በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት የያዝነው አርባ ጾም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲሆን ይህም ጾም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው ነው፡፡ ይህም ጾመ አርባ ወይም ዐቢይ ጾም በኦርቶዶክስ ተወሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ጾም ነው፡፡ ምክንያቱም በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ ጾም ስለሆነ ነው፡፡ ሌሎቹ አጽዋማት ቅዱሳን አበው ነቢያት እና ሐዋርያት የጾሙአቸው አጽዋማት ናቸው፡፡ አበው ነቢያት እና ሐዋርያት በጾሟቸው አጽዋማት በረከተ ሥጋን እና በረከተ ነፍስን ያገኙ በመሆናቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እነሱን አብነት አድርጋ አጽዋማቱን ታከብራቸዋለች፡፡
ወደ ተነሳንበት ዐቢይ ጾም ስንመለስ በዐቢይ ጾም ወራት ያሉትን ሳምንታት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በሰየማቸው ስያሜ መሠረት ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ ደበረ ዘይት፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስ፣ ሆሣዕና ተብለው ተሰይመዋል፡፡ እነዚህ ሳምንታት ራሱን የቻለ መድሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ አላቸው፡፡
ከሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ድረስ ያሉት ቀናት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሞተ ሥጋና ከሞተ ነፍስ ነፃ ለማውጣት የማዳን ሥራውን ያከናወነባቸው ቀናቶች ናቸው፡፡ እኛም እነዚህን ቀናቶች የምናስታውሳቸው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ የተቀበለውን መከራ እያሰብን የምናዝንበት ልዩ የሀዘን ጊዜ ነው፡፡ ከላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ በዳ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት በጾመበት ወቅት ታላላቅ ፈተናዎችን ያሰተናገደ በመሆኑ እና የፈታኙን የሰይጣንን ፈተና ድል ያደረገ በመሆኑ ይህንን ታሪካዊ ጾም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በቀመረ ድሜጥሮስ እየቀመረች በመጾም ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ አሁንም አየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡
ምንም እንኳን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው አርባ ሌሊት እና አርባ ቀን ቢሆንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐቢይ ጾም መጀመሪያ ዘወረደ በተባለው በመጀመሪያው አንድ ሳምንት በመጨመር እና በመጨረሻ ሳምንት ሕማማትን በመጨመር እና ለጾም በማድላት 55 ቀናትን ትጾማለች፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ዘይፈቅድ ያድኅና ለነፍሱ ለይግድፋ ወዘሰ ገደፋ ለነፍሱ በእንቲአየ ይረክባ፡፡
“መስቀሌንም የማይዝ በኋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ነፍሱን ሊያድን የወደደ ሰውነቱን በመከራ ይጣላት ስለ እኔ በመከራ የጣላትን በሕይወት ያገኛታል” /ማቴ 1ዐ ÷ 38 / ያለውን በማሰብ የደከሙ የጾሙ፣ የጸለዩ ፣መከራን የተቀበሉ አበው ቅዱሳን ዋጋ አንዳላቸው የሚያስረዳ ሲሆን ነገር ግን የማይጾሙና የማይጸልዩ፣ ስለ ክርስቶስ ብለው መከራ የማይቀበሉ ኃጥአን ፍዳ እንዳለባቸው አውቀው ሌት ተቀን እየተጋደሉ ሊኖሩ ይገባቸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖት እና ምግባር ተስማምተው፣ እንድ ሆነው የሚኖሩባት ናት፡፡ ከዚህ አንፃር ዋነኛው ተልዕኮአችን ምዕመናን በክርስቶስ አምነው የሃይማኖት ፍሬን አፍርተው በምድራዊ ሕይወታቸው ለሀገር ለወገን ብሎም ለራሳቸው የሚጠቅም ሥራ ሠርተው በመልካም ሥራቸው፣ በጸና እምነታቸው ዘለዓለማዊት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሱ ዘንድ ለዚህ የሚያበቃ ትምህርተ ወንጌል መስጠት ነው፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ሁላችንም ድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም የሚሆነው እንደጊዜው ሁኔታ ራሳችንን በትምህርተ ወንጌል አንፀን ምዕመናንን ከነጣቂ ተኩላ መጠበቅ ስንችል ነው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን በብዙ ልፋት እና ድካም ቤተ ክርስቲያናችንን ጠብቀው ለእኛ አስረክበውናል፡፡ በዚህ አኩሪ ሥራቸውም ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ በጸሎት ታስባቸዋለች፡፡ እኛም ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ተግተን መሥትራት ይኖርብናል፡፡
እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ የሠራነውን ሥራ መለስ ብለን ለማየት እና በሩጫችን ጊዜ ያጋጠሙን ችግሮች ካሉም በመወያየት ጠንካራ ጎናችንን አጉልተን ለመሄድና ተጋግዘን ቤተ ክርስቲያናችንን በሁሉም ዘርፍ ለማሳደግ ጥረታችንን መቀጠል ይኖርብል፡፡ በተለያየ ወቅት ደጋግመን እንደተነጋገርነው እግዚብሔር የወደደውን ሥራ ለመስራት የምንችለው ዛሬ ነው፡፡ ነገ እንሠራለን እንዳንል ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተገናገረው ነገ የእኛ አይደለም፡፡ ስለዚህ የእኛ የሆነው ቀን ዛሬ ስለሆነ ለነገ የሚባል ቀጠሮ ሳይኖር ዛሬውኑ ተግተን መሥራት ግዴታችን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የምታድገው ስብከተ ወንጌልን አጠናክረን ስንቀጠል፣ አብነት ትምህርት ቤቶችን ስናስፋፋ፣ ቅርሶቻችንን ስነጠብቅ፣ በኅብረት እና በፍቅር ስንሠራ ነው፡፡ እኛ በሙሉ ልብ ሆነን ለመሥራት ከተነሣሣን ዓለሙ ሁሉ ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ የጠየቅነውንም ሁሉ እናገኛለን፡፡
ቤተክርስቲናችን ጠይቃ ያጣችበት ጊዜ የለምና፡፡ ወደ ሀገር ስብከታችን ሁለገብ እንቅስቃሴ መለስ ስንል ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሚሰጠን አባታዊ መመሪያ መሠረት በመጀመሪያ የትምህርት ደረጃን መሠረት ያደረገ የሰው ኃይል አደረጃጀት በማድረግ ሥራና ሠራተኛ እንዲገናኙ አድርገናል፤ በርዕሰ ከተማውም ሰባት የክፍላተ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቋቁመናል፤ የፐርሰንት ክፍያም ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ ከፍ እንዲል ጥረት እያደረግን እንገኛለን፤ ካርታና ፕላን ለሌላቸው አድባራት እና ገዳማት ካርታና ፕላን እንዲያገኙ አድርገናል፤ ለሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ አድርገናል፤ ከሥራና ከደመወዝ የታገዱ ልዩ ልዩ ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አድርገናል፡፡
እነዚህ የዘረዘርናቸው ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ከዚህ ውጭ ዘርፈ ብዙ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ተከናውኖአል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እስከ አሁን ድረስ የተከናወኑትን የሥራ ክንውኖች በቸርነቱ እያገዘን እና እየረዳን የሠራነው በመሆኑ ለቸሩ አምላካችን ምስጋና እያቀረብን ለወደፊቱም ያቀድናቸውን የልማት እቅዶች ለፍጻሜ ያበቃን ዘንድ ልመናችንን እናቀርባለን፡፡ መጪው የሆሳዕና፣ የስቅለት እና የትንሣኤ በዓል የሰላምና የፍቅር በዓል ይሁንልን፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ሕዝባችን በቸርነቱ ይጠብቅልን፤ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን አሜን፡፡
አባ እስጢፋኖስ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
{flike}{plusone}