የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ130 ገዳማትና አድባራት የሒሳብ ሠራተኞች 3ኛ ዙር ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሥልጠና መስጠት ተጀመረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከ130 ገዳማትና አድባራት ለተወጣጡ የሒሳብ ሠራተኞችና ከሰባቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ለተውጣጡ 14 ሠራተኞች በዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሙያ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ተገጿል፡፡
ስልጠናውን የሚሰጡት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ ባለሙያዎችና ከሌሎች ተቋማት የተጋበዙ የሒሳብ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ የስልጠናው ጊዜ ከመጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት ይቆያል፡፡
ሰልጣኖቹ ስልጠናውን የሚወስዱት በቲኦሪ እና በተግባር ላይ በተመሠረተ አሠራር ነው፡፡ ሠልጣኞቹ ከብዛታቸው አንፃር የተነሣ በ3 ቡድን ተከፋፍለው ሁለቱ ቡድን በ4 ኪሎ በሚገኘው በሲፒዩ ኮሌጅ በኮምፒውተር (በተግባር) ስልጠናውን ሲወስዱ አንደኛው ቡድን ደግሞ በሀገረ ስብከቱ የሥልጠኛ ማዕከል በኮምፒውተር (በተግባር) እየወሰዱ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ለስልጠናው በተዘጋጀው የመማሪያ ዝግጅት ላይ በተብራራው መሠረት የሒሳብ አያያዝ ትርጉምና ታሪካዊ አመጣጡ፣ የዓላማችን የንግድ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት እያጎላው የመጣ መሆኑ፣ የመንትያ ሒሳብ (double entry) አመዘጋገብ ሲስተም ለሒሳብ አያያዝ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ፣ የሒሳብ አያያዝ ማለት ገንዘብ፣ ቋሚና አላቂ ንብረት መረጃዎች የሒሳብ አያያዝ መሆናችን መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ በአይነታቸው በማደራጀት፣ በመተንተን ለግምገማና ውሳኔ አሰጣጥ በሚያመች በሪፖርት የመግለፅ ሂደት፣ በሒሳብ መዝገብ ውስጥ የሚካተቱ የሒሳብ መረጃዎች፣ ቋሚ ንብረቶች የተገዙበትን ዋጋና አሁን ያላቸውን የመዝገብ ዋጋ ማሳየት፣ ሀብትና እዳን ለይቶ ማወቅ፣ በየቀኑ የተገኘውን ገቢና ወጪውን ከምክንያት ጋር ማያያዝ፣ የተገዙና የተሸጡ ዕቃዎችን አገልግሎት መለየት፣ የሽያጩ ግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ በመጋዘን የተከማቹ የንግድ ዕቃዎች አይነት ብዛትና ለዕቃዎች የተደረገውን ወጪ እንዲሁም ዕቃዎቹ የተገመቱበት ዘዴ፣ በሒሳብ ዘመኑ መጨረሻ በዕዳ ያሉትን ዕቃዎች ማሳየት፣ የግብር ዓመት፣ በባንክ እና በእጅ ምን ያህል ጥሬ ገንዘብ እንዳለ ማወቅ፣ ያልተሰበሰበ ገቢና ያልተከፈለ ዕዳን በመዝገብ ላይ የተመሠረተ የሒሳብ አያያዝ፣ የነጠላና ጥንድ (Single entry) (Double entry)፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ደረሰኞች፣ የንብረት መቀበያ ደረሰኞች የሚሉት የሥልጠናው ቁልፍ ሐሳቦች ሲሆኑ ሠልጣኞቹ በጋራ የተማሩአቸውን የሒሳብ መርሆች በመጀመሪያ በቲኦሪ ከተማሩ በኋላ እንደገና በግሩፕ እና በግል በመሥራት ተግባር ተኮር ሥልጠና ወስደዋል፡፡
ይህ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሙያ ስልጠና ባለፈው ዓመት እስከ 2ኛ ዙር የተሠጠ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ደግሞ በአይነቱ ልዩ የሆነው ይህ ስልጠና ለ3ኛ ዙር የተሰጠ እና የመጨረሻ የስልጠና ሂደት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የሰለጠኑት የአንደኛ እና የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች ወደ ተግባር በመግባት የሒሳብ አያያዙን ሥራ በዘመናዊ የሒሳብ አሠራር መሠረት ሲያከናውኑ የቆዩ ሲሆን በአሁኑ በ3ኛው እና በመጨረሻው ዙር የሠለጠኑ ሠልጣኝ የሒሳብ ሠራተኞች ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት ጀምሮ በተሰጣቸው ስልጠና መሠረት የሒሳብ አያያዙን ሥራ በዘመናዊ የሒሳብ አሠራር መሠረት እንደሚሠሩ ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም አሁን እየተሰጠ ያለው የዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሙያ ስልጠና እንደተጠናቀቀ በተመሳሳዩ የቁጥጥር ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እንደሚቀጥል የሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር አገልግሎት ዋና ክፍል አብራርቷል፡፡
ስለሆነም ሀገረ ስብከቱ ይህንን መልካም ተሞክሮ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል፤ የገዳማቱና የአድባራቱ ሠራተኞችም ትኩረት ሰጥተው ሥልጠናውን በተሻለ ንቃትና ትጋት ሊቀጥሉበት ይገባል እንላለን፡፡