሚያስችል መመሪያን ሰጥቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል ፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ሕዝባችንን፣ ሀገራችንን ይባርክ፤
ለሀገራችን ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፤
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም፤ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

{flike}{plusone}