የ2007 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ
በየአመቱ ከጥቅምተ 12 ቀን ጀምሮ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ በዞንደሮው 2007 ዓ.ም ጥቅምት 11ቀን 2007ዓ.ም. ከቀኑ ዐሥር ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎተ ምኅላ የተጀመረ ሲሆን በማግስቱ ከጥቅምተ 12 ቀን 2007 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤው ተጀምሯል፡፡
በዚሁ የመክፍቻ መርሃ ግብር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚከተለውን ጋዜጣዊ መግለጫ አስተላልፈዋል፡፡
የጥቅምት 2007 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ምእመናንን በንጹሕ ደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በቅዱስ መንፈሱ መሪነት እየጠበቀ ከዚህ ጊዜ ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን ፡፡
እንደዚሁም ሁላችንን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከየሀገረ ስብከታችን በረድኤት ስቦ በሀብት አቅርቦ በዚህ ሐዋርያዊና ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተገናኝተን በእግዚአብሔር ስለተሰጠን ዓቢይ ተልእኮ እንድንመካከር ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን ፡፡
ወመጺኦ ውእቱ መንፈሰ ጽድቅ ይመርሐክሙ ኀበ ከሉ ፍኖተ ጽድቅ፤ ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል ፤ (ዮሐ. 16:13)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቃሉና በክቡር ደሙ ከመሠረታት በኋላ በበዓለ ሐምሣ በወረደውና ወደ እውነት ሁሉ በሚመራው በመንፈስ ቅዱስ እንድትመራ ማድረጉ ሁላችንም የምናውቀው ነው ፡፡
ከበዓለ ሐምሣ ጀምሮ እስከ ዛሬ፣ ከዚህ በኋላም እስከ ዕለተ ምጽአት፣ ከዚያም ቀጥሎ ማኅለቅት በሌላቸው አዝማነ መንግሥተ ሰማያት ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና አስተማሪነት ተጠብቃ ትኖራለች ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቅበት የራሱ የሆነ ጥልቅና ረቂቅ አምላካዊ ጥበብ ያለው ሲሆን፣ ከሚታወቅ የአመራር ጥበቡ አንዱ የሐዋርያት ጉባኤ ወራሽ በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን የሚመራበት ጥበቡ ነው ፡፡
መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማካኝነት በኒቅያ፣ በቁስጥንጥንያና በኤፌሶን ብዙ መናፍቃንን ከቤተ ክርስቲያን ለይቶ በማውጣት ቤተ ክርስቲያንን ከስሕተትና ከውድቀት ታድጓል ፡፡
በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለትም ሦስትም ሆናችሁ በስሜ በምትሰበሰቡበት እኔ በዚያ አለሁ$ ብሎ ቃል ኪዳን የገባለትና በባለቤትነት የሚገኝበት ዓቢይና ቅዱስ ጉባኤ ነው ፡፡ (ማቴ.18:20)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት፣ በሁሉም ያለች፣ ቅድስትና አንዲት እንደመሆንዋ መጠን ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል የተመራችው በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው ሲኖዶስ እንጂ በሌላ በማንም አይደለም ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በምሥራቅ አፍሪካ፣ ብሎም በአፍሪካ ምድር በጠቅላላ፣ በማንኛውም ሐዋርያዊ ሚዛን ትክክለኛ ሃይማኖት ያላት ጠንካራና አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናት ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንታዊው ትምህርተ ሃይማኖት ዝንፍ ሳትል በሚያስደንቅ ሁኔታ የሁለት ሺሕ ዘመናት ዕድሜ ክርስትናን ማስቆጠር የቻለችበት ዓቢይ ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሚቃኝ ሲኖዶሳዊ አመራር መመራቷ ነው ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ዛሬም እንደጥንቱና እንደትናንቱ የቤተ ክርስቲያናችን ብቸኛ መሪ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ቅዱስ ሲኖዶስ እንጂ ሌላ አይደለም ፡፡
ሁላችንም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ይህንን ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ ተልእኮ ጠብቀን እንዳለ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን፡፡
ሉዓላዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣንና ኃላፊነት በተለያየ ምክንያት በመጋፋት የራሳቸውን ሥውር ዓላማ ለመፈጸም የሚከጅሉ ወገኖች ከስሕተታቸው እንዲመለሱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው ይብዛም ይነስ፤ ዘመን ያለ ታሪክ አያልፍም፤ በየዘመናቱ ያለ ትውልድ በይበልጥ ደግሞ በኃላፊነት የሚቀመጡ ኃላፊዎች የታሪኩ አካል መሆናቸው አይቀርም፤ እንደሌላው ሁሉ እኛም ከዚህ እውነታ ማምለጥ አንችልም፡፡
ታሪክ አንድን ትውልድ በመልካም ወይም በመጥፎ ሊመዘግብ ይችላል፤ የእኛ ታሪክ እየተመዘገበ ያለው ከሁለቱ በየትኛው ነው? የሚለው ግን የሁላችንም መሠረታዊ ጥያቄ ሊሆን ይገባል፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሩቅ መጓዝና ልዩ ምሁርን መጠየቅ አያስፈልገንም ፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ እስመ ኢኮነ ርኁቀ እምኔነ፤ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም እንዳለው የሰው ኅሊና በአካባቢውና በውስጡ ያለውን ለይቶ ማወቅ ይቅርና ከአእምሮ በላይ የሆነውን የረቂቅ አምላክ ህልውና እንኳ በመጠኑም ቢሆን ማወቅ የሚችል ነው፡፡ (ዮሐ.ሥራ.1:27 )
መንፈስ ቅዱስም #ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታጽንዑ ልበክሙ ‹ዛሬ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ ልባችሁን አታጽኑ›› እያለ የሚጣራበት ጊዜ እንደሆነ ማወቁ አይከብድም$:: (ዕብ. 315)
በመሆኑም ራስን በራስ በመጠየቅ የሚገኝ መልስና ራስን በራስ በመወሰን የሚሰጥ ዳኝነት ከሁሉም የበለጠ ፈዋሽ መድኃኒት ነውና በራሳችን ዳኝነት የቤተ ክርስቲያናችንን ሉዓላዊነትና አንድነት እንደዚሁም ምእመናንዋና ሀብቷ የሚጠበቁበት ሥራዎችን መሥራት የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ተግባር ነው ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ታላቋና መተኪያ የማይገኝላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በውስጥም ሆነ በውጭ የተጋረጡባት ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች እንዳሉ መገንዘብ አለብን ፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ከሚታዩ ፈተናዎች አንዱና ዋነኛው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ወደ ሌላ እምነት እየፈለሱ ከመሆናቸው ሌላ፤
• የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት አያያዝ አስተማማኝ ሆኖ አለመገኘቱ፤
• የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የንብረት አስተዳደራችን በዘመኑ ቴክኖሎጂ የተቃኘ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አለመሆኑ፤
• በቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን የማታውቀውና የማትቆጣጠረው ሀብትና ንብረት የሚሰበስቡ ማኅበራት እየተበራከቱ መምጣታቸው፤
• በቤተ ክርስቲያን ስም ሀብትን የሚሰበስቡ ማኅበራት በእነርሱ የምትተዳደር ቤተ ክርስቲያን ሳትኖር የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ መብት የሆነውን ከምእመናን ገንዘብና ንብረት የመሰብሰብ ሥልጣንን ወደራሳቸው በማዞር ገንዘብና ንብረት ከምእመናን መሰብሰብ መልመዳቸው፤
• በዚህም ምክንያት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት የተለያዩ ዓሥራትና በኩራት ሰብሳቢዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው፤
• በቤተ ክርስቲያን እየተፈጠረ ያለው ሁለተኛ ባለሀብት ማኅበር በሂደት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሁለት የመክፈል አዝማሚያ እንዳለው ግልጽ ማስረጃ መገኘቱ፤
• ማኅበራቱ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት የሚሰበስቡ በመሆናቸው ገንዘቡ በሚያስከትለው ሌላ ጉዳት ቤተ ክርስቲያን በአክራሪነት የምትፈረጅበት አጋጣሚ መከሠቱ፤
• ማኅበራት በሌላቸው ሥልጣን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥራ በቀጥታ ጣልቃ እየገቡ የሰላም ጠንቅ ሆነው መገኘታቸው፤
• ችግሩን በቀላሉ ለማስተካከል ቢሞከር እንኳ ማኅበራቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሰጣቸውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኝነቱና ቅንነቱ ፈጽሞ የሌላቸው ሆነው መገኘታቸው አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ሆኖ ተገኝቶአል ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
‹‹በይሉኝታ የራስ ዓሊ ቤት ተፈታ›› እንደተባለው ትዕግሥትና ደግነት በዚያም ላይ ይሉኝታ ተጨምሮበት ካልሆነ በቀር እነዚህን ወገኖች የምናስተናግድበት ቤትና የምንዳኝበት ሕግ ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም ፡፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በሃይማኖታችን ትውፊት ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ጸበልን ቀምሶ የሚኖር የጽዋ ማኅበር ካልሆነ በቀር በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ቤተ ክርስቲያንን አህሎ የተደራጀና ቤተ ክርስቲያን አከል የሆነ ገንዘብ ሰብሳቢ ማኅበር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ፡፡
ስለሆነም በመልካም አስተዳደር፣ በሀብትና በንብረት አያያዝ፣ በመሪ እቅድ እየተመሩ ሥራ መሥራትን አስመልክቶ የተጀመሩ ሥራዎች አጠናክሮና አፋጥኖ ከዳር የማድረሱ ተግባር እንዳለ ሆኖ በተለይም በምእመናን ፍልሰትና በማኅበራት ጉዳይ ላይ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጡ ቤተ ክርስቲያንን የመታደግ ጉዳይ መሆኑን በአጽንዖት ሳንጠቁም አናልፍም ፡፡
በመጨረሻም
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ግልጽ በሆነ ሁኔታ እያልን ያለነው
1. የምእመናን ፍልሰት በአሁኑ ጊዜ እየተባባሰ ስለመጣ ሁላችንም ተባብረንና አስፈላጊውን ሥራ ሠርተን ፍልሰቱን እናስቁም፤
2. የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በመጠበቅ መልካም አስተዳደርን እናስፍን፤
3. በቤተ ክርስቲያን ስም የሚሰበሰብ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው፣ የማትቆጣጠረውና የማታዝበት ገንዘብና ሀብት ሊኖር አይገባም፤
4. በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ያልታቀፈና ለቤተ ክርስቲያን የማይታዘዝ ማኅበር በቤተ ክርስቲያን ስም ተደራጅቶ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ ስለሆነ፣ በሕግ ማስተካከል አለብን የሚሉትን ነው ፡፡
ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን በግልጽ አውቆ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወቅታዊ ችግር በመፍታት ረገድ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ፣
እንደዚሁም በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ያሉትን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ልትመሩ ይገባችኋል ብሎ እንዲመክራቸው፣
እነዚህ ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ተጽዕኖ በመፍጠር ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ አሜን ፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም፤ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
{flike}{plusone}