“150 ተፈናቃይ አገልጋዮችን” በተመለከተ ሀገረ ስብከቱ ወደ ሥራ መድቦ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ
በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነላቸውን “150 ተፈናቃይ አገልጋዮችን” በተመለከተ ሀገረ ስብከቱ ወደ ሥራ መድቦ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መሪነት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ፣ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሁሉም ሠራተኞች የተሳተፉበት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና የውይይት መርሐ ግብር ተካሒዷል።
በመርሐ ግብሩ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነላቸው 150 ተፈናቃይ አገልጋዮችን በተመለከተ በሰው ኃይል አስተዳዳር ዋና ክፍል ሐላፊ በሊቀ ኅሩያን ባዩ ተዘራ፣ የ2017 ዓ/ም የሥራ ሪፖርትና ዓመታዊ የቅጽ አሞላል ሂደት በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ሐላፊ በመምህር ጥዑመ ልሳን እንዲሁም የ2018 ዓ/ም በጀት ዓመት የሥራ ዕቅዶችን በሚመለከት ደግሞ በመጋቤ አእላፍ ማሙየ ሸዋፈራው አጫጭር ማብራሪያዎችና ገለጻ ተሰጥቷል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በተለያዩ ጊዜያት በሀገረ ስብከቱና በአጥቢያ አስተዳዳር ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ አገልጋዮች ለሀገረ ስብከቱና ለበላይ መሥሪያ ቤት መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሁም ለቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ በቁጥር 150 ተፈናቃይ አገልጋዮችን ሀገረ ስብከቱ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመልሳቸውና በተገኙ ቦታዎች እንዲመድባቸው መወሰኑ የሚታወስ ነው።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ሀገረ ስብከቱ የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።
በግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ከመጡ ጀምሮም ተፈናቃይ አገልጋዮች ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ በሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የሰው ኃይል አስተዳደር ዋና ክፍል ሐላፊ ሊቀ ኅሩያን ባዩ ተዘራ ገልጸዋል።
በተለይ በሀገረ ስብከቱ የተፈናቃይ አገልጋዮችን የተሟላ ሕጋዊ የሥራ ሰውነትን የሚያረጋግጡ ዋናና ደጋፊ ሰነዶችን ከማሰባሰብ ጀምሮ ለሕጋዊ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ አሠራርን በመዘርጋት ረገድ እምርታ ያለው ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ሰነድ በማሰባሰቡ በተገኘው ውጤትም ከ150 ተፈናቃይ አገልጋዮች መካከል በርከት ያሉት ቅጥራቸው የመቅጠር ሥልጣን ባለው ሕጋዊ አካል የተፈጸመ እንዳልሆነ ያቀረቡትን ሰነድ ዋቢ አድርገው አስረድተዋል።
እንደማሳያም ከተፈናቀሉት መካከል ያልተመደቡት አገልጋዮች 52 ሲሆኑ ከነዚህ
#18 ቱ የመቅጠር ሥልጣን ባለው በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተቀጠሩ
#6ቱ የመቅጠር ሥልጣን በሌላው ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት
#27ቱ የመቅጠር ሥልጣን በሌለው በደብር
#1 ከሱዳን ካርቱም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ እንደነበር ማስረጃ ያቀረቡ አገልጋይ ነገር ግን በተፈናቃይ ስም ዝርዝር ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በአስረድተዋል።
በተጨማሪም ካልተመደቡት ከ52 ተፈናቃዮች መካከል 24ቱ አገልጋዮች የኮዬ ፈጨ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲመሠረት በደብሩ መሥራችነት የነበሩና በደብሩ ቅጥር የተፈጸመላቸው ሲሆን ይሁን እንጂ የሥራ መደባቸው እንዲጸድቅላቸው ለክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጥያቄ አቅርበው ያልጸደቀላቸው ናቸው።
ባልታወቀ ምክንያት ሀገረ ስብከቱ ሌሎች አገልጋዮችን መደቦብናል ብለው ላቀረቡት አቤቱታም የሸገር ሀገረ ስብከት ስለተባሉት ሠራተኞች ቅጥር እንደማያውቅ ገልጾ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብዳቤ ማሳውቁንም ሊቀ ኅሩያን ባዩ አክለው ገልጸዋል።
ካልተመደቡት ከ52 ተፈናቃይ አገልጋዮች የቆሬ ጌቴሴማኒ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን 14 ሠራተኞች መካከል 8ቱ የመቅጠር ሥልጣን ባለው አካል (ሀገረ ስብከት) የተቀጠሩ ሲሆኑ 6ቱ ደግሞ የመቅጠር ሥልጣን በሌለው ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የተቀጠሩ መሆኑቸውን ያቀረቡት ሰነዶቻቸው የሚያስረዳ ሲሆን በሀገረ ስብከቱ የጸደቀ ወርኃዊ ደመወዝ እንዳልነበረም የአቤቱ አቅራቢዎችን ሰነድና የእምነት ቃልን መሠረት አድርገው ዋና ክፍል ሐላፊው አብራርተዋል።
የሀገረ ስብከቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ዋና ክፍል ሐላፊ ያቀረቡትን በሰነድ የተደገፍን ማብራሪያ ያደመጠው ጉባኤው በጉዳዮቹ ላይ አስተያየትና ምክረ ሐሳብ በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች አማካኝነት ተሰጥቷል።
ሥራ አስኪያጆቹ በተለይም ሀገረ ስብከቱን ያለበትን ወቅታዊ ጫናን ለመጋራትና የሚጠበቅባቸውን ቤተ ክርስቲያናዊ ሐላፊነት ለመወጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው የሀገረ ስብከቱ ውስብስብ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከሁሉም የሥራ ሐላፊና ሠራተኛ ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
አክለውም ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሌሊት ከቀን አዙሪት ከሆነው ችግር ተላቆ መደበኛ የሆነው የሕያው ወንጌል ተልእኮና የራስ አገዝ ልማት ለመሠራት የሚያስችለውን ተግባር ተኮር ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውን በአድናቆት ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለቤተ ክርስቲያን ክብር የመሸነፍን ሕይወት፣ ኑሮየ ይበቃኛል የሚለውን ሐዋርያዊ መንገድን በመከተል ያሉብንን ተደራራቢ ሥራዎችን ለመፍታት በጋር መቆም ይኖርብናል ብለዋል።
ከተፈናቀሉ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ምን እንኳ ሰነዳዊ ማስረጃቸውና ቃላዊ ማረጋገጫቸው በቀጥታ ሀገረ ስብከቱን እንዲመድብ የሚያስገድዱ ጉዳዮች አጠያያቂ ቢሆኑም የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ማከብር ግዴታ በመሆኑና አሁናዊ ኑሮው የበረቱ ትከሻዎችን ባደከመበት ይልቁንም ብዙ ቤተሰብ ያላቸው ካህናትና ሠራተኞች በርኅብና በእንግልት ያሉ በመሆኑ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በዘመቻ መድበን ለማጠናቀቅ የተጠናከሩ ሥራዎችን እየሠራን ነው ብለዋል።
ለዚህም የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጆች የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና ሰበካ ጉባኤ አባላት ችግሮችን ለመፍታትና ወደ ቋሚ ቤተ ክርስቲያናዊ አደራ በሙሉ አቅም ለመመለስ በምናደርገው ርብርብ እንዲያግዙ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ ብለዋል።
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ