በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2ኛው ዙር የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ለጠናቀቁ የሒሳብ ባለሙያዎች አዲሱን አሠራር በተመለከተ የሥራ መመሪያ ተሰጠ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለዘመናት ሲሠራበት የነበረውን የሲንግል ኢንትሪ ሒሰብ አሠራር ወደ ደብል ኢንትሪ ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር መቀየሩን ተከትሎ በሥሩ ለሚገኙ ገዳማት እና አድባራት የሒሳብ ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ (የአቅም ግንባታ)ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር 30 የሒሳብ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁ እና ተመራቂዎቹም በተመደቡባቸው አብያተ ክርስቲያናት ሥራ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡
በዚህም ረቡዕ ታኅሣሥ 27 ቀን 2008 ዓ.ም በሁለተኛ ዙር የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና የወሰዱ የሒሳብ ባለሙያዎች፣ ተልከው ከመጡባቸው ገዳማት እና አድባራት የተጠሩ አለቆች እና ጸሐፊዎች በተገኙበት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና የሀገረ ስብከቱ ሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫኔ የሥራውን ሁኔታ እና የንብረት ቆጠራን አስመልክቶ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት አሠራሩ ለቤተ ክርስቲያን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተሰብሳቢዎቹ በርካታ ጥያቄዎች ተነሥተው ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ከተሰብሳቢዎቹ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል፡-
1.ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር (ደብል ኢንትሪ) ጥሬ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ንብረትን በተመለከተ እና በአጠቃላይ የአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ንብረት የሚታወቅበት የሒባብ ዓይነት ነው፡፡ ይህን ንብረት ለመቁጠር ወይም ለመገመት የሚመረጡ ሰዎች ማንነት ከሃይማኖት እና ከሥነ ምግባር አኳያ መታየት አለበት? ወይስ እንዴት ነው ሊሆን የሚችለው? ቢብራራልን?
2.በቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ ከበጎ አድራጊዎች በስጦታ የሚበረከቱ ንብረቶች አሉ፡፡ እነሱ በምን መንገድ ነው የሚገመቱት? ምክንያቱም የሚያመጣቸው ግለሰብ ንብረት እንጂ የገዛበትን ዋጋ ብዙ ጊዜ አይናገርም ሪሲትም አብሮ የማስረከብ ልምድ የለም፡፡ ይህስ እንዴት ነው መታየት ያለበት?
ሁል ጊዜም ለውጥ ከመሪዎች ሳይሆን ከሥር ነው የሚጀምረው፡፡ ስለዚህ ሀገረ ስብከታችን ከሁሉም ቀድሞ ለውጥ መጀመሩ ያኮራናል፡፡ እኛም የውጡ አካል በመሆናችን ደስተኞችም እድለኞችም ነን፡፡ ነገር ግን ስልጠናው ለአለቆች እና ለጸሐፊዎች እንዲሁም ለቁጥጥር ሠራተኞች ጭምር ቢሰጥ?
ሀገረ ስብከቱም ዘመኑን የዋጀ ሥራ እየሠራ ለመሆኑ ማየት ማመን ነው እንዲሉ፣ ሁሉም ኮምፒውተር ያልነበራቸው አብያ ክርስቲያናት ለሒሳብ ሹሞቻቸው ኮምፒዩተር በመግዛት እና በማዘጋጀት ላይ ናቸው፤ ለተግባራዊነቱም አብረን ነው መስራት ያለብን፡፡ ስለዚህ ሥልጠናው ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን አባል ቢያካትት? የሚሉና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን የተሰብሳቢዎቹን ጥያቄ ተከትሎ የሀገረ ስብከቱ ሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫኔ እዚህ ደረጃ ላይ እንደምንደርስ ግምቱ ነበረኝ፤ ውጤታማ እንደምንሆንም አውቅ ነበር፡፡
ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ምን እንደሆነ ሁላችንም እናውቀዋለንና ነው፡፡ ከየትም አልመጣንም፤ ሁላችንም የተገኘነው ከዚህችው ታሪካዊት እና ጥንታዊት ቅድስት ቤተክርስቲያን ስለሆነ ችግሩንም መፍትሔውንም እናውቀዋለን፡፡
አለማወቅ ለመዋሸት ያስደፍራል ስለዚህ ላለመዋሸት ማወቅ፣ ለማወቅ መማር፣ ወይም መሠልጠን እና ከሥልጠናው በየምናገኘው ችሎታ ራሳችንን ማሻሻል አለብን፡፡ በዚህም ስድባችንን እናርቃለን፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሃብት ላይ ነው ያስቀመጠች በአግባቡ በሥነ ሥርዓት እግዚአብሔርን በመፍራት ልናገለግል እና የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል፡፡ በእውነት እና በትክክል ከሠራን ቅዱስ ሲኖዶስን ጨምሮ ለቤተ ክርስቲያን እድገት የሚያስቡ አካላት እንደሚደሰቱብን እርግጠኛ ነኝ፡፡
በነገራችን ላይ ሥልጠናው የተጀመረው በ2000 ዓ.ም ነበር ስኬታማ መሆን ግን አልተቻለም ምክንያቱም በሀገረ ስብከቱ የነበርን ሰዎች ይህንን ስኬታማ ለማድረግ አቅሙም ዝግጅቱም አልነበረንም፡፡ አሁን ግን እድሜ ለሊቀ ማእምራን የማነ ተሳክቷል፡፡ ሥልጠና ሲባል አሳ እንዲበር ወፍ እንዲዋኝ ማድረግ አይደለም ዓላማው፣ አሳ በፍጥነት እንዲዋኝ ወፍም በፍጥነት እንዲበር ማድረግ በማለት ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የሀገረ ሰብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የመጀመሪያው አቅም ለውጥ መፈለግ ነው በዚህ ስብሰባ ላይ የማየው መንፈስ ይህንን ነው የሚያስረዳው በዚህም እድለኞች ነን፡፡ በሰለጠነው ዓለም ዶክተሮች ሳይቀሩ በየጊዜው የሙያ ማሻሻያ ይወስዳሉ፡፡ የሙያ ማሻሻያውን ካልወሰዱ ለሚሠሩት ሥራ ብቁ መሆን አይችሉም በዚህም የሚያሠራቸው ተቋም እና ሚሠሩት ሥራ ማግኘት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ተፈላጊዎች ለመሆን በየጊዜው ሥልጠና መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እኛም በየጊዜው ሞያችንን ካላሻሻልን እውቀታችን ያረጃል ስለዚህ ስልጠና እውቀትን ለማደስ እና አዳዲስ ግኝቶችን ለማወቅ ያስፈልገናል፡፡
በእኛ መ/ቤት (ቤተ ክህነት) ሰው ክፉ እና ደግ ተብሎ ብቻ ነው የሚከፈለው፡፡ ይህ ደካማ አመለካከት ነው፡፡ ሰው በእውቀት በአመለካከት ነው መመዘን እና መለየት ያለበት፡፡ ብዙ አቅም ያለው ሰው በቤተክርስቲያን ውስጥ አለ ለምሳሌ ሊቀ ጠበብት ኤልያስን ማየት ይቻላል፡፡ የሥልጠና ማንዋሉን የሰራው እሱ ነው ከብዙ ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ ነው ማንዋሉ ያለፈው የእኛ ስለሆነ ብቻ ግን ዝም ብለን ወደ ሥልጠና አልገባንም የተሸሉ የተባሉ የሂሳብ ባለሙያዎች፣ በሒሳብ ሥራ ላይ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሰዎች ከገመገሙት በኋላ ነው ማንዋሉን ለሥልጠና የተጠቀምንበት ስለዚህ ከተጠቀምንባቸው ቤተክርስቲያናችን የሰውም ሆነ የእውቀትም ደሃ አይደለችም፡፡
በነገራችን ላይ እኛን የሚነቅፉን ሰዎች በሁለት ይከፈላሉ የመጀመሪያዎቹ እዚህ መግባት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ዲግሪ አላቸው ግን በዓለማዊ ሥራ ተወዳድረው ገብተው ሥራ መሥራት አይችሉም ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ወደዚህ ቤት ገብተው እኛ እናውቅላችኋለን በማለት ማተራመስ ነው፡፡
ሁለተኛዎቹ በእኛው ተቋም ውስጥ ያሉ ነገር ግን ደመወዝ እንጂ ሥራ የሌላቸው ማለትም በቤተክርስቲያኗ ሥር ሠራተኞች ተብለው ተቀጥረዋል፤ ቤተክርስቲያኗ ደመወዝ ትከፍላቸዋለች፤ ሥራ ግን የላቸውም ምክንያቱም መሥራት አይችሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ጨመረ ቀነሰ? ማን ተዛወረ? ማን ተቀጠረ? ማን ገባ? ማን ወጣ? በማለት የወጣ የገባውን ሲቆጥሩ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚነቅፉን ሰዎች ሥራ ፈትና ሥራ ፈላጊዎች እንጂ ትክክለኛ ተቺዎች አይደሉም፡፡ በመሰረቱ አሁን ስድባችን ቀንሷል፡፡ ከአምስት ወራት በፊት የምንሰደብበት ስድብ አሁን የለም መረጃ ከላይ ወደታች ወይም ከታች ወደ ላይ የሚፈስ ከሆነ መግባባት አለ ማለት ነው፡፡ ያነሳችሁት ጥያቄ መግባባት መኖሩን ነው የሚያመለክተው ካሉ በኋላ ክቡር ሥራ አስኪያጁ ከተሰብሳቢዎቹ የተነሱትን ጥያቄዎች እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
ንብረት የሚቆጥሩ ሰዎችን በተመለከተ የሚመጡት መመዘኛ ወጥቶላቸው በጋዜጣ ማስታወቂያ አውጥተን ከመጡት መካከል ፕሮፋይላቸውን ታይቶ የተሻለ አቅም እና ልምድ ያላቸውን ነው ለመምረጥ የታሰበው፡፡ ሁላችሁም በማስታወቂያ ነው መጋበዝ ያለባችሁ፡፡ ዝም ብሎ የፈለጉትን ሰው አምጥቶ ማሠራት ተገቢም አግባብም አይደለም፡፡
ከተለያዩ ግለሰቦች በስጦታ የተበረከቱ ወይም የተሰጡ ንብረቶችን በተመለከተ ከተቻለ የተገዙበትን ሪሲት ማቅረብ ካልተቻለ ደግሞ ንብረቱን ወይም እቃውን ባለበት ሁኔታ ላይ ባለሙያው የሚሰጠውን ግምት መቀበል፣ በቤተክርስቲያን በገንዘብ የማይተመኑ ንብረቶች አሉ ለምሳሌ ቅርሳ ቅርስ፣ ሕንፃ ቤተክርስቲያን፣ እንደ ጽናጽል ከበሮ እና ልብሰ ተክህኖ ሌሎችም የብራና መጻሕፍትን ጨምሮ በዋጋ የማይተመኑ ቋሚ ቅርሶች ናቸው፡፡ በንብረትነት የሚመዘገቡ ንብረቶች ለመንፈሳዊ አገልግሎት የምንጠቀምበትን አውደ ምሕረቱን ሳይጨምር ለልማት አገልግሎት የሚሆን መሬት በካሬ ተሰልቶ፣ ለልማት የሚሆኑ ከሕንፃ ቤተክርስቲያን ውጪ ያሉ ሕንፃዎች በሙሉ በዚህ ሲስተም ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
በመጨረሻም ለሁሉም የቤተክርስቲያን ሠራተኞች ሥልጠናው መሰጠት አለበት የተባለው እኛም አስበንበት እየተዘጋጀንበት ነው፡፡ እኛንም በአመራር ላይ ያለነውን ጨምሮ ሁላችንም በየጊዜው ራሳችንን በሥልጠና እያጠናከርን አቅማችንን ማጐልበት አለብን፡፡ በመሠረቱ ወደዚህ ለውጥ ለመሸጋገር ስናስብ ዝም ብለን በስሜት አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ወሳኝ ለሆነው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሁም ለቅዱስ ፓትርያርኩ አቅርበን አስፈቅደን ነው፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ጠቅላላ የሀብት መጠን ይታወቃል፡፡ ምክያቱን በዘመናዊ መንገድ ነው እየተሠራ ያለው በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡
የስብሰባው ታዳሚዎችም ማለትም የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች አዲሱን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተው ስብሰባው ተጠናቋል፡፡
{flike}{plusone}