የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ባለ 16 ነጥብ የአቋም መግለጫ አወጡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መ/ር ጎይቶኦም ያይኑ፤የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት፣በቅዱስነታቸው ጸሎት የተከፈተው መርሐ ግብር በቤተክርስቲያናችን ብሎም በሐገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በመመካከር ሥራችንን እንፈትሽ፤አንድነታችንን እናጠናክር፤ቤተክርስቲያንችንን እንጠብቅና መብታችንን እናስከብር በሚል ሐሳብ የካቲት 8/2010 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር ተደርጓል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩም፡- አሁን በሀገራችን ላይ እየተደረገ ያለው የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ እንዳይመጣ የጥፋቱ አሻራም ወደ ትውልድ እንዳይተላለፍ የእኛ የአገልጋዮች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንና ሁሉም ነገር በሥርዓትና በሕግ እንዲፈታ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠል መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ ይህ ከባድና ጽኑዕ ተጠያቂነቱ መንታ (ሰማያዊና ምድራዊ) የሆነ የኃላፊነት ቀንበር ትክሻችን ከወጣ ዘንድ እንዴት መሥራት እንዳለብን፤ ምን ላይ እንደቆምን፤ አካባቢያችን ምን እንደሚመስል መቃኘት እንድንችል፣አሠራራችንን እንድንፈትሽ፤ አንድነታችንን እንድናጠናክር፤ መብታችንን እንድናስጠብቅ፤የሥራ አፈፃፀማችን ምን መምሰል እንደሚገባው አሠራራችንን ለመፈተሽ ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው የውይይት መድረክ መክፈት፣መነጋገርና መወያየት ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ መሆኑን፤የገንዘብ/ የሀብት ንብረት አያያዛችን ለሕዝብ ግልጽና ተአማኒ እንዲሆን፣የካህናትና የምእመናን ግንኙነት ጠንካራና ጤናማ መደማመጥና መከባበር የነገሠበት እንዲሆን አስተዳዳሪዎቻችን በየአጥቢያው በሚገኙ በካህናት፣ በምእመናንና ወጣቶች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ወይም በጎ ተጽእኖ ፈጣሪነትን ለማሳደግ ብሎም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አሠራር ተጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ የዚህ ዓይነቱ ውይይት እንደሚኖር በዚህም መሠረት ምንም እንኳን ወቅቱ የጾምና የጸሎት ቢሆንም ጸሎትን ከሥራ ሥራን ከጸሎት ጋር እያጣመርን መጓዝ ስለሚገባን ያሉብንን ጉድለቶች በማረም ጠንካራ ጎናችንን ይበልጥ በማጎልበት በሚያስችል ሁኔታ ላይ በጥልቀት እንድንወያይ በሚል የተናገሩትን መነሻ በማድረግ ጥልቅ ውይይት ከተደረገ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
1.ከቅዱስ ሲኖዶስና ከቅዱስ አባታችን በሚሰጠን አንድ ወጥ መመሪያ መሠረት ለመሥራት አንድነታችንንና ሕብረታችንን አጠናክረን ቤተ ክርስቲያንና ሕዝብን ከችግር ለመጠበቅ የጠራውን እውነተኛይቱን የኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ለሕዝባችን በጠራ መንገድ ከወትሮው የበለጠ ለማስተማር ቃል ገብተናል፣
2.የክርስቶስ የማዳን ትምህርት ዘርና ጎሳን ሕዝብና አሕዛብን አንድ ያደረገ ወደ አንዲት ሰማያዊ መንግሥት የሚጠራ ትምህርት መሆኑን ስለ ምንረዳ በክርስቶስ ትምህርትና ከአባቶቻችን በወረስነው ትምህርት መሠረት ዓለም የሚገለገልበት የዘር የቀለም የጎሳ የቋንቋ ልዩነት የቤተ-ክርስቲያናችን መግለጫ ባለመሆኑ ልዩነትን አስወግደን እንደ ቤተክርስቲያን ሰው በፍቅር እየሠራን ምሳሌነታችንን በተግባር ለማረጋገጥ ቃል ገብተናል፡፡
3.በአደረግነው ጥብቅ ውይይትና ምክረ ሐሳብ ደረጃ በተስማማነውና በተማመነው መሠረት በአሁኑ ጊዜ የዚችን ታሪካዊትና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ነፋስ የማያወዛውዘው ማዕበል ሞገድ የማያናውጠው መዋቅሯን በመፈተን ረገድ ያልተለመደና ክርስቲያናዊ ያልሆነ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ጠባይና ጠረን የሌለው እንግዳ ክስተቶች አልፎ አልፎም ቢሆን ምልክታቸው እየታየ በመሆኑ ምእመን አያያዛችን እጅግ የጠበቀ እንዲሆን፣ አዳዲስ እንግዳና ያልተለመደ ባዕዳን ድርጊቶች እየተከሰቱ ነው በተለይም በቅርቡ በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያምና ቅ/ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል የአጥቢያ አባልነታቸው እንኳን በውል ባልታወቁ ግለሰቦች ስብስብ የተከሰተውን ችግርና አደጋ በጽኑ እንቃወማለን ለወደፊቱም ድርጊቱ በቅዱስ ሲኖዶስና በቅዱስነትዎ እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩና በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰቶ መንግሥት የቤተክርስቲያንን ህልውና በመጠበቅ ረገድ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ችግሩ በሕግ አግባብ እንዲፈታ እንዲደረግልን እየጠየቅን ይችን ቤተክርስቲያን ከጥፋት ለማዳን በሚደረገው ርብርቦሽ ላይ ሁላችንም ከሀገረ ስብከቱና ከቅዱስነትዎ ጎን ለመቆም ቃል ገብተናል፡፡
4.በአንዳንድ ቦታ እየተከሰተ ያለው ሂደት የበለጠ ተግተን እንድንሠራና የማንቂያ ደወል እንደሆነ በመረዳት በቅድሚያ የእኛን አሠራር በሚገባ ፈትሸን ራሳችንንም እየፈተሸን በሥራ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶች ካሉ እያረምን አጥፊዎችን በሕግ አግባብ ብቻ በማረም በሕገ-ወጥ አካሂድ የሚንቀሳቀሱ ክፍሎች ምንጫቸው ማን እንደሆነ ከየት እንደሆነ ማን እንደላካቸው በማጥናትና በመረዳት በሕግና በአሠራር ለመግታት ተስማምተናል፡፡
5.ስብከተ ወንጌል የእግዚአብሔር ሐሳብ ወደ ሰው ልጆች የሚደርስበት አመጸኛውን ትሁት ቀማኛውን መጽዋች የምናደርግበት የአገልግሎት ትልቁ ዘርፍ በመሆኑ የወንጌል አገልግሎታችንን ከወትሮው በበለጠ አጠናክረን በመቀጠል የተለየ አመለካከት ያላቸውን በእግዚአብሔር ቃል በማነጽ ከተሳሳተ መንገድ እንዲጠበቁ ለማድረግ ቃል ገብተናል፡፡
6.የሰንበት ት/ቤት ልጆቻችን በሃይማኖትና በመልካም ሥነ ምግባር ታንጸው የሚያድጉበት ቢሆንም በሚጠበቀው ዓላማ መሠረት እንዲሆን በአግባቡ ካልተያዘ ወጣቱ ትውልድ ለሠርጎ ገብ አስተሳሰብ ቅርብ በመሆኑ ይህን በመገንዘብ ወጣቱ ሃይማኖቱን እንደ አባቶቹ ሥልጣኔን እንደዘመኑ ይዞ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግል ከአፍራሽ አስተሳሰብ እንዲርቅ አባቶቹን የሚያከብር የሚከተል ቤተክርስቲያኒቱን ለመረከብ ብቁ የሆነ ትውልድ የማነጽ ኃላፊነታችን ለመወጣት ቃል ገብተናል፡፡
7.የተቀመጥንበት የኃላፊነት ወንበር ተራ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ወንበር በመሆኑ ይህን ወንበር የማስከበር የማስጠበቅ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ትምህርት መሠረትነት የሠጠችንን መብትና ክብር ማስከበር አባቶቻችን አክብረውና አስከብረው እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም አክብረንና አስከብረን ለትውልድ ለማስተላለፍ አሠራራችን እናራሳችንን ፈትሸን አጥፊን በመለየት በታማኝነትና በትጋት ለመሥራት ቃል እንገባለን፡
8.የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደርና አሠራር እንከን የለሽ ለማድረግ የእርስ በርእስ አንድነት ተጎናጽፈን አጥፊ ሲገኝ ደግሞ ሀገረ ስብከቱ በጀመረው አግባብ በወቅቱ አጥፊዎችን ብቻ እጅግ በጥንቃቄ እየተለየ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ውሳኔ እየተሰጠ በአንፃሩ የኃላፊዎችና ሠራተኞች ሹመትና ምደባ ብቃትን ጥራትን የሥራ ልምድን ፣ የሥነ-ምግባርን፣ አገልግሎትንና የሥራ አፈፃፀም ውጤትን ያገናዘበ እንደሆን አበክረን እንጠይቃለን፡፡
9.በአሁኑ ጊዜ እንደማንኛውም አስነዋሪ ተግባር ቤተክርስቲያንን እየፈተነ ያለው በክርስቶስ ትምህርት የሌለ አባቶቻችን ያላስተማሩን ያላስረከቡን አካባቢያዊ ጠባይና አመለካከት ከአሁኑ ካልተገታ ጥፋቱ ቀላል ስለማይሆን የክርስተናውንም ዓላማ የሚያናጋና የሚያደበዝዝ በመሆኑ ተምረናል አውቀናል ተራቀናል ካልን ከዚህ አስተሳሰብ ራሳችንን ነፃ አድርገን አርአያ ሆነን የምንመራውን ካህንና ሠራተኛም ነፃ ለማድረግ ይህንም በሥራ ለማሳየት ከልብ ተስማምተናል፡፡
10.በአንዳንድ አጥቢያ የሚኖሩ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተሰነዘረ ያለው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የቤተ ክርስቲያናችንን ሉዓላዊነት የሚፈትን የግለሰቦቹንም ክርስትና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ አስተሳሰቡንና ድርጊቱን አጥብቀን እንቃወመዋለን በአንጻሩ መደማመጥ መከባበር እንዲሰፍን እንደሰለጠነ ትውልድ ክብር ይግባቸውና አባቶቻችን እንዳቆዩን መመካከር መወያየት በሐሳብ የማመንና የማሳመን ኢትዮጵያዊነት ባህላችንን አጠናክረን ለመቀጠል ተግተን ነቅተን ለመሥራት ቃል ገብተናል፡፡
11.ዛሬ እንደተወያየነው ሁሉ ደካማ ጎናችንን አርመን ጠንከራ ጎናችንን አጠናክረን በቤተ ክርስቲያኒቱ መመሪያ ቀኖናና ሥርዓት መሠረት ሠርተንና አሠርተን ራሳችንና ቤተክርስቲያናችንን ከችግር ለማዳን ጠንክረን ለመሥራት ቃል ገብተናል፡፡
12.ከአባቶቻችን የተረከብነውን የመሪነት አደራና ሓላፊነት ጠብቀንና አስጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን፡፡
13.አሁን ባለን የስብከተ ወንጌል ትምህርት ብቻ ሕዝቡን በትምህርት መድረስ አጥጋቢ ሰለማይሆን ካህናት ከቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት፣ ከቅዳሴ፣ ከማህሌት ባሻገር ከምእመናን ጋር ያላቸው ግንኙነት ተጠናክሮ ባላቸው ዕውቀትና ተግባቦት ምእመናንን ቤት ለቤት በሰንበቴ በማህበር እንዲያስተምሩ ለማድረግ ተስማምተናል፡፡
14.ግለሰባዊ አመለካከት ትተን ተቋማዊ አስተሳሰብ ተጎናጽፈን በተሰጠን ሓላፊነት መሠረት ሕግንና መመሪያን መሠረት አድርገን ለመሥራት ተስማምተናል፡፡
15.አንድነታችንን አጠናክረን እራሳችንን ፈትሸን አሰራራችንን አስተካክለን የቅዱስ ሲኖዶስና የቅዱስነትዎን መመሪያ በመቀበል ቤተክርስቲያናችንን ለመምራትና አገልግለን ለማስገልገል በጽኑ ቃል እንገባለን፡፡
16.በሁለተኛው የውይይት መርሐ ግብር ላይ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ከቅዱስነታቸውና ከቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን እየተቀበለ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተናል ፡፡
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን፡፡