የአዲስ አባ ሀገረ ስብከት በአዲሱ አስተዳደራዊ የመዋቅር ሰነድ ዙሪያ ያደረገውን የ2 ቀናት ውይይት በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ህዳር 17 ቀን 2006 ዓ/ም የተጀመረው የአዲሱ መዋቅር ሰነድ በ8 ዓበይት ርዕሶች የተከፈለ ሲሆን የሰነዶቹም ዝርዝር ረቂቅ የአደረጃጀት ሰነድ፣ የፋይናንስ መመሪያ ሰነድ፣ የግዥመመሪያ ሰነድ፣የልማትመመሪያ ሰነድ፣ የዕቅድመመሪያ ሰነድ፣ የቁጥጥርመመሪያ ሰነድ፣የስልጠናመመሪያ ሰነድ፣የአብያተ ክርስቲያናትመመሪያ ሰነድ አጠቃላይ ባለአስራ ሶስት ጥራዝ መሆኑን ከአቅራቢዎቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ 950 እስከ 1,000 የሚደርስ ገፅ አለው ፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የክፍል ኃላፊዎች፣ እና የዋና ክፍል ኃላፊዎች ፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እና የሰው ሀብት ክፍል ኃላፊዎች በረቂቅ ሰነዱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡የተለያዩ ገንቢ ሐሳቦችም ከተሳታፊዎቹ ተሰጥቶአል፡፡
በመጨረሻም የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ እንዲህ ነበርን ከማለት ይልቅ አሁንም አለን ማለት ይኖርብናል አባቶቻችን ብዙ ሥራ ሠርተው አልፈዋል፡፡ መሪጌታ፣ደብተራ እየተባሉ እየተጠሩ የፍርድ ቤት ዳኞች ፣ጠበቆች እና ዐቃብያነ ሕጎች ነበሩ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የሕግ አውጪ እና ሕግ ተርጓሚ ነበረች፡፡ከዚህም ጎን አባቶቻችን እንደ ግሸን እንደ ደብረ ዳሞ ያሉትን ተራራዎች እየወጡ ብዙ ሥራ ሠርተው አልፈዋል፡፡
እኛ ዛሬ የነሱን ሥራ ጎብኚዎች ብቻ መሆን የለብንም እኛም በዘመናችን ታሪክ መሥራት አለብን፡፡ አባቶቻችን ያወረሱንን ታሪክ ከነትውፊቱ ተቀብለን እና ጠብቀን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የቤተክርስቲያንን መብት ለማስከበርና ቤተክርስቲያኒቱን በልማት ለማሳደግ በሚሰሩበት ወቅት ብዙ ፈተና እንዳጋጠማቸው ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ የመጡ እንግዶች አዲስ ሥራ ሠርተው ለመታወቅ ጥራት ያደርጋሉ፡፡ እኛ ግን አባቶቻችን የሰሩትን እና ያስረከቡንን ታሪክ መጠበቅ አቅቶናል፡፡ አሁን ባለው ዘመናችን አንዱ ሌላውን ማጥላላት እና መተቸት ብቻ ነው የሚቀናው፡፡ አዲስ አበባ ሀገረ ስከት የመላው ቤተ ክርስቲያናችን የደም ሥር ነው በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያናችንን በር የሚከፍተው አዲስ አበባ ነው ፡፡ አንድ አምራች ገበሬ የሚጓዘው ምርት ወደሚገኝበት ማሳ ነው፡፡
ስለዚህ ሁላችንም ለምንፈልገው የዕድገት ለውጥ መረባረብ ይኖርብናል፡፡ በ2005 ዓ/ም የበጀት ዓመት ፍጻሜ ላይ ከታየው የፐርሰንት ገቢ ዕድገት በመላው ሀገራችን የሚገኙት አህጉረ ስብከት ከሰላሳ ሚሊዮን ያልበለጠ ፐርሰንት ሲያስመዘግቡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ግን ከሃምሳ አምስት ሚሊዮን ያላነሰ የፕርሰንት ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
ይህ ሊሆን የቻለው ቀደም ሲል የነበረው አመራር የጋራ ጥረት በማድረጉ የተነሳ ነው ፡፡ ለወደፊቱም ከዚህ የተሻለ የዕድገት ለውጥ ለማምጣት ሁላችንም ተባብረን እና ጠንክረን መስራት አለብን፡፡ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል፡፡
ታለቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሰው የተመኘውን ካገኘ የሚጠብቀው ጊዜ ሞቱን ነው እንዳሉት ሁላችንም የምንመኘውን ዕድገት ለማምጣት መጠንከር አለብን፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰፊ ሥራ የሚከናወንበት ሀገረ ስብከት ነው ቢባልም ከዚህ ቀደም ግን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተብሎ የወጣ መዋቅር አልነበረም፡፡
በዋናው ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየጊዜው የሚወጡ አንድ አንድ መመሪያዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በሚመለከት ወደፊት ሊወጣ ይችላል እያሉ ከመጠቆም በስተቀር ምንም ዓይነት የወጣ መመሪያ አልነበረም ፡፡ በዚሁ መሠረት የተሻለ መመሪያ እንዲወጣ በባለሙያዎች ተጠንቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበውን የመዋቅር ሰነድ ከታች ጀምሮ ሐሳብ እንዲሰጥበት እና በቋሚ ሲኖዶስ ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል በሰጠው መመሪያ መሠረት በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይቱ እየተደረገበት ይገኛል፡፡
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ሐሳብ እንዲሰጡበት ይደረጋል፡፡ መመሪያው የእግዚአብሔር ቃል ባለመሆኑ ሊሻሻል የሚገባው ነጥብ ካለ ይሻሻላል፡፡ ነገር ግን ሁሉን ነገር በቀና አመለካከት ልንመለከተው ይገባል፡፡
እኛ ነገ እናልፋለን ለሚተካው ትውልድ መልካም ምሳሌ ሆነን ማለፍ ይኖርብናል፡፡ እኛ ከተሰማማን ያልተስተካካለውን ማስተካከል አይከብደንም፡፡ ሁላችንም የረቂቅ ሰነዱ አቅራቢዎች ልንሆን ይገባናል፡፡ ሁላችንም የለውጥ መሪዎች መሆን ይኖርብናል ፡፡ከሁላችንም የሚጠበቀው እየተራረምን መሥራት እንጂ መተማማት አይደለም በማለት ብፁዕነታቸው ለተሳታፊዎቹ መልእክታቸውን ካስተላለፉ በኃላ መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል::
{flike}{plusone}