የአዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት በ2006 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከፍተኛ የሆነ የልማት እድገት አስመዘገበ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያያን የአዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት በ2006 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከፍተኛ የሆነ የልማት እድገት ማስመዝገቡ ጥቅምት 7/2007 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ በተካሄደው 32ኛው የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የቀረበው ጠቅላላ የሥራ ዝረዝር ሪፖርት ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
“እስመ አነ አእመርኩ ከመ ዓቢይ እግዚአብሔር፡፡ ወአምላክነሂ እምኩሉ አማልክት ኩሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር” መዝ. ፻፴፬ ÷ ፭
“ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ አውቄአለሁና በሰማይ በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ” መዝ.134 ÷ 5
• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
• ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
• ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና በትግራይ ክልል የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
• ክቡር ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሰ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ
• ክብራን የመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች
• ክብራን የየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና ልዑካን
• ክቡራን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ባልደረቦቼ የየዋና ክፍል ኃላፊዎችና የ7 ክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጆች
• ክቡራን የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ም/ሊቃነ መናብርት
• የተከበራችሁ በዚህ ታላቅና ዐብይ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ የጉባኤው አባላትና ታዳሚዎች በሙሉ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2006 ዓ.ም የሥራ ዘመን በ7 ክፍላተ ከተማና በሥሩ በሚገኙ ገዳማትና አድባራት በበጀት ዓመቱ በሀገረ ስብከታችን የተከናወኑ ዓመታዊ የሥራ ክንውን የሚገልጥ ሪፖርት እንድናቀርብ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በቁጥር 3203/7628/06 በ29/09/2006 ዓ.ም ተጽፎ በደረሰን መመሪያ መሠረት የቀረበ አጭር ሪፖርት ነው፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተላለፈው የሥራ ዕቅድ እንዲሁም ሀገረ ስብከቱ በራሱ በነደፈው መርሐ ግብር መሠረት በበጀት ዓመቱ የሥራ ዘመን በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙት 7 ክፍላተ ከተማ እዲሁም ገዳማትና አድባራት የተባበረ ጥረት ከምጊዜም የተሻለ እጅግ አመርቂ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ይህም ስኬታማና ውጤታማ ሥራ ሊከናወን የቻለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ልዩ ሀገረ ስብከታቸው በመሆኑ በየጊዜው በሚሰጡት አባታዊ መመሪያ እና ሀገረ ስብከቱ በየዕለቱ በሚያደርገው ጥብቅ ክትትልና አመራር እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ፣ የክፍለ ከተማው ሠራተኞች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና መላው ሠራተኞች በጋራ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የተገኘ ውጤት ነው፡፡
እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ከተማ የፌዴራል መንግሥት መዲና፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ርእሰ መንበር መገኛ፣ የአፍሪካና የልዩ ልዩ ክፍላተ ዓለማት ዲፕሎማት መናኸሪያ በሆነቸው በዚች ከተማ ውስጥ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት የእነዚህ ሁሉ ተቋማት ማጌጫ አብዛኞቹ በራሳቸው በገዳማቱና አድባራቱ የተገነቡና የተንቆጠቆጡ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ተውበው በልማት ውጤቶች አሸብርቀው የመላዋ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማሳያ ሆነዋል፡፡
እንዲሁም ከተማዋ ሀብታሞችና ደሀዎች፣ ምሁራንና፣ አላዋቂዎች ቅዱሳን ጸሎተኞችና አጥፊዎች፣ ፖለቲከኞችና ስለፖለቲካ መስማት የማይፈልጉ ግለሰቦች፣ ባለሥልጣናትና ሥልጣን የሌላቸው አገልጋዮችና ተገልጋዮች በጋራ የሚኖሩባት ዥንጉርጉር ከተማ ናት፡፡ ይህንኑ አኗኗር ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ልዩነታችን ውበታችን መሆኑ የሚሰመርበት ጉዳይ እንደሆነ በመግለጽ አንዱ የሌላውን ሃይማኖት ማንነትና ባህል በማክበር በጋራ በእኩልነት የምንኖርበት የፌዴራል ወይም የጋራ ከተማችን መሆኗንና የውጭ ሀገራት ዜጎች ከሚመለከተው አካል ፈቃድ በማግኘት ሊኖሩ እንደሚችሉ ሕጉ ይደነግጋል፡፡
በዚህ ሁሉ የተከበበው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብዛት ያላቸው ካህናትና ወጣቶች ሥራ ለማግኘት የሚጎርፉበት በችግር የተከበበ ጽ/ቤት ነው፡፡
ይህንን ውስብስብ ችግር በመቋቋም በልማት፣ በሥልጣኔ፣ በመንፈሳዊ በማህበራዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚጠበቀው ተልእኮ በተቻለ አቅምና መጠን ተከናውነዋል፡፡ በዚህ መሠረት የበጀት ዘመኑን ዓመታዊ ክንውን ዝርዝር የሚተነትነውን ሪፖርት ማለትም፡-
• ሰንበት ት/ቤቶችን
• የካህናት አስተዳደርን
• የትምህርትና ማሰልጠኛን
• የዕቅድና ልማትን
• የቅርስና ቱሪዝምን
• የቁጥጥር አገልግሎትን
• የመንፈሳዊ ፍ/ቤትን
• የጠቅላላ አገልግሎትን የተመለከተ ዝርዝር ዘገባ በጊዜውና በሰዓቱ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ያቀረብን ስለሆነ ጊዜ ለመቆጠብ ሲባል እንዳልፈው ይፈቀድልኝ፡፡
ለዚች አነስተኛ ደቂቃ ለዚህ የተከበረ ጉባኤ የመጥናል ያልነውን ዋና ዋና ሐሳብ ብቻ ለማቅረብ እንሻለን፡፡ በዚሁም መሠረት፡-
1. ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ፡– የቤተ-ክርስቲያኗ ዋና የሥራ ዘርፍ እና የዓላማዋ ማስፈፀሚያ የሆነው ስብከተ ወንጌል እጥፍ ድርብ በሆነ በተትረፈረፈ ሰባክያነ ወንጌል በዘወትር ፣ በሳምንት፣ በወርኃዊና ዓመታዊ ክብረ በዓላት እንዲሁም በአንድነት ልዩ ጉባኤያት በቃለ እግዚአብሔር የተቀመመ የክርስቶስ የምስራች ወንጌል ለምእመናን በበቂና በአስተማማኝ ሁኔታ ደርሷል ብለን እናምናለን፡፡ በተጨማሪም ያልተፈቀደላቸው መምህራንና ሰባክያን እዳያስተምሩ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል፡፡
2. በሰው ኃይል አስተዳደር ሥራ ዘርፍ በኩል፡- በየገዳማቱና አድባራቱ ያሉት አገልጋዮች ብዛት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም ቀላል ቁጥር ያልሆኑ አድባራትና ገዳማት ያለው የሰው ኃይል ከመጠን ያለፈ በመሆኑ እስከ አራት ፈረቃ ድረስ ተደልድለው ለናፍቆት ያህል የሚያገልግሉበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ለ11 ወራት ያህል አዲስ ቅጥር እንዳይፈፀም በመደረጉ በመጠኑም ቢሆን የበጀት ጫና ቀንሷል፡፡ ለመቀጠር በሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና በየአጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚኮለኮሉ ደጅ ጠኚዎች አዲስ ቅጥር መቆሙንና ሥራ ፈተው እንዳይቆሙ አማራጭ እንዲፈልጉ በማሰናበት፤ በአንጻሩ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በልዩ ልዩ ምክንያት በጥፋትም ሆነ ያለጥፋት ከሥራ ተፈናቅለው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን አደጋ ላይ ጥለው የነበሩ ዜጎችን ዳቦ እንዲያገኙ በማሰብ መረጃቸውን በኮሚቴ በመመርመር እንደሙያቸውና ችሎታቸው በተገኘ ክፍት ቦታ እንዲመደቡ በአስተዳደር ጉባኤ በመወሰን ከ80 በላይ የሚሆኑ ከሥራ ውጪ የነበሩ ሠራተኞችን እንጀራ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
3. የሕግ አገልግሎትን በተመለከተ፡- በበጀት ዓመቱ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች 162 ክሶች ቀርበው ከዚህ ውስጥ 133 ክሶች ለሀገረ ስብከታችን ተወስነዋል፡፡ ቀሪዎቹ በይግባኝ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ መካከል ለመጥቀስ ያህል፡-
ሀ. የመሪ ቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ያለበት ቦታ ካርታ እንዲመክን ተደርጎ ቦታው ተሰጥቶኛል የሚሉት ጊፍት ሪል እስቴት ብር 12,000,000.00 (አስራ ሁለት ሚሊየን ብር) ካሣ ከፍለን ቤተ ክርስቲያኑን እንድናፈርስ ሪል እስቴቱ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ መስርቶብን እስከመጨረሻው በመከራከር የተጠየቀው ካሣ ቀርቶ የመከነው ካርታ ጸድቆልን ኪሣራ እንዲከፈለን ተወስኖልን የፍርድ ባለመብት ይሆናል፡፡
ለ. ሀገረ ስብከቱ ከሚያከራያቸው ሱቆች መካከል በሱቅ ቁጥር 10 የተከራዩ ግለሰብ ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ያልከፈሉት ውዝፍ ኪራይ ብር 170,000.00 (አንድ መቶ ሰባ ሺህ ብር) በሱቅ ውስጥ ያሉት ንብረቶች በጨረታ ተሽጠው እንዲከፍሉ ተወስኖልናል፡፡
ሐ. ለዚህ ታላቅ ጉባኤ ሊቀርብ የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ለዘመናት አለመግባባት ነግሦ ጭቅጭቅ በዝቶ በፍ/ቤት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ደርሶ መቋጫ ያላገኘው የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅ/ማርያምና ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል ውዝግብ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ከሰጠበት በኋላ ሀገረ ስብከቱ ገለልተኛ የሆኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ተቋቁሞ በተደረገ ሰፊ ውይይት ለውዝግቡ ምክንያት የነበሩት ሰንበቴ ቤቶች የጋራ መተዳደሪያ ደንብ ወጥቶ በቤተ ክርስቲያኑ እዝና መመሪያ ሥር ለመተዳደር ተስማምተው ለመጨረሻ ጊዜ እልባት አግኝተዋል፡፡ ለዚህ ውጤት የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደርና የወረዳው አስተዳደር ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
4.የሰበካ ጉባኤ እንቅስቃሴን በተመለከተ፡- በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ከሚገኙ 174 ገዳማትና አድባራት መካከል 56 የሰበካ ጉባኤ አባላት በአዲስ ተመርጦ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ በ4 አብያተ ክርስቲናት የሚገኙ የሰበካ ጉባኤ አባላት የቃለ ዓዋዲን መመሪያ ጠብቀው ባለመስራታቸው በሌላ አባላት እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ በ5 ሰበካ ጉባኤ ባልነበራቸው አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በአዲስ መልክ ሰበካ ጉባኤ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
5. መሬት ከወርቅ እና ዕንቁ በላይ ግምት በተሠጠበት በአዲስ አበባ ከተማ ካርታ ለሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት በተቋቋመ ኮሚቴ አማካይነት 204 የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጥ ተደርጎ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኙ ሆኗል፡፡
በዚህ የካርታ አሠጣጥ ሂደት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤትና በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመውን ኮሚቴ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ በኩል በመጋቤ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዘማርያም የሚመራውን ኮሚቴ በቤተ ክርስቲያኗ ስም እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ የምሥጋና መርሐ ግብር እንደሚኖር በአስተዳደር ጉባኤ መወሰኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በከተማው ዕድገትና ስፋት በመነሳት 8 አዳዲስ አብያተክርስያናት ተመሥርተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን የጉባኤ ተሳታፊዎች
በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች በከፊል
1. ትምህርት ቤት ያላቸው ገዳማትና አድባራት ከትምህርት ቤት ገቢ ላይ 20% ክፍያ ላይ ከሀገረ ስብከቱ ጋር መጠነኛ አለመገባባት መኖሩ፣
2. ከሃምሳ አምስት በላይ ካርታዎች ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ከከተማዋ አስተዳደር በተሰጠ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ግንባታ ማካሄድ የማይቻልና ግሪን ኤርያ ስለሚል ህንፃ ቤተ ክርስቲያንና የልማት ግንባታ ማካሄድ አለመቻላቸው፣
3. በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ክልል ውስጥ አንዳንድ ነዋሪዎች በመኖራቸውና አቤቱታ ለመንግሥት በማቅረባቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ላይ ጥያቄ መነሳቱ፣
4. በየትኛውም መ/ቤት የሌለ ሊኖርም የማይገባ በሀገረ ስብከቱ ግን ቅጥር፣ ሹመት ሥራ ምደባ ፣ እድገት በማመልከቻ ሲፈፀም ባህልና ሕግ ሆኖ የኖረ ሲሆን ይህ አሠራር ካልቆመ በስተቀር መልካም አስተዳደር ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የዝውውር ጥያቄ በተመለከተ እንደሁኔታው ችግሩ አሳማኝ ሆኖ ሲገኝ ሊቀርብ ይችል ይሆናል፣
5. ለዳኝነት ትልቁ እንቅፋት ሆኖ የተገኘውና መልካም አስተዳደር እንዳይመጣ ያደረገው ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች የሰውን ስም በውሸት ካላጠፉ ሕገወጥ ሥራና ሕገ ወጥ ጥቅም ካላገኙ አትፀድቁም የተባሉ እስከሚመስሉ ድረስ ኃጢአትን እንደጽድቅ የተለማመዱ ግለሰቦች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መኖሩ፡፡
ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ መፍትሔዎች
ሀገረ ስብከቱ በርካታ ችግሮች ቢፈታተኑትም በተለያዩ ጊዜያት የሀገረ ስብከቱንና የክፍላተ ከተማ እንዲሁም የገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎችን ስብሰባ በመጥራትና ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በእነዚህ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት አስተዳደር እንዲኖር ተደርጓል፡፡
1. ት/ቤት ያላቸው ገዳማትና አድባራት 20% ከገቢ እንዲከፍሉ ሀገረ ስብከቱ ጠንክሮ የሠራ ቢሆንም በዋናው መ/ቤት በኩል መመሪያ እንዲሰጥበት ጥያቄ ቀርቧል፡፡
2. የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ግሪን ኤርያ የተባለባቸው 55 ገዳማትና አድባራትም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንዲሰሩና ህንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲገነቡ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ፊርማ ለክቡር ከንቲባ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም ቅዱስነታቸው የሀገረ ስብከቱ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ክቡር ከንቲባውን ጠርተው አንጋግረው የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ተደርጓል፣
3. በቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ በስምምነት እንዲለቁ ፈቃደኛ ያልሆኑት ደግሞ በሕግ ተገደው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
የዘመኑን የፋይናንስ እንቅስቃሴ በሚመለከት
መኪናን መሪ መርከብን መልህቅ እንደሚዘውረው ሁሉ ዓለምን ገንዘብ እንደሚያሽከረክረው የታመነ ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችንም ዓለምን ለማጣፈጥ ከዓለም ውጪ መሆን ስለማትችል ትውልዱ በሚጠበቀው መንገድ ተልእከዋን ለማከናውን እንድትችል ገንዘብ እንደሚያስፈልጋት አጠያያቂ አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዘመኑ ገንዘብ አሰባሰብ ተግባር ላይ ቋሚ ተሰላፊ በመሆን ከሥራ አጋሮቹ ገዳማትና አድባራትጋር ጥብቅ የሥራ ቅንጅት በመፍጠር በየወሩና በየ3 ወሩ ስብሰባና ሥምሪት በማድረግ ሲያከናወን ቆይቷል ቅዱስነታቸውና ጠቅላይ ጽ/ቤቱም በየጊዜው ክትትል አድርገው መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መሠረት፡-
የገዳማትና አድባራት ጠቅላላ የዘመን ገቢ ብር 445,596,486.80 (አራት መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ አራትመቶ ሰማንያ ስድስት ብር ከማኒያ ሳንቲም) ሆኖ ከዚሁ ውስጥ የሀገረ ሰብከቱን የሂሳብ እንቅስቃሴ እንደሚከተለው ቀርቧል ፡፡ የጉባኤ አባላት በመጽሔቱ ላይ ያለውን ንባብ እንዲታረቅ ገጽ 29 ላይ የተመዘገበው ሳይሆን በገጽ 35 በሰንጠረዡ ላይ የተመዘገበው ትክክል እንደሆነ እንድትረዱልን፡፡
ሀ. የዘመኑን ገቢ በተመለከተ
|
ከ01/11/05 – 30-10-06 ዓ.ም ከአድባራት የተሰበሰበ |
ብር |
75,977,896.19 |
|
ከ01/11/05 – 30-10-06 ዓ.ም ከቤት ኪራይ የተሰበሰበ |
ብር |
1,308,727.30 |
|
ከ01/11/05 – 30-10-06 ዓ.ም ከቤት ኪራይ ዋስትና |
ብር |
145,830.51 |
|
ከ01/11/05 – 30-10-06 ዓ.ም ከሽያጭ የተሰብሰበ |
ብር |
1,327,786.23 |
|
ከ01/11/05 – 30-10-06 ዓ.ም ወደ ባንክ ተመላሽ |
ብር |
82,184.07 |
|
ከ01/11/05 – 30-10-06 ዓ.ም ከባንክ የመጣ |
ብር |
49,442,346.80 |
|
በጥሬ ገንዘብ በሰደኑ የዞረ |
ብር |
49,673.86 |
|
በባንክ የዞረ |
ብር |
40,526,411.81 |
ለ. ወጪን በተመለከተ
|
ለደመወዝ |
ብር |
5,368,736.75 |
|
ሥራ ማስኬጃ |
ብር |
336,515.84 |
|
ሞ/ሞዴል ህትመት |
ብር |
140,000.00 |
|
ልዩ ወጪ |
ብር |
8,636,880.02 |
|
ለ2005 ዓ.ም 65% በበጀት ዓመቱ የተከፈለ |
ብር |
14,410,151.74 |
|
ለዘመኑ 65% የተከፈለ |
ብር |
49,385,632.52 |
|
ለዘመኑ ከልማት ገቢ 65% የተከፈለ |
ብር |
850,672.75 |
|
ለክ/ከ ሥራ ማስኬጃ |
ብር |
1,714,416.65 |
|
ወደ ባንክ የተላከ |
ብር |
42,622,425.76 |
መሆኑን ሂሳቡ ያሳያል፡፡
ሐ. የ2005 እና የ2006 ዓ.ም የገቢ ማነፃፀሪያ
|
የ2005 የዘመን ገቢ ለመ/ፓ/ የተከፈለ 65% |
44,734,360.65 |
|
የ2006 የዘመን ገቢ ለመ/ፓ/ የተከፈለ 65% |
50,236,305.27 |
|
ልዩነት የዘመኑ ብቻ |
5,501,944.61 |
|
ውዝፍ በ2005 ዓ.ም የገባ ብር |
10,522,290.43 |
|
ውዝፍ በ2006 ዓ.ም የገባ ብር |
14,410,151.74 |
መ. የዘመኑ ገቢና ውዝፍ ተደምሮ (ከ2005 እና 2006 ጥቅል ሲነፃፀር) |
||
|
በ2005 ዓ.ም በጠቅላላ 65% ብር |
55,256,651.08 |
|
በ2006 ዓ.ም በጠቅላላ 65% ብር |
64,646,457.01 |
|
ልዩነት በዕድገት ብር |
9,398,805.92 |
(ዘጠኝ ሚሊየን ሦስት መቶ ዘጠና ስምንት ሺህ ስምንት መቶ አምስት ብር ከዘጠና ሁለት ሳንቲም) ዕድገት በማስመዝገብ 64,646,457.01 (ስልሳ አራት ሚሊየን ስድስት መቶ አርባ ስድስ ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሰባት ብር ከዜሮ አንድ ሳንቲም) ገቢ ማድረጋችንን ስንገልጽ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንዲሁም በመላው የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ስም ታላቅ ኩራትና ክብር ይሰማናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የሰበካ ጉባኤ አባላት የቢሮ ሠራተኞች ጭምር የቃለ ዓዋዲን መመሪያ በማክበር የጠቀስነውን ገንዘብ በጊዜው ገቢ በማድረጋቸው ይህ ጉባኤ እንዲያመሰግንልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በያዝነው በጀት ዓመትም ቢሆን ካለፈው የበለጠ መሥራት እንደሚገባን ከወዲሁ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
• ከዚሁ 64,646,457.01 (ስልሳ አራት ሚሊየን ስድስት መቶ አርባ ስድስ ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሰባት ብር ከዜሮ አንድ ሳንቲም) ገቢ ካደረግነው በተጨማሪ ከሀገረ ስብከቱ 35 % ድርሻ ላይ ለመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) የበጀት ዱጎማ ገቢ አድርገናል፡፡
• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰሜን ጎንደር ላደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ለሚገኙ ጉባኤ ቤቶች ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) ድጎማ አድርገናል፡፡
• ለሳውዲ ዓረቢያ ተመላሾች እርዳታ የሚውል 1,500.000.00 (አንድ ሚሊየን አምስት መቶ ሺህ)
• ለርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ መጻህፍት ወመዘክር ግንባታ ብር 1,200,000.00 (አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ብር)
• ለዳውሮ ሀገረ ስብከት በብር 90,277.50 (ዘጠና ሺህ ሁለት መቶ ሰባሳበት ከሃምሳ ሳንቲም) ለስብከተ አገልግሎት የሚውል 1 ሞተር ሳይክል ገዝተን አበርክተናል፡፡
• ለ2006 ዓ.ም የበዓለ ትንሣኤ ለተቸገሩ ወገኖች እርዳታ ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) በቅዱስነታቸው አማካኝነት ድጋፍ ተደርጓል፡፡
• ለብፁዓን አባቶች ማረፊያ ቤት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ህንፃ መብራት ጄኔረተር መግዣ ብር 259,502.00 (ሁለት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ሁለት ብር)
• በአዋሳ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ለሚደረገው ስብሰባ ጉዞ የተከፈለ ብር 20,000.00 (ሃያ ሺህ ብር)
• ለምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጎዛምንና አነደድ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ለደረሰባቸው የእሳት ቃጠሎ አደጋ እርዳታ ብር 20,000.00 (ሃያ ሺህ ብር)
• ለታእካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ድጎማ ብር 235,531.80 (ሁለት መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ አምስት መቶ ሰላሳ አንድ ብር ከሰማኒያ ሳንቲም)
• ለሰዋሰው ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ብር 102,060,00 (አንድ መቶ ሁለት ሺህ ስልሳ ብር)
• ለ2006 ዓ.ም የደመራና የጥምቀት በዓል ማክበሪያ አገልግሎት የሚውል ለጠቅላይ ቤተክህነት ብር 465,767.28 (አራት መቶ ስልሳ አምስት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ሰባት ብር ከሃያ ሳንቲም) ጠቅላላ ድምር 5,093,138.58 (አምስት ሚሊየን ዘጠና ሦስት ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ስምንት ሺህ ከሃምሳ ሳንቲም) በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ትዕዛዝ ወጪ አድርገን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አድርገናል፡፡
• በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ለልማት ቀዳሚነቷን ለማሳየት ባለፈው ዓመት ለሕዳሴ ግድብ የሚውል የብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) ከሠራተኛው የአንድ ወር ደመወዝ ብር 164,608.40 (አንድ መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ስምንት ብር ከአርባ ሳንቲም) ቦንድ ግዢ ከተፈፀመው ሌላ በዘንድሮም በጀት ዓመት ብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) ቦንድ እንዲገዛ አፈፃፀም ላይ ይገኛል፡፡
• በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዝ ብር 388,165.76 (ሦስት መቶ ሰማንያ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ስልሳ አምስት ብር ከሰባ ስድስት ሳንቲም) እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ ከሀገረ ስብከቱ ድርሻ 35% ውስጥ ከላይ ለተገለፁት አካላትና አገልግሎት እንዲሁም ለቦንድ መግዣ ጭምር ወጪ የተደረገው ብር 6,481,304.34 (ስድስት ሚሊየን አራት መቶ ሰማኒያ አንድ ሺህ ሦስት መቶ አራት ብር ከሰላሳ አራት ሳንቲም) ነው፡፡
• ቦንዱን በሚመለከት ገዳማት አድባራት መመሪያ ተላልፎ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
• በዘንድሮ በጀት ዓመት የሂሳብ አመዘጋገባችን ወይም ከላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ብቻ የገባ እንጂ የአሁኑን የሐምሌ፣ የነሐሴ፣ የመስከረም ገቢዎች ያልጨመረና በሀገረ ስብከቱ እጅ የሚገኝ መሆኑን እየገለጽን ካሁን በኋላ የበጀት መደበላለቅ እንደማይኖር መረዳት ይቻላል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን የጉባኤ ተሳታፊዎች
የ2007 ዓ.ም የሥራ ዘመን እቅድ
1. ለወደፊቱም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡
2. የአጥቢያውን ገቢ በየአርዕስቱ በማሳደግ የሀገረ ሰብከቱንም ድርሻ በወቅቱ እንዲገባ ያለሰለሰ ጥረት እናደርጋለን፡፡
3. በአሁኑ ጊዜ በገዳማቱና አድባራቱ የሰው ኃይል ክምችት እያለ በብዛት የሰው ኃይል መጨመር በአበው አነጋገር የበላችው ያገሣታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል እንደተባለው ባለው ሠራተኛ ላይ ሌላ ሠራተኛ መጨመር ቤተ ክርስቲያኒቱን በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ቅጥርን እንደእስካሁኑ ጥናቱ እስከሚያበቃ ድረስ በማዘግየት ሙያተኞች ባስፈለጉ ጊዜ በማስታወቂያና በውድድር እንዲፈጸም ማድረግና የሀገረ ስብከቱን መልካም ገጽታ ጥላሸት የሚቀባውን ሀሜት ለማጥፋት ከተለያዩ ከቤተክርስቲያኒቱ ተቋማት ለሚመረጡና ሕጋዊ ዕውቅና ከደንብ ጋር ለሚሰጣቸው የኮሚቴ አባላት ሥራውን ማስተላላፍ ፣
4. ሀገረ ስብከቱ የተጠናና አዋጭ የግንባታ ፕሮጀክት ቀርጾ ቦታ በማመቻቸት ወደ ኢንዱስትሪ ሊያሸጋግር የሚችል በመልሶ ማልማት ተግባር ውስጥ ገብቶ ባለው ገቢ እና ተጨማሪ ገቢ በማሰባሰብ ሁለገብ ሕንፃ መገንባት፣
5. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ራሱ እንደ ሼር ሆለደር ሆኖ ሀብት ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር አዋጪነቱ የተጠና ፋብሪካ መትከልና ለቤተክርስቲያኗ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መክፈት በመሆኑ በተለይም ግማሽ ቀን እየሠሩ ግማሽ ቀን ጊዜ ለሚያባክኑ አንድ ሣምንት ቀድሰው 3 ሳምንት ለሚያርፉ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሠራተኞችና አገልጋዮች በትፍር ጊዜያቸው በአቅማቸው እና በየሙያቸው በፋብሪካው እየሰሩ ገቢያቸውን የሚያሳድጉ እንዲሆኑ ዕድል መፍጠር ፡፡
6. በረጅም ጊዜ እቅድ ሀገረስብከቱና አብያተ ክርስቲያናቱ ዋናው መስሪያቤት ጭምር በተጠና መንገድ ቅዱስ ሲኖዶስን በማስፈቀድ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው ሁኔታ ባንክ እንዲኖረን ማድረግ፡፡
7. የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የየራሳቸው ቋሚ ቢሮ እንዲኖራቸው ከመንግስትና ከአብያተ ክርስቲያት ጋር በመነጋገር ቢሮ መገንባትና ከኪራይ ነፃ መውጣት፡፡
8. የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላገኙ ገዳማትና አድባራት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር አጠናክሮ መሥራት፡፡
9. ማንኛውንም ሥራ ለማከናውን በቅድሚያ የልማት አስተሳሰብ ሲበለጽግ በመሆኑ ለሠራተኞች እንደየሙያቸውና ደረጃቸው ልዩ ልዩ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማካሄድ የሚሉ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በመጨረሻም ብር 64,646,457.00 (ስልሳ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ አርባ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሰባት ብር) የያዘውን የባንክ እስሊፕ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እንዲያስረክቡልን በታላቅ አክብሮትና ትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ንባርኮ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሜን
ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም
{flike}{plusone}