ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም. ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

0908

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የተወደዳችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ሕዝበ ክርስቲያን በአጠቃላይ እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለ2006 ዓ.ም ጾመ ማርያም በሰላም አደረሳችሁ፡፡
‹‹ወዘሰ እንተ አንቀጽ ይበውእ ኖላዌ ዓባግዕ ውእቱ፤ በበሩ የሚገባ የበጎች እረኛ ነው›› (የሐ 10 ÷ 2)
በብሉይ ኪዳን የበጎች እውነተኛ እረኛ እንደሆነ በብዙ ስፍራ የተነገረለት መሢሕ አንድ ቀን በዓለም እንደሚገለጽና በጎቹን በትክክል እንደሚጠብቅ በሕዝበ እግዚአብሔር ዘንድ የታወቀና የታመነ ነበረ (ሕዝ 34 ÷ 1-24) ፡፡ እግዚአብሔር ያስቀመጠው ቀመረ ዘመን ሲደርስ እውነተኛው እረኛ ክርስቶስ በተነገረለት በር በኩል ወደዚህ ዓለም መጣ፤ ይኽ በር የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ማኅፀን ነበረ፤ (ሕዝ 44÷2-3) በኦርቶዶክሱ ዓለምና በሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የምንገኝ ክርስቲያኖች ቅድስት ድንግል ማርያምን ከእግዚአብሔር በታች፤ ከፍጡራን በላይ፤ ከፍ አድርገን የምናከብርበት ዋና ምክንያት ድንግል ማርያም የዓለም መድኅን የክርስቶስ መግቢያ በርና ለሰው ልጅ የድኅነት ምክንያት ስለሆነች ነው ፡፡
ከዚህም የተነሣ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የተነሡ ቅዱሳን ሊቃውንት ቅድስት ድንግል ማርያምን ‹‹አንቀጸ አድኅኖ ይእቲ አልባቲ ሙስና ማለትም ስሕተት ጥፋት የሌለባት የድኅነት በር ናት፤ ብለው በተደጋጋሚ ገልጸዋቷል፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በዜማ ድርሰቱ በዚህ ኃይለ ቃል ደጋግሞ አመስግኗታል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በር በመሆኗ ክርስቲያን ለሆኑ ምእመናን ሁሉ እናት ናት፤ ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ እርስዋ የክርስቲያን እናት፤ እኛ ክርስቲያኖችም የእርስዋ ልጆች በማድረግ አስተሳስሮናል (የሐ 19 ÷ 26-27) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅዱሳን ሐዋርያት  ጌታችን በነገራቸው ቃል መሠረት ድንግል ማርያምን  በእናትነት ተቀብለው በክብር ይከተሏት ነበር፤ ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይም አስከሬንዋን ራሳቸው ቀብረው የበረከቷ ተካፋይ ለመሆን በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 14 ቀን ሱባዔ ገብተው ፈጣሪን በጾምና በጸሎት ስለለመኑ ነሐሴ 14 ቀን የለመኑትን አግኝተው አስከሬንዋን በጌቴ ሴማኒ ቀብረዋል፤ ሆኖም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ
16 ቀን ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማያት አርጋለች፤ ቅዱሳን ሐዋርያትም ትንሣኤዋን በዓይን አይተው የበረከቷ ተካፋይ  ሆነዋል ፤
ይህንን ሐዋርያዊ ትምህርትና ትውፊት መነሻ በማድረግ በዓለም ያሉ ኦርቶዶክሳውያንና ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ  በየዓመቱ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ 15 ቀን በመጾም ነሐሴ 16 ቀን በዓለ ትንሣኤዋን በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊትና ጥንታዊት እንደመሆንዋ መጠን ከጥንት ጀምሮ ይህንን ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም ጠብቃ እስካሁን አቆይታለች፤ ለወደፊትም እስከ ዕለተ ምጽአት በዚሁ ይቀጥላል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
የቅድስት ድንግል ማርያምን በዓለ ትንሣኤ ምክንያት አድርገን የምንጸመው ይህ ጾመ ማርያም ለሀገራችን፤
ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ መዳንን፤ ምሕረትንና ይቅርታን ለማስገኘት ነው፡፡ የሃይማኖት ተልእኮ
ምን ጊዜም ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን ለጉዳት መዳረግ አይደለም፤ ሃይማኖት ተቀባይነትን ሊያገኝ፤
ለወደድና ሊከበር የሚችለው ለሰው ልጆች በሚሰጠው ክብርና የድኅነት አስተምህሮ ነው፤ ሃይማኖት
ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ተልእኮ በአግባቡ ማከናወን የሚችለው ሰላምን፤ እኩልነትን፤ መከባበርን፤
መረዳዳትን፤ ማስተዋልን ትዕግሥትንና ፍቅርን ማእከል አድርጎ ሲጓዝ ነው፡፡
ይህንን በሚቃረን መልኩ የሚጓዝ ሃይማኖት ባይኖርም የሃይማኖቱን ትክክለኛ አስተምህሮ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጉሙና የሃይማኖትን ካባ ያጠለቁ ግለሰቦች በየሃይማኖቱ ውስጥ አይጠፉም፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም የሰላምና የልማት ጠንቅ ሆነው ሰላማዊ ሕዝብንና እውነተኞች አማንያንን በማስቸገር የሚገኙት እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው፤ግለ ሰዎቹ የሃይማኖት ተልእኮ ፈጽሞ እንደሌላቸው ከምንም በላይ ግብራቸው ይመሰክርባቸዋል፤ ወደ ሃይማኖቱ መድረክ በእውነተኛው በር ሳይሆን በሌላ በር እየገቡ ከምንም በላይ ራሱን ሃይማኖቱን እየተገዳደሩት እንደሚገኙ ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡
ስለሆነም ‹‹በበሩ ሳይሆን በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ እውነተኛ የበጎች እረኛ አይደለም›› (የሐ 10 ÷1 ) ብሎ ጌታችን ባስተማረን መሠረት እንደዚህ ዓይነታቸውን ግለሰቦች ነቅተን ልንከላከላቸው ይገባል፡፡ የሃይማኖት በሮች እምነት፤ ምግባር፤ መታዘዝ፤ ትሕትና፤ በሕግና በሥርዓት መኖር፤ ሰላም፤ አንድነት፤ ፍቅር፤ ስምምነት፤ መተሳሰብ፤ መከባበር፤ ሥራ መውደድ፤ ከተንኮልና ከአስመሳይነት መራቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ የማስመሰል ተግባራት ሁሉ ማታለያ ከመሆን አልፈው የእውነተኛ ሃይማኖት መገለጫ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

እግዚአብሔር ከላይ የተገለጹት የሃይማኖት መገለጫ ፍሬዎችን ይዘንና ከማናቸውም ግብረ ኃጢአት ርቀን እርሱን በመፍራትና ለእርሱ በመታዘዝ እንድንጾም ይፈልጋል፡፡ እንደዚሁም የተራበውን በማጉረስ፤ የታረዘውን በማልበስ፤ የተቸገረውን በመርዳት እንድንጾም ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ይህ ነውና፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ይቀድስ አሜን አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኩስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም

{flike}{plusone}