በአ/አ/ ሀገረ ስብከት በመዋቅርና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ ላይ ለ2 ቀናት ሲካሄድ የቆየውን የመጀመሪያ ዙር የውይይት መርሃ ግብር ተጠናቀቀ

                                                     በሀገረ ስብከቱ አይቲና ዶክሜንቴሽን ክፍል

0006

ህዳር 17 እና 18/2006 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፤የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፤የሀገረ ሰብከቱ የዋና ክፍል እና ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ለ2 ሙሉ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መልካም የሥራ ጅምር የሆነውን የሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ ላይ ለአዘጋጆችና አቅራቢ ባለሞያዎች ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና በተሞላበት መንፈስ ህዳር 18/2006 ከቀኑ 11፡45 ሰዓት ላይ ተጠናቅቋል፡፡

መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነዱ 13 ጥራዞች ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ እስከ 1,000 የሚደርስ ገፅ አለው ፡፡

 

 

 

 

በ2ቱም ቀናቶች ውይይት ከተካሄደባቸው ረቂቅ ሰነዶች መካከል፡-

1. አጠቃላይ ስለ መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ ገለፃ

2. ስለ አዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ደረጃ አሰጣጥ ረቂቅ ሰነድ

3. በሰው ኃብት አስተዳደር ረቂቅ ሰነድ

4. በፋይናንስ መመሪያ ረቂቅ ሰነድ

5. በግዥና ንብረት አስተዳደር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ

6. በልማት መመሪያ ረቂቅ ሰነድ

7. በዕቅድና ሪፖርት መመሪያ ረቂቅ ሰነድ

8. በቁጥጥር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ እና

9. በሥልጠና መመሪያ ረቂቅ ሰነድ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በእያንዳንዳቸው ላይ ጥያቄና የቡድን ውይይት እንዲደረግ የተደረገ ሲሆን በተለይም ለቡድን ውይይቱ የተሠጠው ክፍለ ጊዜ ክፍተኛ ነበር የቡድኖቹ ስም በ4ቱ ወንጌላውያን ስም የተሰየመ ሆኖ እያንዳንዱ ቡድን(ማቴዎስ፤ማርቆስ፤ሉቃስ እና ዮሐንስ)ከ20 ያላነሱ አባላት የነበሩት ሲሆን ሰብሳቢ የመምሪያ ኃላፊዎች፤ ፀሐፊዎች ደግሞ የዋና ክፍል ኃላፊውች ሆነው ተሰይመዋል፡፡

በዚሁ ሁኔታ ለ2 ቀናት ሙሉ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መርሃ ግብሩ እጅግ አስተማሪና አስደሳች የውይይት መርሃ ግብር ነበር፡፡በዚህ መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ ላይ በቀጣይ ቀናቶች ከ7 ክፍለ ከተሞች እና እንዲሁም በሥራቸው ካሉት ከሚያስተባብሯው ገዳማትና አድባራት የተውጣጡ የክፍላተ ክተማ ተወካይ ሠራተኞች፤የገዳማትና አድባራት የጉባኤ መምህርን፤የአስተዳደር ሠራተኞች፤የካህናት፤የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ከእያንዳንዱ ገዳማትና አድባራት ከ16 ያላነሱ ተሳታፊዎች የሚገኙ ሲሆን የውይይት መርሃ ግብሩም ለ2 ቀናት ሆኖ ህዳር 27፣28፣29 እና 30 የ2ኛው ዙር መርሃ ግብር እንዲሁም ታሕሣሥ 4፣5፣6፣7፣11፣12፣13 እና 14 የ3ኛው ዙር የውይይት መርሃ ግብር ይካሄዳል:: ሙሉ የመስተንግዶና ልዩ ልዩ ወጪውም በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ይሸፈናል፡፡

በአጠቃላይ ከ2,662 በላይ ተሳታፊዎች በመዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ይህ መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ በገንዘብ ቢሠራ ኖሮ ከ2,000,000 ብር በላይ የገንዘብ ወጪ ይጠይቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቋንቋ አገላለፅ መዘጋጀቱና እንዲሁም የነበረውን ወቅታዊ የሀገረ ስብከቱ የመልካም አስተዳደር ችግር በግልፅ ያሳየ እና ሙሉ መፍትሄውን በዝርዝር ያስቀመጠ በዓይነቱ ልዬ የሆነ ጥናት ነው፡፡

ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብሎም ለሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል የሚሆን ሥራ በመሆኑ ለአጥኝ ቡድን አባላት ክፍተኛ የሆነ ምስጋና ይገባቸዋል ፤ቀሪ ዘመናቸውን እግዚአብሔር አምላክ በደስታና በጤና እንዲያኖራቸው/እንዲጠብቃቸውና በመጨረሻም በማያልፈው የመንግስተ ሰማያት ወራሾች እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እንደምታስባቸው ጉባኤው ገልጿል፡፡

የመጀመሪያው ዙር ለ2ት ቀናት ሲካሄድ የቆየውን የውይይት መርሃ ግብሩን በሰብሳቢት የመሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳትና የጂማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የውይይት መርሃ ግብሩን በፀሎት ሲዘጉ ባስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የሥነ ጥበብ፤የካላንድር ፤የሥነ ፅሁፍ፤የሥነ ህንፃ፤የታሪክ፤የህግ፤የትምህርት፤የልማትና የመልካም አስተዳደር ባለ ቤት የነበረች መሆንዋን አውስተው እንደ ቀደምት አባቶቻን አዲስ ነገር መሥራት አቅቶን የተሠሩትን ድንቅ ሥራዎች መጠበቅ አለመቻሉ ሁሌ እንደሚያሳዝናቸው ገልፀዋል፡፡ለመጪው ትውልድ ምን አስተላለፍን እንደምንሄድ ሁሌ ያስበኛል ብለዋል፡፡

መልካም አስተዳደርና ፍትህ ከቤተ ክርስቲያን ካልተገኙ ከየትስ ሊገኝ ይችላል?አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሀገሪቱ ዋና መዲና የሚገኝ ሀገረ ስብከት በመሆኑ በዓመት ከ58,000,000 ብር በላይ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ፈሰስ በማድረግ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በመድረግ ላይ የሚገኝ ሀገረ ስብከት ከመሆኑም በላይ የተጎዱት የገጠሪቱ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ከዚሁ ሀገረ ስብከት መሆኑን አስታውሰው ያለውን የገንዘብ፤የንብረትና የሰው ኃይል አጠቃቀም በአግባቡ ብንጠቀምበት ኖሮ ለሌላም መትረፍ እንችል ነበረ ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሁን በባለሞያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበው እና በዓይነቱ ልዩ የሆነው መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ ያስፈለገበት ምክንያት በሀገረ ስብከቱና ሀገረ ስበከቱ በሚመራቸው ገዳማትና አድባራት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ፈትቶ ዘላቂነት ያለውና እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ሥራ ለመስራት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

m001
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የሠሯቸውን ወርቃማ ሥራዎች በማውሳት ለምሳሌ ቃለ ዓዋዲ፤ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት የመሳሰሉ የተቀደሱ ሥራዎች ሲሠሩ በወቅቱ ብዙ ፈተና ቢገጥማቸውም በአሁኑ ሰዓት ግን ለቤተ ክርስቲያንዋ ምሶሶዎች ሆነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት መስጠት በመቻላቸው ሁሌም ስማቸው ከመቀብር በላይ ሲጠራ/ሲነገረ ይኖራል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት፤አገልጋዮችና ምዕመናን በጋር የዚሁ የተቀደስ ሥራ ባለ ቤትና ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪቸውን አስተላልፈዋል፡፡

{flike}{plusone}