የ2007 ዓ.ም የደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ
በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን ሲከበር የቆየው የመስቀል ደመራ በዓል በዘንድሮውም ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ክቡር አቶ አባተ ስጦታው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ከተለያዩ አህጉራት የመጡ ጎብኚዎች፣ካህናት፣የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲሆን በተረኛው ደብር በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ለበዓሉ ተስማሚ የሆነ ያሬዳዊ መዝሙር ቀርቦአል ከክክፍለ ከተማ በተውጣጡ ወጣቶች መንፈሳዊ ትርኢት ቀርቦአል በማያየዝም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ፣
– በሀገራችን እና በመላው ዓለም የምትኖሩ ልጆቼ፣የሀገራችንን ዳር ድንበር በመጠበቅና በማስከበር በየዘርፉ ያላችሁ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ የተኛችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ በመስቀል ላይ በተከፈለው መስዋዕትነት የሰውን ልጅ ከኃጢአት ፍዳ የታደገ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ2007 ዓ.ም በዓለ መስቀል አደረሳችሁ፡፡
ወመነና ለሀፍረተ መስቀል ( ዕብ12፡-2) ተብሎ እንደተጻፈው በመስቀል ላይ የተከናወነው እና የተከፈለው ዋጋ ድንገተኛ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢተ ነቢያት የተነገረ ነው፡፡
የመስቀሉ ሥራ የማዳን ሥራ ነው፡፡
የጌታ ደስታ ከድኅነተ ምዕመናን ጋር የተያያዘ ነው (ዮሐ 15፡-11) የሰውም ደስታ የድኅነት ባለቤት ሆኖ መገኘት ነው፡፡ መስቀል የሚለው ቃል ብዙ ትርጓሜ ቢኖረውም ሁለት አበይት ነገሮችን ማየት ይቻላል፡፡ ይኸውም በምስጢራዊ ትርጉሙ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መስዋዕት በመሆን በኃጢአት የተበከለውን ዓለም ማዳኑን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዓለም በክርስቶስ መስቀል ዳነ ሲል ሰው በክርስቶስ መስዋዕትነት መዳኑን ያመለክታል፡፡ መስቀል ኃይላችን ነው፣መስቀል ቤዛችን ነው፣መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ ከመስቀሉ በቀር ሌላ የምንመካበት ነገር የለንም የሚሉት ኃይለ ቃላት መዳናችንና ማሸነፋችን ነው፡፡ በሌላ በኩል መስቀል የመስዋዕትነት ትምህርት ወይም አርማ ነው፡፡ የክርስቶስ ኃይል በመስቀሉ ላይ ስለሚአደረጉት ብዙ ተአምራት ያደርጋል፡፡ እኛም በመስቀሉ እንፈወሳለን እንባረካለንም መስቀልን ማክበር ክርስቶስን ማክበር ማለት ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት በተጀመረበት ዘመን የነበሩ ሰዎች የክርስቶስን መስቀል በመቅበርና በመሰወር የተነሱበት ምክንያት መስቀሉ የመፈወስ ስልጣን በማሳየቱ ነው የመስቀሉ መገኘት ኢአማንያንን ያሸማቀቀ ክስተት ነበር፡፡
የመስቀሉ አዳኝነት እስከ አሁን ድረስ ቀጥሎአል የቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችን ካወረሱን መንፈሳዊ ውርስ አንዱ በዓለ መስቀልን እያከበሩ በሃይማኖት ፀንተው መኖርን ነው፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማንያን በየአመቱ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በምናከብረው የመስቀል በዓል አማካኝነት የክርስቶስን አዳኝነት ለዓለም እንመሰክራለን በዚህም ዓለምን ወክሎ በሚገኘው የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
የመስቀል በዓላችን ያሬዳዊ ዜማችንና ብቸኛው ፊደላችን ልዩ የሆነው የዘመን አቆጣጠራችን የዓለም አቀፉ ተቋም ዩኒስኮ እንዲመዘግባቸው የማስተዋወቅ ሥራ ለመስራት ጥሪአችንን እናስተላለፍላን፡፡
የዘንድሮው የመስቀልን በዓል የምናከብረው ልማታዊ እና ሰላማዊ ተልዕኳችንን ከግብ ለማድረስ ቃል በመግባት ነው፡፡ እየተገነቡ ያሉት ህንፃዎች የአንድነታችን መገለጫዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም ሁላችንም አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን በዕኩልነት እና በመከባበር ለአንዲት ሀገር መነሳት አለብን በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ ትምህርታዊ ማብራርያ ከሰጡ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው የመስቀል ደመራ አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች በቅርስነት መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚገኘው ጠቀሜታ ባሻገር የሀገራችንን መልካም ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አወንታዊ በሆነ መልኩ በመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚኖረው ይሆናል፡፡ ከቱሪስት መስህብነት ባሻገር በዓሉ ከቀድሞ በተሻለ እንክብካቤ የሚደረግለትና ለትውልድ እንዲተላለፍ ዕገዛ እንደሚሰጥ ፅኑ እምነት አለኝ ፡፡ የሀገራችን መንግሥት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ልዩ ልዩ የማይዳሰሱ ቅርሶች በቅርስነት እንዲመዘገቡ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት በድምቀት ሲአከብሩት የኖሩት ሃይማኖታዊ በዓል ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቶ የሀገራችንን ገፅታ በቱሪዝም ልማት ይቀይራል በኢፊድሪ ሕገ መንግሥት በተረጋገጠው የእምነት ነፃነት መሠረት ሀገራችን ሕዝቦች በዓላትን እንደ እምነታቸው ማክበር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ሲባል አንዱ ባንዱ ላይ ጣልቃ ሳይገባ የየራሳቸውን ሥራ እንዲፈጽሙ የሚአደርግ እንጂ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚአደርጉት ተሳትፎ የሚደነቅ ነው፡፡ ይህንንም አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል፡፡ የመከባበርና የመቻቻል አኩሪ ባህላችን ማውሳት አንዱ ጉዳይ ሆኖ ዛሬ በዓለም ካሉና በስልጣኔ ካደጉ ሀገራት እኩል የሀገራችንን ስም ለማስጠራት በመንግሥታችን የተጀመረውን ፀረ ድህነት ትግል በእልህና በወኔ እንዲሁም በታላቅ ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት ለማሳካት መረባረብ ይኖርብናል በማለት ሰፋ ያለ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ደመራውን በመባረክ እና ችቦ በመለኮስ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡
{flike}{plusone}